ከዚህ ሰው ደም ነፃ ነኝ!

(ነፃ ነኝ የሚል ሼር ወይም ኮፒ ፔስት ያድርግ)
-
ሲኞሬ!

የኢትዮጵያዊ ትልቁ ችግር ምን እንደሆነ ታውቃለህ? የወሬ ነፋስ ተከትሎ መጥፋት! አንድን ሰው ሰብሰብ ብለው ሲያሞካሹት ከሰማህ… ያንን ሰው የግል አዳኝህ አርገህ ትቀበላለህ። የሞገቱትን በምላስህ ትጨረግዳለህ። የተቹትን በድንጋይ ተወግሮ እንዲሞት ትፈርድበታለህ። ሰውየው ከሞተ በኋላ ነው ምንም እንዳላጠፋ የሚገባህ።
አንድን ሰው ሰብሰብ ብለው ሲቦጭቁት ካየህ… ያ ሰው ላንተ ቤተክርስቲያን የገባ ውሻ ነው። ያንን ለማለት ማስረጃህ "አሉ" ነው። ለእርሱ ሲከራከርለት የሰማኸው ሁሉ የኢትዮጵያ ጠላት ነው ላንተ!
በርካቶች በ"አሉ" የዚህ ሰለባ ሆነዋል። ሻሸመኔ ላይ የተሰቀለው ምስኪን… ጎጃም ውስጥ በድንጋይ ተወግረው የሞቱት ዶክተሮች… በሙስና ተከሶ አፈር ሲበላ የከረመው መላኩ ፈንቴ… ሀገር ሸጧል ተብሎ በነፍስ ሲፈለግ የነበረው ደመቀ መኮንን… እና ሌሎች በርካቶች!
እስቲ በሞቴ የታከለ ኡማ ጥፋት ምንድነው? አዲሳባ በታሪኳ እንደዚህ ያለ ለህዝብ የወገነ ከንቲባ አይታ ታውቃለች? ይህ ሰው አበረታች ነው የሚያስፈልገው ወይስ ተሳዳቢ?
ሴራው የተጠነሰሰበት ገና ሰውየው ቦታውን ሳይረከብ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር በማሰብ ዶ/ር አምባቸው ከንቲባ ተደርጎ ሊሾም መሆኑን ያለምንም ማስረጃ ተገለፀ። ህዝቡም ደስታ በደስታ ሆነና "ዜናውን" ያስተጋባው ጀመር። የሆነው ግን ያልተጠበቀ ነበር። አንድ ታከለ የሚባል ብዙም ስሙ ያልገነነ ወጣት መሪ ቦታውን ያዘ። ያኔ ከሰውየው ማንነት በፊት የብሔር ማንነቱ ላይ ያደፈጠ ህዝብ የወቀሳ ውርጅብኙን ያወርድበት ጀመር!
ሰውየው የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል ስላልሆነ ቦታው አይገባውም ይልሃል። ዶ/ር አምባቸውም የምክርቤቱ አባል አልነበረም። ዶ/ር ደብረፅዮን የትግራይ ምክርቤት አባል አልነበረም። የሶማሌውም ፕሬዚደንት እንደዛው።
ጊዜያዊ ከንቲባ ስለሆነ ምንም ህግ የማውጣትም ሆነ የመቀየር ስልጣን የለውም ይልሃል ደግሞ እጅ እግሩን ሊያሽመደምድ ሲሞክር… ህግ የሚከበርበት ሀገር ላይ የሚኖር ይመስል። ሁሉም በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ ርዕሰመስተዳደር ሆኖ ነው ሀገር እያስተዳደረ ያለው።
እኔ እንደጲላጦስ ከደሙ ንፁህ ነኝ ሲኞር! ምንም ጥፋት አላገኘሁበትም። አንተው አጥፍቷል ካልክ ውሰድና ስቀለው።
ከዚህ በፊት ልመና የሚበረታታባት የሚሰራ ሰው የሚጉላላባት ከተማ ነበረችህ። ታኬ መጣና በየመንገዱ ከጨለሌ ጋር እየተሯሯጡ ሲነግዱ የነበሩ፣ በተገኙበት የሚደበደቡ፣ ንብረታቸው የሚወረስባቸውን ዜጎች ሼድ ሰጥቶ ህጋዊ ለማድረግ ህግ አወጣ። (ህግ ማውጣት ስልጣኑ አይደለም ይልሃል እዚጋ) በልመና የሚተዳደሩ ከአስር አመት በላይ የአዲሳባ ጎዳና ላይ የኖሩ ምስኪኖች የነዋሪነት መታወቂያ አግኝተው የዜግነት መብታቸውን እንዲጠቀሙ ህግ አፀደቀ። (በሰበቡ ለኦሮሞው ህዝብ መታወቂያ አድሎ ከተማዋን የኦሮሚያ ለማድረግ ነው አሉት ደግሞ እዚጋ)
ሲኞር! ይሄ ጥፋት ከሆነ አንተው ራስህ ፍረድ! እሺ ምን ያድርግ ሰውየው?
ለራሱ ዘረኝነት የተጣባው ህዝብ ታከለን ወደዘር ሸለቆ ሊፈጠፍጠው ይሞክራል። ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስአበባ ብሔር የማይጠቀስበት መታወቂያን ያስተዋወቀው ታከለኡማ ነው። ብርሃኑ ነጋንም ዳውድ ኢብሳንም እኩል እጁን ዘርግቶ ነው የተቀበለው። ለምን ስሙን ከኦነግ ጋር እንደሚያገናኙት አይገባኝም።
ህዝብ ኡኡ እያለ ሲያለቅስባቸው የነበሩ ቦታዎችን ራሱ ሄዶ እየጎበኘ አቤቱታዎችን ሰበሰበ። ከታክሲ ተራ አስከባሪዎች ጋር ቁርስ እየበላ፣ ከዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጋር የካፌ ምግባቸውን እየቀመሰ፣ ከእግርኳሱ ማህበረሰብ ጋር ምሳ እየተጎራረሰ፣ በአንበሳ አውቶቡስ አብሮ ከህዝቡ ጋር እየተጋፋ፣ አቅመደካሞችን እየጠየቀ… ህዝብ መስሎ፣ ህዝብን ሆኖ ስራውን መስራት ሲጀምር "አራዳው" የአዲሳባ ጀማ በሰውየው "ሰገጤነት" ላይ ይሳለቅ ጀመር። ዶ/ር አምባቸው ይምራኝ ሲል የነበረ ህዝብ የአዲሳባ ተወላጅ ካልሆነ አንቀበለውም እያለ ተቃውሞውን አጧጧፈው። ልብ በል እዚህች ጋር… አዲሳበባን ከቆረቆሩት ከዐፄ ምኒልክ ጀምሮ አንድም ጊዜ አዲሳበባ በአዲስአበባ ተወላጅ ሰው ተመርታ አታውቅም! ለምን ታከለ ላይ ነገሩ እንደገነነበት አላውቅም። ዶ/ር አምባቸው ራሱ ስለታከለ ቢጠየቅ የሰውየውን ምርጥነት አድምቆ እንደሚነግርህ እርግጠኛ ነኝ።
ሰውየው ከዚህ በፊት ማንም ደፍሮ ሊናገራቸው ያልቻላቸውን በባለሀብት የታጠሩ ቦታዎች ነጥቆ ለህዝብ ጥቅም አዋለ። በስግብግቦች የተያዙ የቀበሌ ቤቶችን ለይቶ አጋዥ ላጡ አዛውንቶችና አካል ጉዳተኞች አስተላለፈ። ቤታቸው በመፍረስ አደጋ ውስጥ ላሉ አቅመ ደካሞች ቤታቸውን በዘመቻ አሳደሰ። በህገወጥ መንገድ የተያዙ ኮንዶሚኒየሞችን እየለቀመ ለሚገባው ማከፋፈል ጀመረ። ከተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች ጋር በመወያየት ኢንቨስትመንቶችን ወደከተማዋ ጠራ።
ይሄ ሁሉ የሆነው በጥቂት ወራት ወስጥ ነው።
ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ከተማዋ ላይ የሚሰሩ ኢንቨስትመንቶች ቅድሚያ ለነዋሪዎች እዛው ሰፈራቸው ላይ ደረጃውን የጠበቀ መኖሪያ እንዲገነቡ አስገዳጅ አሰራር አስተዋወቀ። ከጠቅላይ አቃቤ ህጓ ጋር በመቀናጀት በየክፍለከተማው የተሰገሰጉ ሙሰኞችን የማጥራት ዘመቻ ጀመረ። በአዲሳበባ ቢሮዎች ኢትዮጵያዊነትንና ኢትዮጵያዊነትን ብቻ መስፈርት ያደረገ ሹመቶችን ሰጠ። የከተማዋን ወጣቶች ይዞ በተለያዩ የክልል ከተሞች በመጓዝ የህዝብ ለህዝብ ወንድማማችነትንና ኢትዮጵያዊነትን የሚያጠናክሩ ስራዎችን ሰራ። ይህን ሁሉ ሲያደርግ ግን ከሰውየው አፍ ወስጥ የወጣው ቃል "አዲሳበባ የሁላችን ሀገር፣ የሁላችን ቤት ናት" የሚል ነበር። ባገኘው አጋጣሚ ኢትዮጵያዊነትን ሰብኳል። "ሁላችሁም የአዲስአበባ ከንቲባ ናችሁ" በምትል አባባሉ ነው የሚታወቀው።
ይኼን ሰው "ስቀሉት" ማለት ያጎረሰን እጅ መንከስ አይንብህም ሲኞር?!
ሰውየው ምንም እንኳ ለስላሳና ፈገግተኛ ቢሆንም ለአላማው ቀጥ ብሎ የቆሞ ፅኑ ኢትዮጵያዊ ነው። ፍርሃት በዞረበት አልዞረም። የኦሮሚያውን የተቃውሞ ማዕበል የመጀመሪያ ክብሪት የጫረው ታከለ ኡማ ነው። ሁሉም የለውጥ ሃይል ( አብይና ደመቀን፣ ለማና ገዱን ጨምሮ) ድምፁን አጥፍቶ ውስጥ ለውስጥ ስራውን ሲሰራ ስልጣን ላይ እያለ ያለምንም ፍርሃት ቀድሞ ከህዝብ ጎን መቆሙን ያሳወቀ የመጀመሪያ ባለስልጣን ነው። ከሶስት አመት በፊት ጀምሮ እስርና ሞት ሳይፈራ፣ ለስልጣኑ ሳይሳሳ ሀገር ውስጥ ተቀምጦ መንግስትን በግልፅ ሲተች የነበረ ሰው ነው።
ይሄን የመሰለን ሰው በብሔሩ ምክኒያት ብቻ ስም ከማጉደፍ የበለጠ ዘረኝነት የለም!


አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Obbo Muktaar Kadir pireezidaantii Mootummaa Naannoo Oromiyaa ta’uun lammata filataman