ጎታች የሆኑ አስተሳሰቦችን ወደኋላ በመተው ወደፊት እንገስግስ
አንድ በትንሽ ገጠር መንደር የሚኖሩ ህፃናት ከመንደራቸው ፊት ለፊት ካብ ስር ሆነው ይጫወታሉ፡፡ አንድ ዝምተኛ ህፃን በመካከላቸው አለ፡፡ ህፃናቱ በሚቦርቁበት ሜዳ ፊት ለፊት እንደሰንሰለት የተሳሰሩ ተራራዎች ይገኛሉ፡፡ ከህፃናቱ መካከል አንዱ በጨዋታቸው መሃል ለምን ያንን ተራራ መውጣት አንወዳደርም የሚል ሃሳብ አቀረበ፡፡ በሀሳቡ የተስማሙት ህፃናቱ ወደተራራው አቀኑ፡፡ ሌሎች ከመወዳደር ይልቅ ዳኛ መሆንን የመረጡና መመልከት ብቻ የፈለጉ ልጆች ከስር ሆነው ሁኔታውን ለመከታተል ተስማሙ፡፡
ውድድሩ ተጀመረ፡፡ ሃሳቡን ያቀረበው ህፃን ወደተራራው ለመውጣት የማሰላሰያ ጊዜም አልፈጀም፡፡ ወደላይ መውጣት ጀመሩ፡፡ ከታች የተደረደሩት ህፃናትም ወደቀ ወደቀች እየተባባሉ ይንጫጫሉ፡፡ ገና ሳይጀምሩ ከመንገድ ያቋረጡ ህፃናትም ከታች ሆነው ሌሎች ወደፊት ሲገሰግሱ የነበሩ ህፃናትን ከማበረታታት ይልቅ ውረዱ እንዳትወድቁ እያሉ ያስፈራሯቸው ጀመር፡፡ ህፃናቱ ተራራ መውጣት አዲሳቸው ባይሆንም ከስር ያሉት ልጆች ጫጫታና ማስፈራራት አቅም ስላሳጣቸው ውድድሩን መጨረስ ሳይችሉ ቀሩ፡፡ ከአንዱ ልጅ በስተቀር የእንወዳደር ሃሳብ ያቀረበው ልጅም ሳይቀር ከውድድሩ ውጭ ሆነ፡፡
በልጆቹ መሃል ዝምተኛው ልጅ ወደፊት እየገሰገሰ ነው፡፡ የልጆቹ ጫጫታም ማስፈራራትም ተራራውን ከመውጣት አላገደውም፡፡ ወደፊት ብቻ፡፡ በመጨረሻም የተራራው ጫፍ ላይ የደረሰው ህፃን ቁልቁል ልጆቹን እያየ በደስታ ተፍነከነከ፡፡ በአሸናፊነት ስሜት እጁን ዘርግቶ ደስታዋን ገለጠ፡፡ ዝምተኛው ህፃን አሸናፊ ሆነ፡፡ ምክነያቱ ደግሞ ልጁ መስማት የተሳናው ነበርና የልጆቹን ጫጫታና ማስፈራራት ከጆሮው ስለማይደርስና ከመንገዱ ስለማያሰናክለው ነበር፡፡ ወደፊት ብቻ ማየቱ ጓደኞቹ ከመንገድ ያቋረጡትን የተራራ መውጣት ውድድር በድል እንዲያጠናቅቅ አድርጎታል፡፡
ይህን አጭር ታሪክ ሁላችንም ወደራሳችን ህይወት ወስደን እንመልከተው፡፡ የበርካቶቻችንም ህይወት እንደዚህ ናት፡፡ እኛ የምንሮጠውን ሩጫ የማይሮጡ ሰዎች ከዳር ሆነው ስለመንገዳችን ይነግሩናል፡፡ ተስፋችንን ያጨልሙብናል፡፡ ከአሸናፊነታችን ይልቅ ውድቀታችንን መሮጥ ጀምረን እንኳን ለማሳመን ይጥራሉ፡፡ እነሱ ሳይሞክሩት ተስፋ በቆረጡበት መንገድ እኛ መንገድ ጀምረን ስኬቱን ማጣጣም ስንጀምር ደግሞ ከውጤቱ ይልቅ ውድቀቱ ይታያቸዋል፡፡ በመሆኑም ድል ማድረግን የፈለገ ተስፋ የሚሰጠውን እንጂ ተስፋ የሚያሳጣውን ወሬ መስማት ኪሳራ ነው፡፡ ከመንገድም መሰናከል ነው፡፡ ጨለምተኞችን ሁሌም ቢሆን እንቅፋት ሆነው ከማሰናከላቸው በፊት ከህይወትህ ቀንሳቸው፡፡ ብርታትና ጥንካሬ የሚሆኑ ብሩህ አሳቢዎችን ብቻ ደምረህ ወደፊት በአሸናፊነት መጓዝን ብቻ ምረጥ፡፡
በተመሳሳይ አሁን በአገራችን የተጀመረው ለውጥ ሲጀመር ብዙዎችን ማርኳል፡፡ በጥርጣሬ የተመለከቱት ቢኖሩም የኋላ ኋላ አገራችንን ወደተሻለ ምዕራፍ እንደሚያሸጋግራት እርግጠኛ በመሆን አጋዥ ሚና እየተጫወቱ ያሉ ቀላል አይደሉም፡፡ አሁን ያለውን የለውጥ ሂደት አጠናክሮ ከማስቀጠል ይልቅ አገራችንን ወደነበረችበት ሁኔታ ለመመለስ ደፋ ቀና የሚልም አልጠፋም፡፡ በመሆኑም የለውጥ ሂደቱ አደናቃፊ የሆኑ አስተሳሰቦችንና ተግባራትን እያንገዋለለና እየቀነሰ ገንቢና ሂደቱን ወደተሻለ ምዕራፍ የሚያሸጋግሩ ሁኔታዎችን እያጠናከረ መቀጠል ይኖርበታል፡፡ በአገራችን የተጀመረው ለውጥ አገራችንን ከተደራረበባት ችግር አላቆ የምንፈልጋትን ኢትዮጵያን እስክንገነባ ድረስ ለአፍታም ቢሆን ጎታች ለሆኑ አስተሳሰቦችና ተግባራት እድልም ሆነ ጆሮ መስጠት አይገባም፡፡
Source:EPRDF Official
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ