ያለ ማስረጃ ተጠርጥረው ጉዳት ለደረሳባቸው እስከ 50,000 ብር ካሳ ይከፈላል


በሥራ ላይ ያለውን የፀረ ሽብርተኝነት ሕግ ለመተካት የተዘጋጀው ረቂቅ አስፈጻሚውንም ተጠያቂ ያደርጋል
ላለፉት አሥር ዓመታት በሥራ ላይ የሚገኘውን የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 ስያሜውን ጭምር ለመተካት ተዘጋጅቶ ውይይት እየተደረገበት የሚገኘው፣ ረቂቅ አዋጅ አስፈጻሚ አካላትን ጭምር ተጠያቂ የሚያደርግ ድንጋጌ የያዘ ነው፡፡
‹‹የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር›› በሚል ስያሜ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ወንጀልን የመከላከል፣ የመመርመር ወይም የክርክር ሒደቱን የማስፈጸም ኃላፊነት የተሰጠው ማንኛውም ሰው፣ የተሰጠውን ኃላፊነት ሕግን በመተላለፍ በሚፈጸመው ማንኛውም ድርጊት እንደመተላለፉ ዓይነትና እንዳስከተለው የጉዳት ዓይነት በዲሲፕሊን፣ በፍትሐ ብሔርና በወንጀል ተጠያቂ እንደሚሆን ደንግጓል፡፡   
የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የተፈጸመውን የጥፋት ዓይነትና ድርጊቱን የፈጸሙ ተጠያቂ መሆናቸውን ማረጋገጥ እንዳለበትና ፍርድ ቤቱም በወንጀል ክርክር ሒደት የሕግ አስፈጻሚ አካላት የሕግ ጥሰት የፈጸሙ መሆኑን ካረጋገጠ፣ የሕግ ጥሰቱን የፈጸመው ሰው ወይም ተቋም ለተጎጂው አካል 1,000 ብር እስከ 50,000 ብር የሚደርስ የህሊና ጉዳት ካሳ እንዲከፈለው በያዘው የክርክር መዝገብ ላይ ሊወሰን እንደሚችል በረቂቅ አዋጁ ተደንግጓል፡፡ ፍርድ ቤት ለተጎጂ የህሊና ካሳ መወሰኑ፣ ተጎጂው ከህሊና ውጪ ለደረሰበት ጉዳት፣ ጉዳቱን ባደረሰበት አካል ላይ የዲሲፕሊንና የወንጀል ክስ ከማቅረብ እንደማያግደው አክሏል፡፡
በረቂቅ አዋጁ ላይ ሐሙስ የካቲት 21 ቀን 2011 .. ከባለድርሻ አካላት፣ ከዘርፉ ምሁራንና ከተፎካካሪ የፖለቲካ አመራሮች ጋር በኢሊሌ ኢንተርናሽናል ሆቴል በተደረገ ውይይት፣ የረቂቅ ጥናት ቡድኑ ሰብሳቢ ጠበቃው አቶ አመሐ መኮንን እንዳስረዱት፣ በሥራ ላይ ያለው የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 በይዘቱም ሆነ በአፈጻጸሙ ብዙ ችግሮች አሉበት፡፡ አዋጁ ትኩረት የሚያደርገው ሽብርን የሚከላከል ወይም ለመንግሥት ብቻ ጥበቃ የሚያደርግ ነው፡፡ በንፁኃን ሰዎችና በተጠርጣሪዎች ላይ ስለሚደርሰው ጉዳት ምንም የሚለው ነገር የለም ብለዋል፡፡ በመሆኑም የሚሻሻለውን አዋጅ ከስያሜው ጭምር አካታች እንዲሆን በማድረግ ‹‹የሽብር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የወጣ አዋጅ›› እንዲባል ስምምነት ላይ መደረሱን አስረድተዋል፡፡      
ዓለም አቀፍ ሕግጋትና የተባበሩት መንግሥታት ውሳኔዎች አበክረው እንደሚገልጹት የፀረ ሽብርተኝነት ሕግ ሁለት ነገሮችን መያዝ እንዳለበት ያስረዱት አቶ አመሐ፣ የመጀመርያው የሽብር ወንጀልን በብቃት መከላከል ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ የተጠርጣሪዎችን ሰብዓዊ መብቶች የሚያስከብር ወይም የማይጋፋ መሆን እንዳለበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የፀረ ሽብርተኝነት ሕግ በአንዳንድ የዓለም አገሮች እንደ ሰብዓዊ መብት ማስጠበቂያ ሕግ እንደሚያገለግልም አክለዋል፡፡
ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸውን ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች መረዳትና በጥንቃቄ መተግበር አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው፣ ይኼንን የሚያስገድድ በረቂቅ አዋጁ ላይ መካተቱን አስረድተዋል፡፡ አንድ ተጠርጣሪ ሰብዓዊ መብቱ በአስፈጻሚ አካል መጣሱን ለፍርድ ቤት ካመለከተ፣ ፍርድ ቤቱ ከሁሉም በፊት በማጣራት በያዘው መዝገብ ላይ ውሳኔ እንዲያሳልፍ የሚፈቅድ ድንጋጌም መካተቱን አክለዋል፡፡
በረቂቅ ሕጉ የተካተቱ ድንጋጌዎች ተግባራዊ ሲሆኑ ችግር እንዳይፈጠር መጠበቂያ ድንጋጌ መቀመጡን የገለጹት አቶ አመሐ፣ የሽብር ወንጀል እየተጠነሰሰ ማወቁን ካልሆነ በስተቀር ጋዜጠኛ የመረጃ ምንጩን ያለ መግለጽ መብት እንዳለው በረቂቁ ተደንግጓል ብለዋል፡፡ በሰላማዊ ሠልፍ የመብት ጥያቄ የሚያነሱ አካላት ሆን ተብሎ በሰው ሕይወት፣ በአካልና ንብረት ላይ ጉዳት ለማድረስ ካልሆነ በስተቀር፣ በሽብርተኛነት ሊፈረጁና ሊጠየቁ እንደማይገባ በረቂቅ ሕጉ መደንገጉን አስታውቀዋል፡፡

በአጠቃላይ ረቂቅ ሕጉ በስድስት ክፍሎችና 54 አንቀጾች ተከፋፍሎ የተዘጋጀ ሲሆን፣ በመጀመርያው ክፍል ስለጠቅላላ ድንጋጌዎች፣ በክፍል ሁለት ስለሽብርና ተያያዥ ወንጀሎች፣ በክፍል ሦስት ድርጅቶችን በአሸባሪነት ስለመሰየምና በሽብርተኝነት በተሰየመ ድርጅት ውስጥ መሳተፍ፣ በክፍል አራት ስለሽብር ወንጀል ምርመራና መከላከል፣ በክፍል አምስት ስለተቋማት ኃላፊነት፣ ትብብርና ተጠያቂነት፣ እንዲሁም በክፍል ስድስት ልዩ ልዩ ድንጋጌዎች ማለትም ፈንድ ስለማቋቋምና ሌሎችም ድንጋጌዎች በረቂቁ ተካተዋል፡፡
የሽብር ተግባር ሊባል የሚችለው የፖለቲካ፣ የሃይማኖት ወይም የርዕዮተ ዓለም ዓላማን ለማራመድ በማሰብ፣ ሕዝብን ወይም የተወሰነ የኅብረተሰብ ክፍልን ለማሸበር፣ ወይም መንግሥት ለማስገደድ የተፈጸመ የወንጀል ድርጊት መሆኑን ረቂቁ ይገልጻል፡፡ በዚህም በሰው አካል ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ፣ ለአደጋ ያጋለጠ፣ ሰውን ያገተ፣ የጠለፈ፣ በንብረት፣ በተፈጥሮ ሀብት ወይም አካባቢ ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሰ፣ የሕዝብ አገልግሎት እንዳይሰጥ ያስተጓጎለ ማንኛውም አካል ከአሥር እስከ 15 ዓመታት በሚደርስ ፅኑ እስራት ሊቀጣ እንደሚችል በረቂቅ ሕጉ ተገልጿል፡፡
እንደ ወንጀል ድርጊቱ ጥንካሬ የፀረ ሽብርተኝነት ሕጉ የቅጣት ጣሪያ እስከ 25 ዓመት ፅኑ እስራት የሚያስቀጣ መሆኑን ደንግጎ፣ በወንጀል ድርጊቱ የሰው ሕይወት የጠፋበት ከሆነ፣ በወንጀል ሕግ አንቀጽ 539 የሚዳኝ በመሆኑ በፀረ ሽብር ሕጉ እንደማይሸፈን ተገልጿል፡፡ በሥራ ላይ በሚገኘው የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 የተካተቱና በሌሎች ሕጎች መታየት የሚገባቸውን የክስና የቅጣት ዓይነቶች፣ በአዲሱ አዋጅ በመተው በነባሮቹ ሌሎች ሕጎች እንዲታዩ ማድረጉም ተገልጿል፡፡
በረቂቅ አዋጁ ዋስትና መጠየቅ መብት መሆኑንና አፈጻጸሙ በሌሎች ሕጎች ተፈጻሚ የሚሆነው፣ በሽብር ወንጀል ተጠርጣሪም ላይ እንዲሠራ መተውን ይጠቁማል፡፡ በሥራ ላይ ያለው አዋጅ ጊዜ ቀጠሮን በሚመለከት 28 ቀናት ያላነሰ ጊዜ እንደሚሰጥና ለአራት ጊዜ እንደሚፈቀድ የሚደነግገውን በማሻሻል፣ 14 ቀናት በመፍቀድ ለአራት ወራት መጠየቅ እንደሚቻል ደንግጓል፡፡
ከቅጣት ጋር በተያያዘ በሥራ ላይ ያለው አዋጅ በትንሽ በትልቁ ድርጊት እስከ ሞት ድረስ የሚያስቀጣ ድንጋጌ ቢኖረውም፣ በረቂቁ ካለማስቀጣት እስከ ዕድሜ ልክ ብቻ መሆኑ ተደንግጓል፡፡
በሽብር ወንጀል ውስጥ ተሳታፊ መሆኑ የተረጋገጠበትን ድርጅት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ‹‹አሸባሪ›› ብሎ መሰየም እንደሚችል በረቂቁ ተደንግጓል፡፡ ድርጅቱ በአሸባሪነት የሚሰየመው የሽብር ወንጀልን ዓላማው አድርጎ የሚንቀሳቀስ ከሆነ፣ የድርጀቱ አመራር ወንጀሉን ተቀብሎ ወይም አፈጻጸሙን  ከመራ፣ የድርጀቱ ሠራተኛ ወንጀሉን በማያውቀው አኳኋን የሚያንቀሳቀስ ከሆነ ብቻ መሆኑን ረቂቁ ሕግ ይገልጻል፡፡ ድርጅቱ ‹‹አሸባሪ›› ተብሎ ከተሰየመ በኋላ ስያሜው እንዲሰረዝ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት በማቅረብና ያቀረበው ሐሳብ ተቀባይነት ሲያገኝ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ ሊነሳለት እንደሚችልና ሌሎች ዝርዝር ድንጋጌዎች በረቂቁ ተካተዋል፡፡
ረቂቅ ሕጉ በፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንደሚፀድቅም ተጠቁሟል፡፡  

Source:Reporter


አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Eessa turre,Maalirra Geenyeerra? Kutaa 4ffaa