‹‹ኢትዮጵያ ከለውጡ እየተጠቀመች ነው::›› ዘ ኢስት አፍሪካን
ኢትዮጵያ የጀመረችው ፖለቲካዊና ምጣኔ ሀብታዊ ለውጥ ባለፉት ዓመታት የነበራትን የምጣኔ ሀብት ዕድገት ለማስቀጠል ጠቃሚ ነው፡፡
ዓለማቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይ ኤም ኤፍ) ለኢትዮጵያ በሰጠው ምክረ ሐሳብ መሠረት በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐብይ አህመድ የተጀመረው ምቹ የፖለቲካ ሥነ-ምኅዳር ቀጣይ የሀገሪቱን ዕድገት በጉልህ የሚያፋጥን ነው፡፡
ባለፈው የአውሮፓውያን ዓመት ተገትቶ የነበረው የሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት 7 ነጥብ 7 ከመቶ ጥቅል ሀገራዊ ዕድገት አስመዝግቦ ነበር፤ በተያዘው የአውሮፓውያን ዓመት ግን ዕድገቱ ወደ 8 ነጥብ 5 እንደሚያድግ ያለውን ጠንካራ ፖለቲካዊ መሻሻል መነሻ በማድረግ አይ ኤም ኤፍ ትንበያውን አስቀምጧል፡፡
የፖለቲካ ሁኔታው እየተረጋጋ መምጣት በመጀመሩ ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ የሚመጣው የገንዘብ መጠን ጨምሯል፤ የውጭ ቀጥታ መዋዕለ ንዋይ ፍሰትም አድጓል፤ የውጭ ምንዛሪ እጥረትም እየተቀረፈ ነው፡፡
‹‹ስለሆነም የፖለቲካ ሥነ-ምኅዳሩ ሲረጋጋ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት ይነቃቃል፤ አጠቃላይ ሀገራዊ ዕድገቱም በዚህ የአውሮፓውያኑ ዓመት ወደ 8 ነጥብ 5 በመቶ ያድጋል፡፡ በዚህ ወቅት ያለው የበጀት ጉድለትም እየቀነሰ ይሄዳል›› ብሏል አይ ኤም ኤፍ፡፡
ዓለማቀፍ የገንዘብ ድርጅቱ ተስፋን ብቻም አላስቀመጠም፤ ያለው ሀገራዊ የዕዳ ጫናና የንግድ ሚዛን አለመጠበቅ የሀገሪቱ ቀጣይ የዕድገት ፈተናዎች እንደሚሆኑም ስጋቱን አመላክቷል፡፡
በተለይ ኢትዮጵያ የዕዳ ማረዘሚያ ጊዜዋ እየጠበበ የመጣ በመሆኑ በቀጣዮቹ ጥቂት ዓመታት ከፍተኛ የብድር መመለስ ጫና ውስጥ ትገባለች፤ ይህም አንዱ ዓይነተኛ ፈተናዋ እንዳይሆን ሰግቷል፡፡
በአውሮፓውያኑ 2016/2017 የኢትዮጵያ የዕዳ ጫና ከዓመታዊ ምርቷ 57 ነጥብ 2 ከመቶ ነበር፤ በቀጣዩ ዓመት (2017/18) ወደ 60 በመቶ አድጓል፤ ይህም በጥቅል ከ26 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ ዕዳ አለባት ማለት ነው፡፡
ከዚህ ቀውስ ለመውጣት ኢትዮጵያ የመንግሥት ዕዳን (ብድርን) መቀነስ በተለይም የተራዘሙ ብድሮችን መምረጥ፣ የታክስ ገቢዋን ማሳደግና የወጪ ንግዷን ማሳደግ አለባት፤ ይህም የዕዳ ጫና ተጋላጭነቷን ይቀንስላታል፡፡
አሁን ቀደም ከተጫናት ዕዳ በቀር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ዘመን ምጣኔ ሀብቷ በእግሩ እየቆመ ነው፤ ለፖለቲካ ልሂቃን ሜዳውን በማስፋት፣ ከኤርትራ ጋር ሰላም በማውረድ በሀገራቱ መካከል የምጣኔ ሀብት ትስስር እየፈጠሩ ነው፡፡ ይህም የውጭ ቀጥታ መዋዕለ ንዋይንና የግሉን ዘርፍ ተወዳዳሪ ለማድረግ አጋዥ ነው፡፡
በኢትዮጵያ የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴው በአምራችና አገልግሎት ዘርፉ ዕድገት እየታገዘ፣ የአየር መጓጓዣ ዘርፉ እየተስፋፋ እንደሚያድግ ይጠበቃል፡፡
አይ ኤም ኤፍ እንደተነበየው በመካከለኛ ጊዜ ውስጥ የኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት በ7 በመቶ አካባቢ በአማካይ እያደገና የውጭ ቀጥታ መዋዕለ ንዋይ ፍሰት እየጨመረ ይሄዳል፡፡ በመሠረተ ልማት ማስፋፋት ላይ ማተኮር፣ በወጪ ንግድ ላይ ያተኮሩ አምራች ዘርፎችን መደገፍና አምራቹን ሰፊ መሠረት ማስያዝ ከባድ የቤት ሥራዋ ነው፡፡
በዚህ ወቅት ያለው 11 ነጥብ 5 ከመቶ አጠቃላይ የዋጋ ግሽበትም በቀጣዩ የአውሮፓውያን ዓመት ትርጉም ባለው መልኩ ይቀንሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ትንበያው ያሳያል፡፡
ምንጭ፡- ዘ ኢስት አፍሪካን
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ