የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን መቋቋም በሚመለከት ከጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት የተሰጠ መግለጫ
የሀገራችንን ሕዝቦች ጥቅም፤ መብት እና ነጻነት በጋራ እና በተደጋጋፊነት ለማሳደግና አንድ የኢኮኖሚ ማኅበረሰብ ለመገንባት የሚያስችሉ ዘርፈ ብዙ የሪፎርም ሥራዎችን መንግሥት እያካሄደ ነው፡፡
ከዚህ ሰፊ የሪፎርም ሥራ ጎን ለጎን የሀገራችንን ዘለቄታዊ ሰላምና የሕዝቦችን ደኅንነት በአስተማማኝ ሁኔታ ለማረጋገጥ እንዲቻል በተለያዩ ጊዜያት እየተነሡ ያሉ የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጉዳዮችን በሳይንሳዊ ዘዴ በማጥናት የመፍትሔ ሐሳብ የሚያቀርብ ኮሚሽን በአዋጅ እንዲቋቋም ተደርጓል፡፡
ኮሚሽኑ በዚህ ጊዜ የተቋቋመው ከማንነት ፣ ከአስተዳደር ወሰን እና ከራስ በራስ አስተዳደር ጥያቄዎች ጋር በተያያዘ በሃገሪቱ እያጋጠሙ ያሉ ችግሮች ስፋትና እያስከተሉ ያሉት ጥፋቶችን ለመከላከል እንዲቻል ጥናትን መሠረት ያደረገ የውሳኔ ሃሳብ ለሚመለከተው የመንግሥት አካል የሚያቀርብ ተቋም በማስፈለጉ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት ከሁሉም ማዕዘናት ማንነትንና የአስተዳደር ወሰንን በተመለከተ እየተነሱ ያሉ ጥያቄዎች በመደበኛ ሥርዓቱ ለመፍታት ሕገ መንግስታዊ አካሄድ እንዳለ ግልጽ ነው፡፡
እነዚህን ጉዳዮች እና ተመሳሳይ የመብት ጉዳዮች ጥያቄ ሲቀርብ ወይም አለመግባባት ሲኖር በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 48 እና አንቀፅ 62 ንኡስ አንቀፅ 3 እና 6 መሰረት ዉሳኔ የመስጠት ስልጣን የተሰጠው የፌደሬሽን ምክር ቤት መሆኑ በግልፅ ተደንግጓል፡፡
የፌደሬሽን ምክር ቤት ከላይ የተገለፀው በሕገ መንግስቱ የተሰጠው ጥቅል ስልጣን አፈፃፀም በአዋጅ ቁጥር 251/1993 መሰረት በመዘርዘር ተደንግጓል፡፡
በማንነትንና የአስተዳደር ወሰንን በተመለከተ እየተነሱ ላሉ ጥያቄዎች “በሕገ መንግሥቱ ምላሽ አግኝተዋል” በሚል ጥቅልና የግብር ይውጣ አያያዝ ጋር በተገናኘ አግባብ የሆኑት ጥያቄዎች በሕገ መንግሥቱ እና በአዋጁ በተገለጸበት አኳኃን ለሚመለከተው ክልል እና ፌደሬሽን ምክር ቤት ጥያቄ የማይቀርብበት ሁኔታ በመኖሩ የአገሪቱን ሕልውና አደጋ ላይ በመጣል ላይ ይገኛል፡፡
ጥያቄዎቹ ከብዛታቸው እና ከግጭት ባሕሪውያቸው ምክንያት በሕዝቦች ሰላምና ደህንነት ላይ እየጋረጠ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ እናም ኮሚሽኑ ተጨባጭ አደጋና ስጋት እየፈጠሩ ያሉ እነዚህ የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ጥያቄዎች ከጊዜ ወደ ጊዜ ተባብሰው ለአገር ህልውና ሥጋት የማይሆንበት ሁኔታ ለመፍጠር በመስኩ ምሁራን ጥልቀት ያለው ጥናት በማድረግ ሳይንሳዊ የሆነ ምክረ ሃሳብ ለሚመለከተው የመንግስት አካላት የማቅረብ ዓላማ አለው፡፡
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመሩ የመጡ መሠረታዊ የሆኑ የአስተዳደር ወሰን እንዲሁም የማንነት ጥያቄዎች “በሕገ መንግሥቱ ምላሽ አግኝተዋል” ከሚል ጥቅልና የግብር ይውጣ መልስ በዘለለ ጥናትን መሠረት ባደረገ መልኩ መታየት አለባቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ በበቂ የሰው ሀብትና በሕጋዊ ማዕቀፍ ቅቡልነት ያለው ብቁ ተቋም አስፈላጊ ነው፡፡
ከዚህ ቀደም ሰፊ ሕዝባዊ መሰረት ያላቸውን ጥያቄዎችን ባጭር መግለጫ በማዳፈን የተሄደበት አግባብ ለሀገራችን ሰላምና ለሕዝባችን አብሮነት እንዳልጠቀመ ሁሉም የታዘበው እውነታ ነው፡፡
“ምላሽ አግኝተዋል” የሚለው ምላሽ ትክክል አለመሆኑን የሚያሳየው ምላሽ የሚፈልጉ ጥያቄዎች እያደር እየጨመሩ ከመምጣታቸው ባሻገር የቀረቡት ጥያቄዎች በቸልተኝነት መታለፋቸው ጥያቄዎቹን ያነሱ የማሕበረሰብ ክፍሎች በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ የተቋቋሙ የአስተዳደር እርከኖችን አመኔታ ከመንፈግ በተጨማሪ ወደ አላስፈላጊ እርምጃ የመገፋፋት አዝማሚያ መገፋፋታቸው ሊታወቅ ይገባል፡፡
በአጠቃላይ ተገቢውን ምላሽም በአፋጣኝ የሚሰጥ ሥርዓት በየእርከኑ ስላልተዘረጋ ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣው ጥያቄዎች ሀገራዊ ሰላማችንን በማወክ ላይ ይገኛሉ። አንዳንድ ጉዳዮችም በማንነት ጠያቂዎች ብቻ ሳይታጠሩ የክልል መንግሥታትን ወደ ማጋጨት ደረጃ በመድረስ ላይ ናቸው። በየዘመኑ እየጨመሩ ለሚመጡና ተጨባጭ አገራዊና ክልላዊ ፈተናዎች ለሚጋርጡ ሕዝባዊ ጥያቄዎች ብቃት ያላቸው ተቋማት፤ አሰራሮችና ሥልቶችን ቀይሶ መንቀሳቀስ ጊዜው የሚጠይቀው እርምጃ ነው፡፡
ሕገ መንግሥቱ የሕጎች ሁሉ የበላይ መሆኑ ግልጽ እውነት የመሆኑን ያህል ሕገ መንግሥቱ ከጸደቀ በኋላ የተስተናገዱ የማንነትና የአስተዳደር ጥያቄዎች እንደዛሬው ሁሉ ትናንትናም እንደነበሩ መዘንጋትም የለባቸውም፡፡
ባለፉት ዓመታት ሲስተናገዱ የነበሩ የማንነትና የአስተዳዳር ወሰን ጥያቄዎች ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ጠብቀው የተፈጸሙ እንደሆኑ ሁሉ አሁንም በአንጻራዊ ብዛትና ሥፋት እየቀረቡ ላሉ ወቅታዊና አንገብጋቢ የመብት ጥያቄዎች ዘለቄታዊና አስተማማኝ ምላሽ የሚያገኙበትን ሁኔታ የሚያጠና እና ለሚመለከተው ሕጋዊ አካል የውሳኔ ሀሳብ የሚያቀርብ ኮሚሽን መቋቋሙ እጅግ አስፈላጊ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡
የማንነት፣ የራስ አስተዳደር እና የወሰን ጥያቄዎቹ ከወዲሁ በተጠናና ዘለቄታዊ በሆነ መንገድ ካልተመለሱ ሀገራችንን አደጋ ውስጥ መክተታቸው የማይቀር ነው። የኢትዮጵያ ሕዝቦች፤ ብሔሮች፤ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ማንነትንና አስተዳደር ወሰንን በተመለከተ ጥያቄዎች ሲያቀርቡ ይህ የመጀመሪያቸው አይደለም፡፡ ለዘመናት የታገሉለትና በፈቃዳቸውም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ያቆሙለት ነው፡፡
በዚህ ዘመንም ማህበረሰቦች ጥያቄ የማንሳት መብታቸውም ሕጋዊ እውቅና ያለው የተከበረና የተረጋገጠም ነው፡፡ የጥያቄዎቹ ሥፋት፤ ብዛትና ውስብስብነት ከጊዜ ወደ ጊዜ በመጨመሩና ግጭቶች በመበራከታቸው የፌዴሬሽን ምክር ቤት፤ የሰላም ሚኒስቴርና ሌሎች መንግሥታዊ አካላት ያላቸው ሕጋዊ ሥልጣንና ተግባር እንደተከበረና እንደተጠበቀ አስፈጻሚው አካል ለአንገብጋቢ ጥያቄዎች ምላሽ የሚያገኙበትን መንገድ መፈለጉ አግባብነት አለው፡፡
በመሆኑም መንግሥት የማንነት፣ የራስ አስተዳደር፣ እና የወሰን ጥያቄዎች በሕገ መንግሥቱ ከተቀመጡ መመዘኛዎች አንጻር በጥልቀት በመፈተሸ በሳይንሳዊ ጥናት ላይ በተደገፈ መልኩ የሚተነትንና ተገቢውን የመፍትሔ ሐሳብ የሚያቀርብ የአስተዳደር ወሰንና የማንነት ኮሚሽን እንዲቋቋም አድርጓል።
ኮሚሽኑም እነዚህን ወቅታዊና አንገብጋቢ ጥያቄዎች አገራዊ ሕልውናን አደጋ ላይ ሳይጥሉ አስቀድሞ አግባባ ላላቸው የመንግሥት አካላት የመፍትሔ ሐሳብ ለማቅረብ በጊዜያዊነት የተቋቋመ ነው፡፡
በብሔር ብሔረሰቦች መካከል የቅራኔ ምንጭ የሆኑና በተደጋጋሚ እየተነሡ ያሉ ጥያቄዎችን ገለልተኛ በሆነ፣ ሙያዊ ብቃት ባለው እና ሰላማዊ በሆነ መንገድ መፍትሔ የሚያፈላልግ ነው፡፡ ለዚህም ሥራው ሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ ልምዶችን በመያዝ ችግሮቹ በሠለጠነ መንገድ ለሀገርና ለሕዝብ በሚጠቅም አካሄድ የሚፈቱበትን የመፍትሔ አቅጣጫ ያመላክታል፡፡
የኮሚሽኑ አባላትም ሕገ መንግሥቱን ጠንቅቀው የሚያውቁ፣ ለሕገ መንግሥቱ ታማኝ የሆኑ፤ በፌዴራል ሥርዓቱ ላይ እምነት ያላቸው እና በሁሉም ክልሎች እና ሕዝቦች ዘንድ ተቀባይነት ያላቸው እንዲሆኑ ይደረጋል።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ