“ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ”


መከባበር ይሻለናል ከተከባበርን አብረን መኖር እንችላለን ከተከባበርን እንደ ቀድሞው በጋራ በመተሳሰብና በመቻቻል አብሮ መኖር ቀላል ይሆናል፤ተራራ መስሎ የሚታየን ሁሉ ሜዳ ይሆናል።
በመናናቅ አብሮ መኖር አይቻልም ከባድ ነው የተናናቀ ግለሰብና ህብረተሰብ እንዴት አድርጎ በጋራ መኖር ይችላል?አሁን በፊንፊኔ ጉዳይ ያለው መናናቅ እጅግ በጣም አደገኛ እንደሆነ በሁሉም ዜጋ ሊታወቅ ይገባል!
ፊንፊኔ የእኔ ናት ያንተ አይደለችም ጨዋታ እጅግ በጣም አደገኛ ጨዋታ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፤ታሪክን በማጣመም ለፊንፊኔ የተለያዩ የፈጠራ ስሞችን መስጠት የትም አያደርስም “በረራ” ብትልም ባትልም ፊንፊኔ ፊንፊኔነቷን መቀየር አትችልም ወደድክም ጠላህም ፊንፊኔ የኦሮሞ ምድርነቷን መቀየር አትችልም።
ይህ ማለት ከጥንት ጀምሮ በተለያዩ ወቅቶችና ዘመናት ወደ ፊንፊኔ መጥተው የኖሩ ነግደው ያተረፉ ሃብት ያፈሩ የወለዱ የከበዱ ብሄር ብሄረሰቦች ከአሁን በኋላ ፊንፊኔ ውስጥ መኖር አይችሉም ማለት አይደለም።ልክ እንደበፊቱ ሁሉም ብሄር ብሄረሰቦች ፊንፊኔ ውስጥ በህጋዊ መንገድ እስከ ሆነ ድረስ መኖርና ነግደው ማትረፍ ሃብት ማፍራት ይችላሉ፤ይገባል ይህን የሚከለክል ኃይል መኖር የለበትም።
ያለፉ ገዢ ስርዓቶች የራሳቸውንና የተከታዮቻቸውን ጥቅም ለማስከበር ሲሉ ብቻ ብዙ ነገር አበላሽተው አልፈዋል፤አሁን እነርሱን መውቀስ ተገቢ አይሆንም አይገባም።እነርሱ በወቅታቸው ባላቸው የግንዛቤ ደረጃ የሰሩትን ሰርተው አልፈዋል ለሰሩት መልካም ነገር ሁሉ ምን ጊዜም እናመሰግናቸዋለን፤ለፈፀሙት ጥፋት ግን እነርሱን መውቀስ ምንም የሚያመጣው ነገር የለም ዋጋ የለውም።
ዋናው ነገር የተበላሸውን ነገር ለቀጣዩ ትውልድ በሚመች መንገድ ማረምና ማመቻቸት ነው።አሁን ያለው ትውልድ በየዘርፉ የተበላሹ ነገሮችን በጥበብና በምክክር ማስተካከል ካልቻለ ችግሩ ለዘመናት ይቀጥላል።የወደፊቱ ትውልድም የአሁኑ ትውልድ ማረም ሳይችል ቀጣይ በሚሆነው ችግር ምክንያት ይሰቃያል፤ያለፈውንም ለመውቀስ ይገደዳል።ይህ እንዳይሆን ሁሉም ወገን ሰከን ብሎ ከመግለብለብ ወጥቶ ጉዳዩን በጥሞና ተመልክቶ የተወላገደውን የተጣመመውን ማቃናት ይጠበቅበታል።ይህን ለማድረግ ራሱን ማዘጋጀት ያልፈለገ ወገን አስቦና አቅዶ ለጥፋት ተዘጋጅቷል ማለት ነው።ለጥፋት ያዘጋጀው ኃይልም አለ ማለት ነው፤ምክንያቱም ያለ ምንም ድጋፍ በባዶ መደንፋትና በማን አለብኝነት መንቀሳቀስ አይቻልምና!
ፊንፊኔ ዛሬ ወደምትገኝበት ደረጃ እንዴት መድረስ ቻለች?
Finfinnee/አዲስ አበባ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ አርሶ አደሮችን በተለያዩ ምክንያቶች በማፈናቀል ነው ዛሬ ወደምትገኝበት ደረጃ መድረስ የቻለችው።ይህ እውነት ነው አሁን በአፋን ኦሮሞ ስያሜዎች የሚታወቁ ጉለሌ፤ቦሌ ቡልቡላ፤ገርጂ እና የመሳሰሉ በርካታ አካባቢዎች ጥንት ኦሮሞዎች ሲኖሩባቸው የነበሩ ናቸው፤በአሁኑ ወቅትም በእነዚሀ አካባቢዎች ባህልና ታሪካቸውን ለመርሳት የተገደዱ ኦሮሞዎች በብዛት ይገኛሉ።
ሁለቱ የአፄ ስርዓቶች /ሚኒልክና ኃይለስላሴ/ የባለስልጣኖቻቸውን የመሬት ሃብት ፍላጎት ለማሟላት የአሮሞ አርሶ አደሮችን በጉልበት አፈናቅለው ከአካባቢው ከማራቅ ውጭ ሌላ መፍትሄ ለመሻት ጥረት አላደረጉም።በርካታ የኦሮሞ አርሶ አደሮች መሬታቸውን በጉልበት ተነጥቀው የስርኣቶቹ ባለስልጣናት አገልጋይ ሆነው ለመኖር ተገድደው ነበር።
ከፊሎቹም በተመሳሳይ ሁኔታ በግፍ ከመሬታቸው ተባርረው ወደ አርሲ ባሌና ሌሎች አካባቢዎችም ተሰደው እዚያም የገዢዎቹ አገልጋይ ሆነው ከነቤተሰቦቻቸው የስቃይ ኑሮ ሲገፉ ኖረው አልፈዋል።የዚህ ፅሁፍ ፀሓፊ አያትና ቅድመ አያት አሁን  በተለምዶ ካራ ቆሬ ተብሎ ከሚታወቀው አካባቢ ወደ አርሲ አሰላ አካባቢ ተሰድደው ለመኖር በመገደድ እዚያው አልፈዋል።
“መሬት ለአራሹ” በሚል መፈክር ስልጣን የያዘው የደርግ ስርዓትም በተራው ለስርዓቱ አገልጋዮች መኖሪያ ሰፈር ለማቋቋም ሲያቅድ የመጀመሪያ ምርጫው የኦሮሞ አርሶ አደሮችን ከተለያዩ የፊንፊኔ አካባቢዎች ማፈናቀል ነው።አሁን ገርጂ ከሚባለውና ሌሎች አካባቢዎች  በርካታ የኦሮሞ አርሶ አደሮች ተፈናቅለው ወደ ዳር እንዲወጡ ተደርጓል።
የኢህአዴግ ስርዓትም በልማት ስም ቀደም ሲል የተለመደውን ችግር በእጥፍ ጨምሮ በሺዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ አርሶ አደሮችን ማፈናቀሉ አገር ያወቀው ፀሐይ የሞቀው ጉዳይ ነው።የኢህአዴግ ስርዓት ለነዋሪዎች የመኖሪያ ቤት ችግር መፍትሄ ይሆናል በሚል በቤቶች ልማት ፕሮግራም ምክንያት መሃል ከተማውን አፍርሶ አርሶ አደሮችን ከመኖሪያ አካባቢያቸው ሲያነሳ የሚሰጠው የካሳ ክፍያ በቂ አልነበረም እጅግ በጣም ዝቅተኛ ነው።
አሁን በህይወት ያሉ አርሶ አደሮችና ቤተሰቦቻቸው በሰጡት መረጃ መሰረት አንዱን ካሬ ሜትር በሶስት ብር ሂሳብ በማስላት ነው አርሶ አደሩ የእርሻ መሬቱን የተነጠቀው።ከነቤተሰቡ የመኖሪያ ቤት ግንባታ ቦታና ከሁለት መቶ ሺህ ብር ያልበለጠ ገንዘብ የተረከበው አርሶ አደር ገንዘቡን ጨርሶ የዘበኝነት ስራ ለመስራት ሲገደድ ወንድ ልጆቹ ስራ አጥ ሆነው ሴት ልጆቹም የአረብ አገራት ገረድ በመሆን ለመኖር ሲገደዱ የኢህአዴግ ባለስልጣናት ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው በውስን ገንዘብ ከአርሶ አደሩ የተነጠቀውን መሬት በሊዝ ዋጋ እያሉ ለሪል እስቴት ባለሃብቶች በብዙ ሚሊዮን ብር ሲቸበችቡት እንደኖሩ ይታወቃል።
ባለስልጣናቱ በህዝብ ጥቅም ስም ስግብግብነታቸውን በመቀጠል በመሃል ከተማ የኮንዶሚንየም መኖሪያ ቤት መገንቢያ ቦታ እያለ ከ15 እስከ 30 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እስከ ቱሉ ዲምቱ አያት፤ገላን፤የካ አባዶ አራብሳና ኮዬ ፈጬ ድረስ በመዝለቅ የኮንዶሚንየም መኖሪያ ቤቶችን አስገነቡ፤ይህን ሲያደርጉ ለባለ ዕድለኖች የትራንስፖርት ችግር መፍትሄ እንኳ አላስቀመጡም ነዋሪው ከመሃል ከተማ ተመላልሶ በተገነቡ ቤቶች ከአካባቢው አርሶ አደሮች ጋር በሰላም የሚኖርበትን ሁኔታ አላመቻቹም።
ለዚህ ሁሉ ችግር ከኢንጂነር ታከለ ኡማ ውጭ ያሉ የኢህአዴግ ዘመን የቀድሞ የፊንፊኔ ከተማ ከንቲባዎች በግንባር ቀደምትነት ተጠያቂ ናቸው።ከንቲቦቹ ኦሮሞ መሆናቸው ከተጠያቁነት ሊያስቀራቸው አይችልም አይገባም!እነርሱ በበላይ አመራሮች ቀጭን ትዕዛዝ በደመ ነፍስ በፊንፊኔ ያከናወኗቸው ስራዎች ለብዙዎች የእንግልት ኑሮ ምክንያት ሆኗልና።
ይህ ሁሉ የሆነው “ባለቤቱን ካልናቁ አጥሩን አይነቀንቁ” እንዲሉ በማን አለብኝነትና ንቀት የስርዓቱ ባለስልጣናት ህገ ወጥ ስራዎችን በመስራታቸው ነው።አርሶ አደሩ ተጠቃሚ ሆኖ ቀጣይ ህይወቱን የሚመራበት ሁኔታ እስከ ተመቻቸ ድረስ በልማት ምክንያት የትኛውም አርሶ አደር ከኖረበት አካባቢ መነሳቱ ችግር የለውም።ግን ይህ አልሆነም የይስሙላ ከሳ ክፍያ አሁን ያለውን ተጨባጭ ችግር አርግዞ ወለደ።በመሆኑም አርሶ አደሩ ምሬቱን ማሰማቱ   የኦሮሞ ህዝብም ተቆጥቶ ከመላ አሮሚያ  መነቃነቁ ትክክል ተገቢና አስፈላጊ ነው።
የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት አቋም
መንግስት በሚመራው ህዝብ ተቀባይነት ኖሮት በቀጣይነት መምራት የሚችለው የሚመራውን ህዝብ ፍላጎትና ጥቅም ማስከበር ሲችል ብቻ ነው።ከዚህ አንፃር የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የኦሮሞ ህዝብ በፊንፊኔ ጉዳይ ላይ ከኦሮሞ ህዝብና ከክልሉ መንግስት እውቅና ውጭ ማንም ምንም መወሰን አይችልም ሲል የያዘውን ጠንካራ አቋም ይፋ ማድረጉ ተገቢ ነው።
የክልሉ መንግስት ይህን ግልፅ አቋም ከመያዝ ባሻገር ለዘላቂ መፍትሄ መንቀሳቀስ ይጠበቅበታል።ፊንፊኔ የአሃዳዊ አመለካከት አራማጅ ኃይሎች መፈንጫ ብቻ መሆን አትችልም አይገባም።የኦሮሞ ህዝብ መቼም ተጠቃሚ የሚሆንበት የፌዴራል ስርዓት አመለካከት አራማጅ ኃይሎችም በፊንፊኔ ውስጥ መኖርና መንቀሳቀስ መቻል አለባቸው።
ኦሮሞ ባህልና ቋንቋውን በፊንፊኔ ውስጥ ማሳደግ መቻል አለበት፤ በፊንፊኔ ውስጥ ሆን ተብሎ እንዲረሱ የተደረጉ የኦሮሞ የአካባቢ ስያሜዎችና መጠሪያዎች በህግ መመለስ አለባቸው፤ፊንፊኔ ውስጥ የሚኖሩ የኦሮሞ ልጆች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው በአፋን ኦሮሞ መማር አለባቸው፤ለዚህም ሁሉም አስፈላጊ ነገር መሟላት አለበት።ይህ የሁሉም ኦሮሞ ህዝብ ፍላጎት ነው ይህን ጨምሮ ሌሎች የህዝብ ፍላጎቶችን ስርዓት ባለው መንገድ በመምራት ማሟላት የሚችለው የህዝብ ውክልና ያለው መንግስት ነው፤እሱም የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ነው።
የክልሉ መንግስት በፊንፊኔ ጉዳይ ላይ ከፌዴራል መንግስት ጋር ተቀናጅቶ በመስራትና የህዝቡን ግልፅ ጥያቄና አቋም በማስረዳት መብትና ጥቅሞቹን ማስከበር መቻል አለበት።የክልሉ ህዝብ በበኩሉ አንድነቱን በማጠናከር መንግስቱ የሚያደርገውን ጥረት ለጋራ ጥቅም በሙሉ ልብ መደገፍ ይጠበቅበታል፤ከሰሞኑ ከኮንዶሚንየም እጣ ጋር ተያይዞ የታየው የኦሮሞ ህዝብ ንቅናቄ ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው።በሁሉም የክልሉ ህዝብና የአገር ጉዳዮች ኦሮሞ እንደለመደው በዚህ አይነት ሁኔታ መንቀሳቀስ ያለበት።

ከእጣው አወጣጥ ስነ ስርዓት በኋላ የሆነውን መመልከት ጠቃሚ ነው።የአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ በእጣ አወጣጡ ስነ ስርዓት ላይ ባሰሙት ንግግር የአካባቢውን አርሶ አደሮች “ህመማችሁ ህመማችን ነው፤እንክሳችኋለን” ከማለት አልፈው ምንም ማለት አልቻሉም፤እዚጋ ችግር አለ ማለት ነው።ምክትል ከንቲባውም ሆኑ ሌሎች የአስተዳደሩ የስራ ኃላፊዎች ተጎጂዎች ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ጥቂት ነገር ከመናገር አልፈው በምን አይነት መልኩና እንዴት አርሶ አደሮቹ ተጠቃሚ  እንደሚሆኑ ማስረዳት አልቻሉም፤ይህ የተድበሰበስ አካሄድ በግልፅ ሲታይ አንድ የተቆለፈ ነገር አለ ብሎ ህዝቡ በመጠርጠር ሆ ብሎ መነሳቱ እውነት አለው፤ምክንያቱም በፊትም እንዲሁ ምክንያት በመደርደር ነው ብዙዎች ተጎጂ ሆነው የቀሩት።
አሁን በፊንፊኔ ጉዳይ የፌዴራል መንግስትም ከምር ተንቀሳቅሶ መፍትሄ እንደሚሻ በተግባር አሳይቷል።የአስተዳደር ድንበር ጉዳይን በማጥናት መፍትሄ የሚያቀርብ ኮሚቴ በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲቋቋም መደረጉ ትልቅ እርምጃ ነው።እዚህ ደረጃ ላይ መድረስ የተቻለው የክልሉ መንግስትና የህዝብ ትግል ተጠናክሮ በመቀጠሉ ነው።

የሰላም ሚኒስትር በሆኑት ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል የሚመራው ስምንት አባላት ያሉት የጋራ ኮሚቴ በጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ተቋቁሟል፤ኮሚቴው ስራውን ማቀላጠፍ ይጠበቅበታል።የኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ሲሆኑ ወይዘሮ ጠይባ ሃሰን፤አቶ አህመድ ቱሳ፤ዶክተር ግርማ አመንቴ፤ኢንጂነር ታከለ ኡማ፤አቶ እንዳወቅ አብጤ፤ዶክተር ሰለሞን ኪዳኔ፤አቶ ተስፋዬ በልጂጌ የኮሚቴው አባላት ናቸው።ኮሚቴው ከፌዴራል መንግስት ከኦሮሚያና ከአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር የተውጣጣ ሲሆን ዘመናትን ላስቆጠረው ችግር ዘላቂ መፍትሄ ያስገኛል ተብሎ ይጠበቃል፤ህዝቡም ውጤቱን በትዕግስት ይጠብቃል።
ዘላቂ መፍትሄ የሚያስገኘው ውጤት ይፋ እስከሚሆን ደረስ ሁሉም ወገን ከተንኳሽ ድርጊቱ መቆጠብ አለበት፤በተለይም የአሃዳዊ አመለካከት አራማጅ ኃይሎች በፊንፊኔ ጉዳይ ላይ ነጋ ጠባ በማራገብ ላይ ያሉት ፕሮፓጋንዳ እነርሱን ጨምሮ ለሁሉም ጠቃሚ ስለማይሆን ከአፍራሽ ፕሮፓጋንዳና አሉባልታ ተቆጥበው መንቀሳቀስ ይጠበቅባቸዋል።አሁን ላለው ለውጥ ዋነኛ ምክንያት የሆነው የኦሮሞ ቄሮም አንድነቱን ጠብቆ በፊንፊኔ ጉዳይም ሆነ በሌሎች የአገራችን ኢትዮጵያ ጉዳዮች ላይ ሰከን ብሎ ስርዓት ጠብቆ ቢንቀሳቀስ ይጠቀማል እንጂ አይጎዳም።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Eessa turre,Maalirra Geenyeerra? Kutaa 4ffaa