«የፀጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ የመሰብሰብ ስልጣን የለውም» አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ





የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ ስብሰባ የመጥራት ህጋዊ ስልጣን የለውም ሲሉ በድርጅቱ የኢትዮጵያ ቋሚ መልእክተኛ አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ተናገሩ።

አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ለአንድ የአገር ውስጥ ሚድያ እንደተናገሩት፣ አሁን ላይ በኢትዮጵያ የተፈጠረው ችግር የውስጥ ጉዳይ ነው፡፡ አገራት ደግሞ ውስጥ ጉዳዮቻቸውን በራሳቸው የመፍታት ሉኣላዊነት አላቸው፡፡ ሆኖም ጉዳዩ ዓለም አቀፍ የጸጥታና ደኅንነት ስጋት እስካልሆነ ድረስ የመንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ጉዳዩን አጀንዳ አድርጎ ስብሰባ የመጥራት ህጋዊ ስልጣን የለውም።

የኢትዮጵያን ጉዳይ ዓለም አቀፍ የጸጥታና ደኅንነት ስጋት ይሆናል በሚል አንዳንድ አገራት ጉዳዩን ከራሳቸው ፍላጎት አንጻር በማየት የሽብርተኛው የሕወሓት ቡድንን ጉዳይ ይዘው ወደ ጸጥታው ምክር ቤት መሄድ ሥራቸው አድርገውታል ያሉት አምባሳደር ታዬ፤ የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ጉዳይን ሳይጨምር በኢትዮጵያ ካለው ወቅታዊ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ብቻ ባለፉት ሁለት ዓመታት ምክር ቤቱ ለ12ኛ ጊዜ ስብሰባ መጥራቱን አስረድተዋል።

እንደ ቋሚ መልዕክተኛው ገለጻ፣ ምክር ቤቱ በሰሜኑ አገራችን ከተከሰተው ጦርነት ጋር በተያያዘ ሁለት ጊዜም መግለጫ ሰጥቷል፤ ጉዳዩ ዓለም አቀፍ የጸጥታ አንድምታ በሌለበት ሁኔታ ምክር ቤቱ የአገራትን ጉዳይ የሚመለከትበት አንዳችም ምክንያት የለውም።

በአንድ አፍሪካዊ አገር ውስጥ ችግር አለ ተብሎ ከታሰበም ጉዳዩ መታየት ያለበት በአፍሪካ ኅብረት በኩል መሆኑን ጠቁመው፤ በአፍሪካ ኅብረት የሰላምና ጸጥታ ምክር ቤትና በመንግሥታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በኩል ያለው ግንኙነት የሚወሰነውም በዚሁ መርህ መሆኑን ገልጸዋል።

አንዳንድ አባል አገራት ካላቸው ፍላጎት አንጻር በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ስብሰባ እንዲጠራ ሊያደርጉ እንደሚችሉ የጠቆሙት ቋሚ መልዕክተኛው፤ «ስብሰባ ከጠሩም ውሳኔዎች እንዳይተላለፉና መግለጫዎች እንዳይሰጡ በማድረግ ስብሰባው ውጤት አልባ ለማድረግ በኢትዮጵያ በኩል እየተሠራ ነው» ሲሉም አብራርተዋል።

ይህን ለማድረግ የሁሉም አባል አገራት ስምምነት እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ «የኢትዮጵያ የውስጥ ችግሮች በራሷ መፈታት አለባቸው» የሚል አቋም የያዙና ወሳኝ ድምጽ ያላቸው በርካታ አገራት እንዳሉም ጠቁመዋል።

ሽብርተኛው የሕወሓት ቡድን ለመንግሥታቱ ድርጅት የላካቸው ደብዳቤዎችን በተመለከተ፣ የሽብር ቡድኑ ከመርህ ባፈነገጠ መልኩ ለስድስተኛ ጊዜ ለድርጅቱ ደብዳቤ መላኩን የተናገሩት ቋሚ መልዕክተኛው፤ ደብዳቤዎቹ እርስ በእርስ የሚጣረሱና ሃሳበ ጽኑነት የሌላቸው መሆናቸውንም አስረድተዋል።

መንግሥት ያልሆኑ አካላት የሚጽፏቸው ደብዳቤዎች በሙሉ የመንግሥታቱ ድርጅትን በር ያንኳኳሉ ማለት አይቻልም ያሉት አምባሳደር ታዬ፤ ነገር ግን በቀረቡ ደብዳቤዎች ሁሉ ስብሰባ አይጠራም ብለዋል።

የመንግሥታቱ ድርጅት የአባል አገራት ተቋም ሲሆን አገራቱ የሚስተናገዱትም በአሠራር፣ በደንቦችና በድርጅቱ ቻርተር መሠረት መሆኑንም አብራርተዋል።

@አዲስ ዘመን  መስከረም 4/2015 ዓ.ም

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Eessa turre,Maalirra Geenyeerra? Kutaa 4ffaa