ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የተሰጠ መግለጫ
ይህ ወቅት በሕዝቡ ጠንካራ ትግል እየተረጋገጠ የሚገኘውን እመርታዊ ለውጥ የምናስቀጥልበት፣ በየጉባኤዎቻችንንና ውይይቶቻችን የለየናቸውን ቁምነገሮች መሬት አስነክተን የሕዝባችንን ተጠቃሚነት በዘላቂነት ለማስፈን የምንረባረብበት ጊዜ ነው።
በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ የሚኖሩ የአማራ ሕዝብ መብት፣ ጥቅምና ልማት ይመለከተናል ከሚሉ ወገኖች ጋር መልካም ግንኙነት በመፍጠር እያደረግን ያለው እንቅስቃሴ ተስፋ አጭሯል፡፡
በሕዝቡ የሚነሱ ትክክለኛ ጥያቄዎችንም በመፍታት ለውጡ ስር እንዲሰድ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛል፤ በመሆኑም ሕዝባችን እየታየ ባለው ለውጥ ላይ ታላቅ ተስፋ የጣለ ሲሆን እንዳይቀለበስበትም በልዩ ልዩ አግባቦች መልዕክቱን አስተላልፏል።
ይሁን እንጅ በለውጡ ሒደት በየጊዜው የሚገጥሙን እንቅፋቶች ፈተና መሆናቸው አልቀረም፤ ይህንን ለውጥ የማይፈልጉ ሀይሎች በሚተበትቡት ሴራ የተጀመሩ መልካም ነገሮችን ለማደናቀፍ አንዳንድ እንቅስቃሴዎች እየተደረጉ መሆኑም ይስተዋላል።
የለውጡ አደናቃፊዎች ከሚጠቀሙባቸው ስልቶች መካከል ሕዝቡንና አመራሩን በልዩ ልዩ መልኩ በመከፋፈል፣ ለውጡን በማጣጣል፣ ሕዝቡ በበርካታ አጀንዳዎች እንዲጠመድና ለውጡ ፋይዳ ቢስ እንደሆነ እንዲሰማው በማድረግ ስርዓት አልበኝነት እንዲነግስ ዘርፈ ብዙ እቅስቃሴዎችን በማድረግ የሚገለጹ ናቸው።
ሰሞኑን በምዕራብና ማዕከላዊ ጎንደር ዞኖች አንዳንድ ወረዳዎችና ቀበሌዎች አካባቢ የተከሰተው ግጭትም የዚህ ማሳያ ሲሆን፥ በግጭቱ ምክንያት በሕይወት፣ በአካልና በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል፤ በአካባቢውም አለመረጋጋት ተፈጥሯል፡።
በተከሰተው ግጭት ምክንያት ሕይወታቸውን ባጡ ወገኖቻችን የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ጥልቅ ሀዘን ተሰምቶታል።
ይህ ግጭት የተጀመረው በጭልጋ ወረዳ አራት ቀበሌዎች ውስጥ ቤቶችን በማቃጠልና ዘረፋ በማድረግ ሲሆን፥ ግጭቱ ከታየበት ቀን ጀምሮ አካባቢው በውጥረት ላይ ሰንብቷል። በአሁኑ ጊዜ የጸጥታ ሀይሎች ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመቀናጀት ሁኔታውን ለማረጋጋት እየሰሩ ይገኛሉ።
የግጭቱ መንስኤ የአካባቢውን ሕዝብ አማራና ቅማንት በሚል ክፍፍል ክፍተት እንዲፈጠር፣ አብሮ በኖረው እና በተጋመደው ሕዝብ መካከል ተቃርኖ እንዲኖር በሚሰሩ ሀይሎች ቀስቃሽነት ሰዎችን በመግደል፣ ዘረፋ በማካሄድ እና ቤቶችን በማቃጠል ነው። ይህንን ግጭት ያቀናበሩና በድርጊቱ የተሳተፉ ተዋናዮችን በቁጥጥር ስር ማዋል ጀምረናል፤ ቀሪዎችንም እግር በእግር ተከታትለን ለሕግ እናቀርባቸዋለን።
የአማራ ብሔራዊ ክልል በውስጡ የተለያዩ ብሔረሰቦች ራሳቸውን እያስተዳደሩ በሰላም የሚኖሩበትና ማንነቶች በአግባቡ የሚስተናገዱበት እንደሆነ የሚታወቅ ሀቅ ነው። የክልሉ መንግስትም በየትኛውም ጊዜ የሚነሳ የማንነት ጥያቄ በአግባቡና ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲፈታ የሚሻ እንደሆነ ባለፉት አመታት የነበሩ አብነቶች ምስክር ናቸው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከተነሱ የማንነት ጥያቄዎች መካከል የቅማንት ሕዝብ የማንነት ጥያቄ አንዱ ነው፤ ጥያቄው ከቀረበ በኋላ ህጋዊና ህገ-መንግስታዊ የሆነውን መንገድ በመከተል የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክር ቤት የቅማንትን ሕዝብ የማንነት ጥያቄ በመሰረቱ በመመለስ ብሄረሰቡ የራሱን አስተዳደር እንዲመሰርት መብት ሰጥቶታል። የክልሉ መንግስትም የቅማንት ሕዝብ በብዛት በሚኖሩባቸው ቀበሌዎች የብሄረሰቡን አስተዳደር ለመመስረት እንቅስቃሴዎችን ጀምሯል።
ይሁን እንጅ የቅማንት ሕዝብ ራሱን በራሱ ለማስተዳደር ያሳየውን ፍላጎት በመጠምዘዝና የሕዝቡን የማንነት ጥያቄ በማድበስበስ "ውሃ ቀጠነ" በሚል የማይረባ ምክንያት የብሄረሰብ አስተዳደሩ እንዳይመሰረት ከፍተኛ ጫናና ሁከት በሚፈጥሩ ግን ደግሞ የቅማንትን ሕዝብ በማይወክሉ ሀይሎች አደናቃፊነት አስተዳደሩ ሳይመሰረት ቆይቷል።
እነዚህ ሀይሎች የብሄረሰቡ የአስተዳደር ጥያቄ እንዳይመለስ የሚሰሩ፣ ለሕዝብ ተጠቃሚነት ሳይሆን ለራሳቸው ተልዕኮ መሳካት የሚንቀሳቀሱ ናቸው። የክልሉ መንግስትም ችግሩን በዘላቂነት እንዲፈታና በአካባቢው በየጊዜው የሚነሱ ግጭቶች እንዲረግቡ የብሄረሰብ አስተዳደሩ ተመስርቶ ስራ እንዲጀምር ከልክ ባለፈ ትግዕስት ከሕዝቡና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ውይይቶችን አድርጓል። ሕዝቡ የሚፈልገው በአካባቢው ሰላምና መረጋጋት ተፈጥሮ፣ ከአማራ ሕዝብ ጋር እንደከዚህ ቀደሙ በአንድነትና በትብብር በመኖር የልማት ተጠቃሚነቱን ማረጋገጥ እንደሆነ በተደረጉ ውይይቶች ተረድተናል።
በሌላ በኩል ደግሞ "የቅማንት ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ" በሚል መጠሪያ የሚንቀሳቀሰው ጽንፈኛና ቅጥረኛ ቡድን በአካባቢው ረዘም ያለ አለመረጋጋትና ብጥብጥ እንዲፈጠር የሚፈልግ፣ የአማራ ብሔራዊ ክልልን ሰላምና ብልጽግና ከማይፈልጉ ሀይሎች ጋር ትስስር በመፍጠር፣ እቅድ በማውጣትና ተልዕኮ በመቀበል የእጅ አዙር መሳሪያ ሆኖ እያገለገለ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ። ሰላማችንን እና ደህንነታችንን በማይፈልጉ ሀይሎች ተልዕኮ የሚንቀሳቀስ ቡድን የሕዝብ ተወካይ ሊሆን ከቶውንም አይችልም።
እንዲህ አይነት ቡድን በባህሪው የራሱን ጥቅም የሚያስቀድም እንጅ ለሕዝብ ደህንነት የሚያስብ አይደለም።
የአማራንና የቅማንትን ሕዝብ በመለያየት ክልሉን የትርምስ ማዕከል ለማድረግ የተቃጣ ሴራ ነው። ይህ ቡድን ክልሉን ለማተራመስ አቅደው ከሚንቀሳቀሱ አካላት ጋር የሎጂስቲክስ ድጋፍ እየተሰጠው፣ ምክር እየተለገሰው፣ የሌሎችን ተልዕኮ ለመፈጸም የሚንቀሳቀስ የቅማንትን ሕዝብ መነገጃ ያደረገ ሀይል ነው።
ከዚህ በመነሳት የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የሕግ የበላይነትን የማስከበር ዋነኛ ተግባሩን እንደሚከውን መታወቅ አለበት። ከዚህ በኋላ በማንነት ስም የሚነግድ የቅማንትን ሕዝብ የማይወክል ህገ-ወጥ ቡድን የሕዝቡን ሰላም ለማናጋት የሚንቀሳቀስ ከሆነ የክልሉ መንግስት ሕግ የማስከበር ሀላፊነቱን ያለ አንዳች ማመንታት ይወጣል።
የቅማንት ሕዝብ ከአማራ ሕዝብ ጋር አብሮ የሚኖር፣ በስነ-ልቦናም ሆነ በታሪክ ተመሳሳይነት ያለውና በማይላላ ገመድ የተሳሰረ እንደሆነ የሚታወቅ ነው። የቅማንትን ሕዝብ ከአማራ ሕዝብ እንዴት መለየት ይቻላል? አብሮ ታሪክ የሰራ፣ የጎንደርን ገናና ስልጣኔ የሚጋራ፣ በብዙ መለኪያ አንድ የሆነ ሕዝብ ነው።
የአማራና የቅማንት ሕዝብ ለዘመናት ተፈቃቅሮና ተጋምዶ የኖረ እንደመሆኑ በመካከሉ እየገቡ ሰላሙን ለመንሳት የሚንቀሳቀሱ ጥቂት ቡድኖችን አንቅሮ በመትፋት እንዲያጋልጣቸው እንጠይቃለን።
አስተዋዩ ሕዝባችን እንዲረዳው የምንፈልገው አንድ ቁምነገር ይህንን ግጭት እያባባሱት ያሉት በግለሰብ ደረጃ የሚቆጠሩ ጥቂቶች እንጂ መላው የቅማንት ሕዝብ እንዳልሆነ፣ ድርጊቱም የቅማንትን ሕዝብ እንደማይወክል ከግንዛቤ በማስገባት እንደሁልጊው ሁሉ ሰላማዊ ግንኙነቱን በማስቀጠል አብሮ በፍቅር እና በመተሳሰብ መኖር እንደሚገባ ነው።
የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት አሁን እየተደረገ ያለው ህገ-ወጥ ድርጊት የአማራን ክልል እንዳይረጋጋ ለማድረግ የተሸረበ ሴራ እንደሆነ ይገነዘባል፤ በመሆኑም መንግስት የሴራውን አንጓዎች በአግባቡ የለያቸው በመሆኑ የጀመረውን ሕግ የማስከበር እንቅስቃሴ አጠናክሮ በመቀጠል የተሸረቡ ሴራዎችን ያፈርሳቸዋል።
ሰላም በአንድ ወገን ብቻ ሊረጋገጥ የማይችል፣ ይልቁንም የሁሉንም ሕዝብ ተሳትፎ እና ርብርብ የሚጠይቅ ጉዳይ ነው። ሕዝቡ በየአካበቢው ሰላሙን በመጠበቅ የተጀመረውን ለውጥ ወደ ኋላ ለመመለስ የሚታትሩ አካላትን በንቃት በመከታተል ከመንግስት ጎን እንዲቆም እንጠይቃለን።
የክልሉን ሰላም ከኅብረተሰቡ ጋር ሆነው ለማረጋገጥ ለሚንቀሳቀሱ የጸጥታ አካላት የተለመደ መልካም ትብብር በማድረግ፣ ወንጀለኞችን በማጋለጥ በጋራ ሆነን የጀመርነውን ለውጥ ወደፊት እንድናስቀጥል ጥሪ እናቀርባለን።
የክልሉ መንግስት ባለፉት ጊዜያት ቃል የገባቸውን ተግባራት ወደ መሬት አውርደን ለመስራት መላው የክልላችን ሕዝብ ከጎናችን እንዲቆም፣ በልማታችን እና ሰላማችን መናጋት ለማትረፍ የሚሰሩ ሀይሎችን በመታገል አንድነታችንን የበለጠ እንድናጠናክር ጥሪ እናቀርባለን፡፡
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ