የኢትዮጵያ ህዝብ…ሊጠራጠረን አይገባም” – የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ለማ መገርሳ


“ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚያዋጣው አንድነት ፣ መተማመንና መተሳሰብ ነው፤ ህዝቡ ነገም ቢሆን ሊጠራጠረን አይገባም” ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዚዳንት ለማ መገርሳ ተናገሩ።

ፕሬዚዳንቱ ”ኢትዮጵያዊነት ሱስ መሆኑን ምንጊዜም ያለ ሀፍረት እናገራለሁ” ብለዋል።

ፕሬዚዳንቱ በክልሉ ከሚገኙ ባለሃብቶች ጋር በወቅታዊ ሁኔታ ላይ ተወያይተዋል።
በውይይቱ ወቅት ከተሳታፊዎች ፕሬዚዳንቱ በኢትዮጵያዊነት ላይ ስላላቸው አቋምና ከአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ጋር ፓርቲያቸው ስላለው ግንኙነት ለተነሳላቸው ጥያቄ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

አቶ ለማ ከነባልደረቦቻቸው ለኢትዮጵያ አንድነት የሰሩትና የለፉት ዝናና ዕውቅና በመፈለግ እንዳልሆነ ተናግረዋል።
ፕሬዘዳንቱ “ለኢትዮጵያ ህዝብ ለኦሮሞ ህዝብ አንድነቱ ነው የሚጠቅመው። አንድነቱ ምርጫ አይደለም ለኢትዮጵያ ህዝብ ምርጫ አይደለም ስንፈልግ የምንወስደው ስንፈልግ የምንጥለው አይደለም አምንበታለሁ። ማመን ብቻ አይደለም ለዚህ ሰርቻለሁ፣ ለፍቻለሁ፣ ዋጋ ከፍያለሁ፤ የኔ ባልደረቦች ዋጋ ከፍለውበታል። ስንሰራ ዝናን ለመፈለግ አይደለም እውቅና በመፈለግ አይደለም ዕውቅና ተሰጠን አልተሰጠን ህሊናዬ ንጹ እስከሆነ ድረስ ለኔ በቂዬ ነው። ስለዚህ አሁንም ኢትዮጵያዊነት ያለ ሀፍረት እናገራለሁ ነገም ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው። ለኦሮሞ ህዝብም የሚጠቅመው እንደኛ አይነት ደሃ ብዙ ድሪቶ ያለብን ህዝብ መከፋፈል አይጠቅመንም። የሚያዋጣን የሚጠቅመን አንድነት ነው። መተማመን፣ መተሳሰብ፣ መቻቻል ነው የሚጠቅመን።” ብለዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ለማ መቼም ቢሆን ለአገሪቱ አንድነት እንደሚሰሩ ገልጸው ኢትዮጵያውያን እናቶች ከልጆቻቸው እኩል በጸሎት ሲያስቧቸው እንደነበር አስታውሰዋል።
የኢትዮጵያ ህዝብ መቼም ቢሆን ሊጠራጠራቸው እንደማይገባ ተናግረው በኦሮሚያ ክልል ውስጥ በሚወስኑት ውሳኔ የሚከፋ ማንኛውም አካል ውሳኔያቸው ትክክል ካልሆነ ቢወቅሳቸውና ቢገስጻቸው እንደሚታረሙ ገልጸዋል።
አቶ ለማ ሰው በመሆናቸው በስራ ሂደት ስህተት ቢሰሩ ለአገሪቱ ያበረከቱትን ስራ በዜሮ ማባዛትና ማንነትን መሰረት ያደረገ ዘለፋ መሰንዘር ተገቢ አለመሆኑን አስገንዝበዋል።
“የኢትዮጵያ እናቶች እንደወለዷቸው ልጆች ከኛ ጋር አምጠው በየጓዳው ጸልየውልናል። ለዚህ ዋጋ እንሰጣለን ክብር ለሚገባው ውለታ ቢሶች አይደለንም። ንጹህ የኢትዮጵያ ህዝብ ነገም ቢሆን ሊጠራጠረን አይገባም። ስለዚህ ነገም ቢሆን የትም ሆንኩ የት በምንችለው አቅም ለዚህች አገር አንድነት እንሰራለን። ስለወደድን ስለፈለግን ብቻ አይደለም ከዚህ ውጪ አማራጭ ስለሌን ነው።” ያሉት፡፡
እሳቸውም ሆኑ ባልደረቦቻቸው ትልቅ የሆነችውን ሀገር ኢትዮጵያን በማፍረስ ቆሻሻ ታሪክ ጥለው ማለፍ የማይፈልጉ መሆናቸውን አመልክተው ሃይማኖት፣ ጎሳና ዘር በመቁጠር አንዱን ለመጥቀም፣ ሌላውን ለመጉዳት እንደማይሰሩ አረጋግጠዋል።
ከአማራ ክልል ጋር ያላቸው ግንኙነት ዛሬም ጠንካራ እንደሆነ ያስረዱት አቶ ለማ የኦሮሚያ ክልል አመራር በአማራ፤ የአማራ ክልል በኦሮሚያ ጉዳይ ላይ እኩል የያገባኛል ስሜት እንዳላቸው ጠቁመዋል።

“ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ነች ደሃ ሆነን ነው እንጂ አፍሪካ ከኢትዮጵያ ውጪ ስሟ ሊነሳ አይችልም። ከናይጄሪያ ቀጥላ ግዙፏ ትልቅ አገር ነች ዛሬ እኛ ዕድል ስላገኘን ዕድል ስለጣለብን ይህቺን አገር መሰብሰብ ነው እንጂ አፍርሰን መሄድ አፍርሰን ቆሻሻ ታሪክ ጥለን ማለፍ አንፈልግም – እኔም ባልደረቦቼም።
በዚህ ደሃ መካከል ሃይማኖትን እየቆጠርን፣ ጎሳን እየቆጠርን፣ ዘርን እየቆጠርን እየለየን አንዱን ጠቅመን አንዱን ጎድተን አንዱን ከፍ አድርገን አንዱን ዝቅ አድርገን ታሪክ እንሰራለን ብለን አናስብም። ሁሉም ተጋግዞ አንድ ላይ እንዲኖር ነው የምንፈልገው።
ይህቺን አገር የመበታተን ህልም የለንም እንዲህ አይነት ክፋት የመስራት ህልም የለኝም። እኔ ለዚህች አገር አንድነት ዋጋ ከፍያለሁ። ባለውለታም ነኝ ከአዴፓ ጋር ተለያይታችኋል ይባላል፤ ስልጣን ቀምታችኋል ይባላል፤ በእርግጠኝነት እነግራችኋለሁ ከትናንት በላይ ዛሬ ኦሮሚያ ላይ ሆኜ ጎንደር ለምን እንዲህ ሆነ ማርቆስ ለምን እንዲህ ሆነ ብዬ ለመደመጥ ዛሬ መብት አለኝ።
ጅማ ላይ ባሌ ላይ ለምን እንዲህ ሆነ ብሎ የሚደመጥ አመራር ባህር ዳር ላይ አለ። ምንም ችግር የለም በመካከላችን ችግር ያለው ፌስቦክ ላይ ነው።” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያን አንድነትና ሰላም አጠናክሮ ለማስቀጠል የአማራና የኦሮሞ ህዝብ. ከመቼውም ጊዜ በበለጠ አንድነቱን ማጠናከር እንደሚጠበቅበት ገልጸዋል።
በአማራና ኦሮሚያ አመራሮች መካከል የተፈጠረው አንድነት ለስልጣን ሳይሆን መስዋትነት በመክፈል አገሪቱን ከመፍረስ የማዳን ዓላማ እንደሆነ ተናግረዋል። “የኢትዮጵያ ህዝብን አንድ ለማድረግ ከምንም በላይ ታሪክ ሃላፊነት የጣለብን።
በአማራና በኦሮሞ መካከል የተቀበረውን ለማምከን የእኛ ሃላፊነት ነው ብለን እናምናለን። እነኚህ ሁለት ግንድ ህዝቦች አንድ ሆነው ሌላውን ኢትዮጵያዊ አቅፈው ወደፊት አምጥተው ይህች አገር ሰላም እንድትሆን ማድረግ አለባቸው። ዛሬ ሳይሆን ነገ ኢትዮጵያ ሰላም እንድትሆን እነኚህ ህዝቦች አንድ መሆን አለባቸው። እራሳቸው አንድ ሆነው ሌላውንም አንድ ማድረግ አለባቸው ብለን በጽኑ እናምናለን።
እኛና የአማራ አማሮች ትናንት ስንስማማ በሆነ ወቅት ላይ የሆነ ነገር ሲከሰት ስልጣን እንደቅርጫ እንከፋፈላለን ብለን አናውቅም። እውነቱን ለመነጋገር ያጋመደን ፍቅር አደለም፤ ችግር ነው። መከራ ነው ያገናኘን እኛ ትናንት ስንገናኝ ነገ ስልጣን አግኝተን ፕሬዚዳንት እንሆናለን ሚኒስትር እንሆናለን የሚል ህልም አልነበረንም እኛ ሞተን ይህቺ አገር ከመፍረስ ማዳን ነው።” ብለዋል፡፡”(ቅዳሜ መጋቢት 21/2011 በኦሮሚያ ክልል ከሚንቀሳቀሱ ባለሀብቶች ጋር የተደረገ ውይይት

ምንጭ OBN)

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Eessa turre,Maalirra Geenyeerra? Kutaa 4ffaa