በህብረትና በመደማመጥ ከሰራን ኢትዮጵያን መለወጥ ይቻላል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ

ፊንፊኔ ሚየዝያ 03/2011(ቶለዋቅ ዋሪ) በህብረትና በመደማመጥ ከሰራን ኢትዮጵያን መለወጥ ይቻላል አሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ።
በነቀምቴ ከተማ የተገነባው የወለጋ ስታዲየም በዛሬው እለት በይፋ ተመርቆ ለአገልግሎት ክፍት ተደርጓል።
የወለጋ ስታዲየምን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ እና የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሀላፊዎች መርቀው ከፍተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በምርቃው ላይ ለአካባቢው ነዋሪዎች እንኳን ደስ አላችሁ በማለት መልእክት አስተላልፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልእክታቸው አክለውም፥ አሁን በሀገሪቱ የተገኘው ድል የትውልድ ቅብብሎሽ የትግል ውጤት ነው፤ ወጣቱ ትውልድም አሁን የተገኘውን ድል ለመጠበቅና ለማስቀጠል ዝግጁ መሆን አለበት ብለዋል።
ትናንት ለኢትዮጵያ መስዋእትነት የከፈሉ ተጋዮች ለዛሬ መሰረት የጣሉ ናቸው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፥ እኛም የተጣለብንን አደራ ለመጠበቅና ሀገሪቱን ለመለወጥ መደማመጥና በህብረት መስራት አለብን ብለዋል።
ይህንን ማድረግ የምንችለው ግን ሰላማችንን እና አንድነታችንን ስንጠብቅ ነው ሲሉም በአደራ ጭምር መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ፥ የምስራቅ ወለጋ ዞን 5 የኦሮሚያ ዞኖችን እንዲሁም ክልሉን ከአማራ ክልል እና ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ጋር የሚያዋስን መሆኑን አንስተዋል።
ስለዚህም ምስራቅ ወለጋን ማልማት ሌሎችንም ተጠቃሚ ማድረግ ስልሆነ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራበት ነው ሲሉም ተናግረዋል።
ለወጣቶች ባስተላለፉት መልእክትም፥ የአካባቢው ነዋሪ ወጣቶች በመደማመጥ መንፈስ ቆርጠው ከተነሱ ወለጋን እና በአጠቃላይ ኢትዮጵያን ማልማት ይቻላል ብለዋል።
ለተፎካካሪ ፓርቲዎችም፥ ለህዝቡ ጥቅም በሀገሪቱ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች በሙሉ በጋራ በመደማመጥና በመተጋገዝ እንስራ ሲሉ በድጋሚ ጥሪ አቅርበዋል።
“ያለጦር መሳሪያ ነፃነትን እውን እንዳደረግን ሁሉ አሁንም ያለምንም የጦር መሳሪያ ያሰብነበት መድረስ እንችላለን” ሲሉም ተናግርዋል።
የነቀምቴ ከተማና የመላ ኦሮሚያ ክልል ነዋሪዎች የኢትዮጵያንና የክልሉን አንድነት በሰላማዊ መንገድ ለማረጋገጥ ተባብረውና ጠንክረው እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል።
የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ በበኩላቸው፥ የእንኳን ደስ አላችሁ መልእከት በማስተላለፍ፤ የስታዲየሙ ግንባታ ከፍተኛ ጥቅም እና ትርጉም ያለው መሆኑን አንስተዋል።
የወለጋ ስታዲየም በህብረተሰቡ ከፍተኛ ርብርብ እዚህ መድረሱን ያነሱት ርእሰ መስተዳድር አቶ ለማ፥ ይህ ደግሞ በእንድነት ከተነሳን ማንኛውንም ነገር ማድረግ እንደምንችል ማሳያ ነው ብለዋል።
“አንድነት ሀይል ነው” ለሚለው አባባልም የወለጋ ስታዲየም ትልቁ ማሳያም መሆኑን ነው ያነሱት።
ስታዲየሙ ተገንብቶ ከመመረቅ በዘለለ ስፖርተኞችን ማፍራት እና የአካባቢውን ነዋሪዎች በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ማድረግ በሚችልበት መልኩ ሊሰራበት እንደሚገባም መልእከት አስተላልፈዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች በተለይም ደግሞ ወጣቶች ስታዲየሙን በአግባቡ በመጠቀም ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚጠበቅባቸውም አንስተዋል።
ርእሰ መስተዳድር አቶ ለማ አክለውም፥ ክልሉን የሰላም፣ የመደማመጥና የመከባበር ምድር ለማድረግ ህብረተሰቡ በተለይም ደግሞ ወጣቶች በአንድነት መስራት እንዳለባቸው ነው ያሳሰቡት።
ምእራብ ኦሮሚያ በተለይም ወለጋ በተፈጥሮ ሀብት የበለፀገ ነው ያሉት አቶ ለማ፥ ነገር ግን በሰላም እጦት ምክንያት ማደግ እና መለወጥ እንዳልቻለ አንስተዋል።
አሁን ላይ ግን የአካባቢውን ሰላም በማስጠበቅ በኢኮኖሚው ዘርፍም ተጠቃሚ ማድረግ ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነውም ብለዋል።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Obbo Muktaar Kadir pireezidaantii Mootummaa Naannoo Oromiyaa ta’uun lammata filataman