ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይና ርእሰ መስተዳድር አቶ ለማ ከምስራቅ ወለጋ ዞን ነዋሪዎች ጋር ተወያዩ
ፊንፊኔ ሚየዝያ 03/2011(ቶለዋቅ ዋሪ) የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ ከምስራቅ ወለጋ ዞን የህብረተሰብ ተወካዮች ጋር ተወያዩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ በነቀምቴ ከተማ አደራሽ ነው ከህብረተሰብ ክፍል ተወካዮች ጋር የተወያዩት።
በውይይቱ ላይ የተካፈሉ የህብረተሰብ ክፍሎችም በዞኑ ባሉ ችግሮች ዙሪያ በተለይም በስራ አጥነት ላይ ትኩረት በማድረግ ጥያቄዎችን አቅርበዋል።
እንዲሁም በፌደራል ደረጃ የተጀመረው ለውጥ በክልልና በዞን ደረጃ እንዲወርድ፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በምክክር እንዲሰራ፣ ያለአግባብ የታሰሩ ሰዎች እንዲፈቱ፣ ባለሀብቶች ወደ አካባቢው በመሄድ ኢንቨስት እንዲያደርጉ፣ የፀጥታ ችግር እንዲፈታ እና አስተማማኝ ሰላም አንዲሰፈን እንዲሁም የኦሮሞ ፖለቲካ ወደ አንድ አቅጣጫ እንዲመጣ ጠይቀዋል።
በመድረኩ ላይ ለተነሱ ጥያቄዎች እና አስተያየቶችም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በሰጡት ምላሽና ማብራሪያ፥ አሁን በተገኘው ድል ህዝብን ወደ ማገልግል አልተሸጋገርንም፤ የምንፈልገውን በሙሉ ለማግኘት ጊዜ ይወስዳል ብለዋል።
ይህንን ለማረጋገጥ ደግሞ ህዝቡ አሁን የመጣውን ለውጥ በመደገፍና ሙሉ በሙሉ የራሱ ማድረግን እንደሚጠይቅ ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያነሱት።
ከልማት ጋር ተያይዘው ለሚነሱ ጥያቄዎችም፥ የመልማት ጥያቄዎች ዘላቂነት ባለው መልኩ መፍትሄ እንዲያገኙ ትኩረት ተሰጥቶበት እንደሚሰራም ገልፀዋል።
ያለ አግባብ ታስረዋል ስለተባሉ ሰዎችም የክልሉ ርእሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ ኮሚቴ አቋቁመው የማጣራት ስራ ይሰሩበታል ሱሉም አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አክለውም፥ መንግስት ወለጋን ለመለወጥ ትኩረት በመስጠት በከፍተኛ ቁርጠኝነት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ወለጋን ለመለወጥ ግን ህብረተሰቡ ከማማረር ስሜት በመውጣት ወደ ድል አድራጊነት ስሜት መሸጋገር ወሳኝ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
ባለበህቶች ለልማት ወደ ወለጋ እንዲመጡ ይደራጋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፥ በለሀብቶቹ በሚመጡበት ጊዜ ግን ለእነሱ ከለላ ማድረግ ከህብረተሰቡ እንደሚጠበቅም አንስተዋል።
ህብረተሰቡ ከአዲስ አበባ አሶሳ የሚዘልቅ የባቡር መስመር ግንባታ እና የነቀምቴ አውሮፕላን ማረፊያ ጉዳይ ላይም ላነሱት ጥያቄ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በሰጡት ምላሽ፥ ከባቡር ጋር በተያያዘ እስካሁን የታሰበ ነገር እንደሌላ ጠቅሰው፤ የነቀምቴ አውሮፕላን መረፊያ ግንባታን ግን በፍጥነት ለማጠናቀቅ እንደሚሰራም ገልፀዋል።
የኦሮሚያ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ለማ መገርሳ በበኩላቸው በሰጡት ማብራሪያ፥ በምእራብ የሀገሪቱ ክፍል ከፍተኛ የሆነ የስራ አጥነት ችግር እንዳለ በማንሳት፤ ችግሩን ለመቅረፍ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ህዝቡም የአካባቢውን ሰላም በማስጠበቅ በልማት ስራ ላይ ተሰማርቶ ከመንግስት ጋር በመተባበር እንዲሰራም ጥሪ አቅርበዋል።
አሁን ያለው የለውጥ መንግስት የተማረ የሰው ሀይል በብዛት ስለሚፈልግ የወለጋ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ የትምህርት ተቋማትን ማስፋፋት ላይ እንደሚሰራም ገልፀዋል።
የምእራብ ኦሮሚያ የፀጥታ ችግር በልማቱ ላይ ተጽእኖ መፍጠሩን የገለፁት አቶ ለማ፥ ባለሀብቶች እንዲመጡ ከተፈለገ የአካባቢው የሰላም ሁኔታ መሻሻል አለበት ብለዋል።
ዘላቂ ሰላም እንዲሰፍን፣ የተፈለገው ልማት እውን እንዲሆን፣ የክልልም ይሁን የሀገሪቱ ኢኮኖሚ እንዲያድግ ህዝቡ ከመንግስት ጋር ተቀራርቦ መስራት እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ