“ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን የሚጐዳ ሥራ ሆን ብዬ ሠርቼ አላውቅም”

“አንድን ወገን የሚጠቅም ሥራ ያፈርሰናል እንጂ አይጠቅመንም”
                         · በአዲስ አበባ ጉዳይ ለመወያየት ቢሮዬ ክፍት ነው


              ጠ/ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ ወዲህ ለሁለተኛ ጊዜ ከሀገሪቱ የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ለተውጣጡ ጋዜጠኞች ከትናንት በስቲያ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ የአዲስ አበባን የባለቤትነት ጥያቄ ጨምሮ በሰፊ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡ 
ከጠ/ሚኒስትሩ የ2 ሰዓታት ማብራሪያ ውስጥ ዋነኛ ርዕሰ ጉዳዮችን እንደሚከተለው አጠናቅረነዋል፡፡ 
ህግ ማስከበርና የህግ የበላይነት 
ጠ/ሚኒስትሩ በቀዳሚነት ማብራሪያ ከሠጡባቸው ርዕሰ ጉዳዮች አንዱ የህግ ማስከበር ጉዳይ ነው፡፡ በአብዛኛው ህግ እየተከበረ አይደለም የሚል እሣቤ የመጣው የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት በመሞከሩ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ መንግስታቸው በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ በመላ ሀገሪቱ ላጋጠሙ የህግ ጥሰቶች የወሰደውን እርምጃም ዘርዝረዋል፡፡ 
በሶማሌ ክልል ከ30ሺህ በላይ የታጠቀ ሃይል ለውጡን ወደ አልሆነ አቅጣጫ ለመቀየር ሲንቀሳቀስ እንደነበር ጠቅሰው፤ በወቅቱ መንግስት በወሰደው እርምጃ የታሰበውን ማምከን መቻሉን አስታውሰዋል፡፡ በጅግጅጋ ለተፈፀመው ጥፋትም ከ47 ተጠርጣሪዎች በላይ ለህግ መቅረባቸውን፣ በሐዋሳ ለተፈጠረው ችግር ከ100 ሰዎች በላይ፣ በቡራዩ ጉዳይ ከ108 ሰዎች በላይ፣ በአዲስ አበባ ከ68 ሰዎች በላይ፣ በወለጋ የተለያየ አካባቢ ባጋጠሙ ችግሮች ከ2 መቶ በላይ፣ ጌዲኦ እና ጉጂ ላይ በማፈናቀልና ተያያዥ ጉዳዮች ከ300 በላይ በቤኒሻንጉል ከ224 ሰው በላይ ለነበረው መፈናቀልና ጥፋት በህግ መጠየቃቸውንና እየተጠየቀ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡፡ መንግስታቸው በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል የህግ ጥሰት በተፈፀመባቸው ጉዳዮች በሙሉ ጠንካራ የህግ ማስከበር እርምጃ መውሰዱንም በአጽንኦት ገልፀዋል። የህግ ማስከበር እየተከናወነ አይደለም ያስባለውም እንደ ቀድሞ ለተፈጠረ አንድ ችግር ሳያጣሩ የጅምላ እስር እየተፈፀመ ባለመሆኑና በማጣራት ላይ የተመሠረተ የህግ ማስከበር የሚከናወን በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡ 

“አዲስ አበባ የማን ናት?”
“አዲስ አበባ የማን ናት የሚል ክርክር ውስጥ በዚህ ወቅት መግባት አሳፋሪ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የአዲስ አበባ የባለቤትነት ጉዳይን አንስተው የሚከራከሩ አካላትም ከጀርባ ምንን ታሣቢ አድርገው ነው ጥያቄውን ያነሱት? በሚልም ጠይቀዋል፡፡ የአዲስ አበባ ጉዳይ አሁን መነታረኪያ ለማድረግ እየሞከሩ ያሉ አካላትም አሁን የተጀመረው ለውጥና የሀገሪቱ የፖለቲካ ሁኔታ በትክክለኛ አቅጣጫ እንዳይሄድ የሚፈልጉ ናቸው ብለዋል ጠ/ሚኒስትሩ፡፡ 
አዲስ አበባ የመጣባትን ኢትዮጵያዊም ሆነ የውጭ ሀገር ዜጋ በሯን ከፍታ ስታስተናግድ እንደነበርም የሶማሊያና የኤርትራ ዜጐች በስፋት በከተማዋ እንደሚኖሩ ጠቅሰው ያስረዱት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ከተማዋ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ነች፣ የእከሌ ብቻ ነች ልንል አንችልም ብለዋል፡፡ 
ስለ ልዩ ጥቅም ጉዳይም ጠ/ሚኒስትሩ አብራርተዋል፡- አዲስ አበባ በኦሮሚያ መሃል እንደመገኘቷ ከኢንዱስትሪ ማዕከሎቿ የሚወጣው ተረፈ ምርትና ቆሻሻ በኦሮሚያ እንደሚራገፍ፣ በአንፃሩ ከተማዋ የምትገነባበት ጥሬ እቃ በሙሉ ከኦሮሚያ ክልል የሚመጣ መሆኑን በመጥቀስ የልዩ ጥቅም ጉዳይን አብራርተዋል፡፡ 
አንዱን ስናለማ ሌላውን መጉዳት የለብንም ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ ፤የአዲስ አበባም ሆነ ኦሮሚያ ክልል ተመካክረው ጉዳዩን መቋጨት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡ ልዩ ጥቅም ሲባል በአዲስ አበባ ውስጥ የኦሮሞ ልዩ መብት አድርጐ መውሰድም ስህተት መሆኑን፣ አንድ ኦሮሞ አዲስ አበባ ሲኖር ከሌላው የበለጠ መብትና ጥቅም ያገኛል ተብሎ መታሰብ እንደሌለበትም አውስተዋል፡፡ 
የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም ሲባል ኦሮሚያ ለአዲስ አበባ በሚያቀርበው ግብአት ልክ ሊያገኝ ይገባዋል ማለት እንጂ እያንዳንዱ ኦሮሞ ከክልሉ እየመጣ አዲስ አበባ ላይ ከሌሎች ዜጐች የተለየ ነገር ያገኛል ማለት አይደለም ብለዋል ጠ/ሚኒስትሩ፡፡ 
አዲስ አበባን ከማልማት ጋር ተያይዞ እስካሁን ከ170ሺህ በላይ አርሶ አደር አባወራዎች መፈናቀላቸውን የጠቀሱት ጠ/ሚኒስትሩ፤ የእነዚህን አርሶ አደሮች ወቅታዊ ሁኔታ በማጥናት ኑሮአቸውን የማስተካከል ስራ ሊሠራ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡ 
“የባልደራስ” ጉዳይ 
በአዲስ አበባ ጉዳይ እኔ ያልተመቸኝ መፈንቅለ መንግስት የሚመስል እንቅስቃሴ መሆኑ ነው ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ የፌደራል መንግስቱ ያቋቋመውን የከተማ አስተዳደር የማይቀበል አካሄድ የህግ የበላይነትን የሚፃረር ነው ብለዋል፡፡ በሌላውም አካባቢ አርአያነቱ ጥሩ ያልሆነ እንቅስቃሴ መሆኑን የገለፁት ጠ/ሚኒስትሩ፤ “ግለሰቦቹ ባነሱት ሃሳብ ላይ ለመወያየትና ለመነጋገር ቢሮዬ ክፍት ነው” ብለዋል። 
አዲስ አበባ ላይ ለኦሮሞ ብሔር ተወካዮች መታወቂያ በገፍ እየተሠጠ ነው የሚባለው ጉዳይም ውሸት መሆኑን ጠ/ሚኒስትሩ ጠቁመው በጉዳዩ ላይም ግምገማ ተካሂዶ ውሸትነቱ ተረጋግጧል ብለዋል፡፡ 
የዲሞግራፊ ቅየራ (የህዝብ አሰፋፈር ስብጥር) ጉዳይም አዲስ አበባ ለ125 አመታት በተሰባሰቡ ዜጐች የተገነባች ከተማ መሆኗን በመጥቀስ፤ ዲሞግራፊን በአጭር ጊዜ ውስጥ መቀየር አይቻልም፤ ቢታሰብ እንኳ የማይቻል ነው ብለዋል፡፡ 
ከሶማሌ የተፈናቀሉ ኦሮሞዎችን ለማቋቋም ለሁሉም የኦሮሚያ ከተሞች በኮታ ተከፋፍሎ የሚከናወን ስራ መሆኑን የጠቀሱት ጠ/ሚኒስትሩ፤ “እርግጠኛ ባልሆንም አዲስ አበባም 6ሺህ ያህል ተፈናቃዮችን እንዲያቋቁም በኮታ ተሠጥቶታል” ብለዋል፡፡ ኦዴፓም ሆነ ሌላው የሚታገለው አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች ከተሜ እንዲሆኑ ነው ያሉት ዶ/ር ዐቢይ፤ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ለማ መገርሣም የተናገሩት አርሶ አደሮችንና አርብቶ አደሮችን ከተሜ ስለማድረግ ነው፤ ይህ ደግሞ የሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች የትግል አላማ ነው ብለዋል፡፡ 
አዲስ አበባ ላይ ሌላውን እያሳነሱ የኦሮሞን ቁጥር ማሳደግን ግን አስበነውም አናውቅም ለወደፊትም አይታሰብም ብለዋል ጠ/ሚኒስትሩ፡፡ “አንድን ወገን የሚጠቅም ስራ መስራት ያፈርሰናል እንጂ አይጠቅመንም” ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያውያን በሙሉ እኩል የሚጠቀሙበት ከተማና ስርአት ነው መፍጠር ያለብን ብለዋል፡፡ 
ኮዬ ፈጬን በተመለከተም የጋራ መኖሪያ ቤት የደረሳቸው በሙሉ ኢትዮጵያውያን መሆናቸውን በመጥቀስም፤ የወሰን ጉዳይ እልባት ካገኘ በኋላ ቤቶቹ ለባለዕድለኞች እንደሚተላለፉ ጠቁመዋል።  የወሰን ውዝግቡም ከባለእድለኞች ጋር የሚገናኝ ችግር አይደለም ብለዋል፡፡ 
የ5 ሚሊዮን ብር እራት ለሸገር 
የዚህን ፕሮጀክት ገጽታዎች በከፊል ያብራሩት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ፕሮጀክቱ በውስጡ ከሚያካትታቸው መካከል 100ሺህ ሰዎችን የሚያስተናግድ አደባባይና 20ሺህ ተጠቃሚዎችን የሚያስተናግድ ግዙፍ ቤተ መጽሐፍት ተጠቃሽ ናቸው፡፡ 
መለስተኛ በአላትና የሙዚቃ ድግስ (ኮንሰርት) ለማቅረብ የሚውል 100 ሺህ ሰዎች የሚያስተናግደው አደባባይ ከሸራተን ጀርባ ባለው የታጠረ ቦታ ላይ የመገንባት ስራ ከአንድ ወር በኋላ እንደሚጀመርና በአንድ አመት ጊዜ ውስጥ እንደሚጠናቀቅ አስታውቀዋል፡፡ 
20ሺህ ሰዎች የሚያስተናግደውና የፕሮጀክቱ አካል የሆነው ቤተ መፃሕፍትም የአዲስ አበባ ልዩ መለያ (ላንድ ማርክ) እንዲሆን ታስቦ ይሠራል ብለዋል - ጠ/ሚኒስትሩ፡፡  
ይህን ፕሮጀክት የሚደግፉ ባለሃብቶችም በፕሮጀክቱ ቦታ ላይ ቋሚ ሐውልት እንደሚኖራቸው ያስታወቁት ጠ/ሚኒስትሩ፤ አንድ ሰው 5 ሚሊዮን ብር የሚከፍልበት የእራት ፕሮግራምም በመጪው ግንቦት ወር መጀመሪያ በብሔራዊ ቤተመንግስት፣ የአፄ ምኒልክ የግብር አዳራሽ ይከናወናል ብለዋል፡፡ 
በዚህ የእራት ፕሮግራም ላይ ለመሳተፍ የግብጽ፣ ኬንያ፣ ጅቡቲና ደቡብ ሱዳን ባለሀብቶች ተመዝግበዋል፡፡ በዚህ ፕሮጀክት ላይ ኢንቨስት ያደረጉ ባለሃብቶች ስማቸው በጉልህ ይቀመጣል ፎቶ ግራፋቸውም በቤተ መጽሐፍት ውስጥ ለታሪክ ማስታወሻነት ይሰቀላል ብለዋል - ጠ/ሚኒስትሩ፡፡ 
“ኢንሣ እና ጠ/ሚኒስትሩ”
ኢንሣን በሚመለከት ለወደፊት ባዮግራፊውን እጽፋለሁ፡፡ እጅግ የሚያኮራ ስራ የሠራሁበት ተቋም ነው፡፡ ምንም የሚያሳፍር ተግባር ኢንሣ እያለሁ ፈጽሜ አላውቅም፤ ይሄን አስመልክቶ ማንኛውም ሰው መረጃ ካለው መረጃውን ለህዝብ ይፋ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ እኔ ነፍስ ካወቅሁበት ጊዜ ጀምሮ ኢትየጵያንና ኢትዮጵያውያንን የሚጐዳ ስራ ሆን ብዬ ሠርቼ አላውቅም፡፡ ይሄ በደሜ ውስጥ ያለ እውነት ስለሆነ በድፍረት መናገር እችላለሁ፡፡ የሆነ ሆኖ የተደበቀ ነገር ካለ ለህዝብ መግለጥ ጥሩ ነው። ተጨባጭ ማስረጃ ይዞ መቀመጥ ተገቢ አይደለም። የሚያስጠይቅ ነገር ካለ ለመጠየቅ፣ የሚያስወቅስ ከሆነም ለመወቀስ ዝግጁ ነኝ፡፡” ብለዋል፡፡ 
ጠ/ሚኒስትሩ ባለፈው 1 ዓመት የስልጣን ዘመናቸው በሠሩት ስራ ውስጥ ይሄን ባላደረግሁ ብለው የሚቆጫቸው ነገር እንደሌለ ገልፀዋል፡፡ “አቅሜ በፈቀደ ሁሉ ካለምንም መታከት ሮጫለሁ፤ በጣም በርካታ ድሎች አምጥቻለሁ” ብለዋል፡፡ 
በአንድ ዓመት ሊታሰቡ የማይችሉ በዲፕሎማሲ፣ በፖለቲካውና በኢኮኖሚ ዘርፍ ሠርቻለሁ፣ በዚህ የሚቆጨኝ ነገር የለም ብለዋል፡፡ 
“ትግራይና አማራ”
በአማራና በትግራይ ክልሎች መካከል የድንበር ይገባኛል ጥያቄዎች የተነሳ ቢሆንም እስካሁን የከፋ ግጭት አለመፈጠሩን ያወሱት ጠ/ሚኒስትሩ፤ ከዚህ በኋላም ወደ ግጭት የሚገቡበት ሁኔታ አይኖርም ብለዋል፡፡ “እዚህ ሀገር ላይ በሁለት ክልል መካከል ግጭት ሊፈጠር አይችልም፤ ትግራይ አማራ ክልልን የሚወጋ ከሆነ ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ይዋጋል፤ የአማራም ክልልም ትግራይ ክልልን ከወጋ ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ይዋጋል” ብለዋል፡፡ 
የትግራይና የአማራ መሪዎችም ችግሮቹን በውይይት ፈትተው ከታሪክ ተወቃሽነት ራሣቸውን እንዲያድኑ ጠ/ሚኒስትሩ አሳስበዋል፡፡ 
ኦዴፓ እና አዴፓ ምንና ምን ናቸው? 
በዚህ የለውጥ እንቅስቃሴ ውስጥ በፊት አውራሪነት የሚጠቀሱት አዴፓ እና ኦዴፓ ግንኙነታቸው ጤናማ መሆኑን ጠ/ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል፡፡ በለውጡ ላይም ታሪካዊ ኃላፊነታቸውን ለመወጣት የሚያስችላቸውን ውይይትና ግምገማ በየጊዜው እያካሄዱ፣ ጠንካራ ተግባራትን እያከናወኑ መሆኑንም ጠ/ሚኒስትሩ አውስተዋል፡፡ 
የዚህችን ታላቅ ሀገር ህልውና ለማስቀጠል ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀላፊነት ስሜት መስራት ይገባቸዋል ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ በኦዴፓ እና በአዴፓ መካከል ግልጽ የፖለቲካ መተማመንና የሃሣብ ልውውጥ መኖሩንም አረጋግጠዋል፡፡ በሁለቱ ድርጅቶች መካከል የሚያሠጋ ልዩነት አለመኖሩንም አስረግጠው ተናግረዋል፡፡ 
በኢሕአዴግ ውስጥ ያሉ ሁሉም ፓርቲዎች አንድ አይነት አሠራር፣ አላማና ግብ እንዳላቸው የጠቆሙት ጠ/ሚኒስትሩ ለውህደት የሚያበቃቸው ጥናት ተሠርቶ መጠናቀቁንና በጥናቱ ላይ መግባባት ሲፈጠር ውህደት ይፈፀማል ብለዋል፡፡ 
“የመለመን ፀጋ አለኝ”
ጠ/ሚኒስትሩ በቤተ መንግስት ስለሚያከናውኑት የእድሳት ተግባር ባብራሩበት ወቅት በልመና ብዙ ተግባራትን እያከናወኑ መሆኑን አውስተዋል፡፡ “እኔ የልመና ፀጋ አለኝ፤ ለምኜ አጥቼ አላውቅም” ያሉት ጠ/ሚኒስትሩ፤ በቤተ መንግስት የሚከናወነው የእድሣትና የፓርክ ግንባታ ውጪም ሙሉ ለሙሉ በልመና ያገኙት መሆኑን እንዲሁም በቀዳማዊት እመቤት ጽ/ቤት በኩል በየክልሉ የሚገነቡ ት/ቤቶችና የአይነ ስውራን ት/ቤቶች በልመና በተገኘ የ1ቢሊዮን ብር ድጋፍ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡ 
ቤተ መንግስቱ በውስጡ የሚደንቁ ታሪኮች ያሉበት መሆኑን በመግለጽ፤ የስራውን ሂደት በየቀኑ እንደሚከታተሉትና እስካሁን ከሠሯቸው ስራዎች የቤተመንግስቱ ስራ ሃውልት ሆኖ ለዘመናት የሚዘልቅ መሆኑን “ልጆቻችን ኢትዮጵያ ምን እንደምትመስል የሚያውቁበት፣ ለትውልድ የሚተላለፍ ፕሮጀክት ነው” ብለዋል - ጠ/ሚኒስትሩ፡፡  
“መፈናቀል”
እሣቸው ወደ ስልጣን በመጡበት ወቅት 1.2 ሚሊዮን ዜጐች ከሶማሌ ክልል ተፈናቅለው በየመጠለያ ጣቢያው እንደነበሩ ያወሱት ጠ/ሚኒስትሩ ከለውጡ በኋላም አሳፋሪ ብለው በገለፁት መልኩ 1.5 ሚሊዮን ዜጐች ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች መፈናቀላቸውን አስታውቀዋል። ከጠቅላላው ተፈናቃዮች 1 ሚሊዮን ያህሉ ወደነበሩበት መመለሳቸውን ቀሪዎቹንም በአጭር ጊዜ ውስጥ መልሶ ለማቋቋም እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ 
በጌዴኦ ተፈናቃዮች ተርበዋል የተባለውም ተጋኖ የቀረበ መሆኑንና አንድም ሰው በረሃብ አለመሞቱን ነገር ግን አሳዛኝ በሆነው መፈናቀል ሴቶች እና ነፃነት ለሰብአዊ ጉስቁልና መጋለጣቸውን፣ ከበሽታም የአንድ ሰው ህይወት ማለፉን በመጠቆም መንግስታቸው ዜጐችን መልሶ ለማቋቋምና ለመርዳት በሙሉ አቅሙ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ 

Source:Reporter

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Eessa turre,Maalirra Geenyeerra? Kutaa 4ffaa