አቶ ፈቃዱ ተሰማ አዲስ ዓመትን ምክንያት በማድረግ ያስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት



እኛ ኢትዮጵያዊያን ከተቀረዉ ክፍለ ዓለም ህዞቦች ለየት ያለ የባህል የፍልስፍ እና የታሪክ አሻራ እና ገጽታ አለን። ለየት ከሚያደርጉን ገጽታዎች አንዱና ዋነኛዉ የዘመን አቆጣጠር ቀመራችን ነዉ። ይህንን ከቀደምት አባቶቻችን ያገኘነዉን አኩሪ ታሪካችን እሰከ ዛሬ ድረስ ሳይበረዝ እና ይዘቱን ጠብቆ ከማይዳሰስ እና ከሚዳሰሱ ወረቶቻችን እና ቅርሶቻችን ዝርዝር ዉስጥ ጎልቶ ይታያል።
በኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጣር እና ዕይታ ወርሃ መስከረም የዘመን መለወጫ ብቻ ሳይሆን በአዲስ ተስፋ አዲስ ራዕይ የሚሰንቅበት ወር ነዉ። አርሶ አደሩ ከአድካሚዉ እና ዉጣ ዉረድ ከበዛበት የክረምት ጭጋጋማዉ ወራት በኋላ በአዝመራዉ ማበብና ማዘርዘር ሃሴት አድርጎ በተስፋ ቀጣዩን የህይወት ዕጣ ፈንታዉን የሚያይበት፣ ተማሪዉ ካለፈዉ ዓመት የትምህርት ተሞክሮዉ ተነስቶ ለሚቀጥለው የትምህርት እርከን ራሱን የሚያዘጋጅበት፣ መምህራን ለተሻለ የትዉልድ ቀረፃ አዲስ ግብና ራዕይ ሰንቀዉ የሚዘጋጁበት፣ በአጠቃላይ መላዉ ኢትዮጵያውያን ካለፈዉ ዓመት ህይወት ተሞክሮአቸዉ በመነሳት አዲስ ትልም፣ በአዲስ የአኗኗር ቅኝትና በተስፋ ለመንደርደር በጉጉት የሚጠብቁት የዘመን መለወጫ ወር ነዉ።ወርሃ መስከረም የተስፋ ተምሳሌት በሆነዉ አደይ አበባ ደምቆ ወደ አዲስ ህይወት የሚያሸጋግረን የዘመን አቆጣጣር መባቻችን እና ሕዝባችን ደግሞ የአዲስ ዓመት መጀመሪያ ምዕራፉን በአብሮነት እና በፍቅር ዓመቱን ትርጉም ሰጥቶት የሚጀምርበት አዉድ ነው። ስለሆነም መላዉ የኦሮሚያ ክልል ህዝብ፣ በሀገር ውስጥ እና በተለያዩ ክፍለ ዓለማት የምትኖሩ ኢትዮጵያዊያን እና ትዉልደ ኢትዮጵያዊያን እንኳን ለ2015 አዲስ ዓመት በሰላም አደረሳችሁ ለማለት እወዳለሁ።
2014 ዓ.ም በበርካታ ተግዳሮቶች፣ድሎች እና ዕድሎች ታጀቦ ያለፈ ዓመት መሆኑ የቅርብ ትዝታችን ነው። በተለይ ደግሞ በወጭ ኃይሎች ላኪነትና በሀገር ዉስጥ ተላለኪ ባንዳዎች የተቀናጀ ሀገርን የማፋረስ ሴራ የተፈተንበት የተግዳሮት ዓመት ነበር። በተለይም ቀደም ሲል ከፋፋይ በሆነዉ የአሸባሪዉ ህውሃት የፖለቲካ ሸር ለዘመናት በአብሮነት ያኖረንን መልካም እሴቶቻችንን በአዳዲስ የሴራ ትርክት እና ዲሪቶ ለመናድ ከፍተኛ ጥረት የተደረገ ዓመት ሆኖ ነበር ያለፈው። ከዚሁ ሴራ ጋረ በተያያዘ የበርካታ ዜጎቻችን ዉድ ህይወት ያጣንበት፣ ከፍተኛ ማህበራዊና ሰብአዊ፣ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ ቀዉስን የተጋፈጥንበት አሳዛኝ ክስተቶችን አስተናግደናል፡፡ ምንም እንኳ ዓመቱ ፈታኝ የነበረ ቢሆንም መሠረተ ባለው የተሰናሰለ ዘመን ተሻጋር የሕዝቦች አንድነት ላይ የተጋመደዉንየአብሮነት እሴቶቻችንን ለመሸርሸር የተደረገው ሙከራ ሊከሽፍ ችሏል። የሀይማኖትና የብሔር ልዩነቶቻችን ህብር የሆነ የዉበታችን ምንጭ ከመሆን አልፎ ለጠላት አሳልፎ ሊሰጠን የማይችል ልዪነት አለመሆኑን በፅኑ አምነን በጋራ በመቆማችን የጠላቶቻችን የጥፋት ድግስ በተለሙት ልክ ሊሳካላቸዉ አልቻለም።
እነሆ ዛሬም ቢሆን በሴራ ተፈጥሮ በዚሁ መንገድ መቀመቅ እየወረደ ያለዉ የሕዝቦች አንድነትን ለመናድ አሁንም አሸባሪዉ ህወሃት ለሦስተኛ ግዜ ጦርነት ከፍቶብናል። ይሁን እንጂ ይህ ጦርነት የጁንታው ለመጨረሻ ጊዜ መቀበሪያ እና የሀገር ህልዉናን ማስጠበቂያ፣ የህዝባችን አንድነት ማጽኛ፣ የአብሮነትና የሀገር ክብር እና ሉዓላዊነት የበለጠ በመጉላት እና አብሮ በመዋደቅ እንደ ትላንት ጥንታዊነታችንን እንደ ዛሬ ደግሞ ዘመናዊያን መሆናችንን በማሳየት እሴቶቻችንን እና አብሮነታችንን የሚናሰቀጥልበት አዲስ ምዕራፍ ነው።ይህን ብዘሃነታችንን እንደ መልካም ዕድል በመጠቀም ሀገርን የማፍረስ ሴራን የወጠኑ ጠላቶቻችን የሄዱበት የጥፋት መንገድ አይሳካላቸዉም፡፡
ዛሬም በእርግጥ ጠላቶቻችን በተላላኪዎቻቸዉ በኩል በዘረጉት የሴራ መረብ ኢኮኖሚዉን በአሻጥር በማዳከም ህዝብ በኑሮ ውድነት ተማሮ በመንግሥት እና በሃገሩ ላይ ተስፋ እንዲቆርጥ ለማድረግ ያደረጉት ፈተና ቀላል አልነበረም። በተጨባጭ ዕይታ ያለዉ የኑሮ ዉድነቱ መሠረታዊ ለዉጥ ያልመጣበት የዓለም አቀፍ ሁኔታ ተፅኖ የታከለበት ጭምር ቢሆንም፣ ከዚህ ቀደም እምብዛም ባልተለመደ መልኩ በበጋ የመስኖ ስንዴን በስፋት በማምረት፣ የኢኮኖሚ ሴራ መደበቅያ የሆነዉን የንግድ ሰንሰለት ለማሳጠር እና የቁጥጥር ሥርዓት በማጠናከር የተደቀነብንን ከፍተኛ አደጋ ለመቀነስ የተሰራበት ጊዜ ቢሆንም ከፈተናዉ ግን አሁንም ያለተላቀቅንበት ዓመት ሆኖ ነበር ያለፈው።
2014 ከተግዳሮቱ ባሻገር አነጋጋሪ እና አኩሪ ብሔራዊ ድሎችን የተጎናፀፍንበት ዘመንም ነበር። በተለይም የህብረብሔራዊነታችን አርማ፣ የፅናትና አይበገሬነታችን ማሳያ፣ የብልፅግናችንና የከፍታ ጉዟችን መወጣጫ ማማ የሆነዉን የታላቁ የህዳሴ ግድብ የሦስተኛውን ዙር የዉሃ ሙሌት በታሳካ ሁኔታ የሞለንበት፣ ሁለተኛዉ የሀይል ማመንጫ ተርባይን የብስራት ብርሃንን ያመነጨበት ታላቅ የድል ዘመን ነበር። በተጨማሪም ‘’እንደ ሀገር ይፈርሳሉ’’ ብለዉ ጠላቶቻችን ሲየሟርቱ ወዳጆቻችን በዚሁ ሥጋት ሲርዱ ከሥኬታማና ፍፁም ዴምክራሲያዊ ከሆነ ምርጫ በኋላ ሁሉንም ተፎካካሪ ፖርቲዎች ያሳተፈና አካታች የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን ጅምር መሠረት በመጣል ታሪካዊ የመንግስት ምስረታን ያካሄድንበት ዘመን ነበር። እንደ ብልፅግና ፓርቲም አካታች ጠቅላላ ጉባዔን በማካሄድ የፓርቲ ውስጠ ዴምክራሲያዊ እምርታን ያሳየንበት ዘመን ነበር።
በአጠቃላይ 2014 ዓ.ም ፈተናዎችን በድል ታጅበን የተሻገርንበት፣ ፈተና ዉስጥ ቆሞ ለድል መፅናትን በይበልጥ የተለማመድንበት፣ የብልፅግናችን ጉዞ በፈተናዎች ብዛት የማይቆም ፅኑ ራዕይ መሆኑን ያረጋገጥንበት እና ኢትዮጵያ በፈተና እና በተንኳሾች ብዛት የምትፈርስ ሳይሆን ይልቁኑ ፈተናዎች ስገጥማት ወረቶችን እንደ ማስፈንጠሪያ በመጠቀም እንደ አለት እየጠነከረች የሚትጓዝ ታሪካዊት ሀገር መሆኗን እኛ ብቻ ሳንሆን ዓለም የመሰከረበት ዘመን ነበር ዓመቱ።
እኛ በየ ቤቶቻችን ሆነን አዲስ አመትን ለመቀበል በምንሰናዳበት በዚህን ስዓት ጀግናዉ የመከላከያ ሠራዊታችን እና መላው የክልላችን የጸጥታ መዋቅር ለሀገራቸዉ ክብርና ህልዉና ሲሉ በየዱር ገደሉ ሀገርን ለማፍረስ ከተነሳዉ ባንዳ ጋር ተናንቀዉ በመዋደቅ ላይ ይገኛሉ። ስለሆነም አዲስ አመቱን ስንቀበል ከምንም በላይ ምታችንን ምቶ ሀገራዊ ክብር፣ ህልዉና እና አንድነታችንን ለማፅናት የሚዋደቀዉን የመከላከያ ሠራዊታችንን እና መላ የጸጥታ መዋቅሩን በማሰብ፣ የሚገባዉን ክብር በመለገሥ እና የተጀመረዉን ህዝባዊ ደጀንነታችንን በማስቀጠል መሆን አለበት። በዚሁ አጋጣሚ ህዝባችን ለጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችን ፈርጀ ብዙ ድጋፎችን በማድረግ የጀመረዉን ጠንካራ ደጀንነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪዬን አስተላልፋለዉ።
ከ2014 ድሎች፣ ተግዳሮቶች ፣ ስኬቶች እና ዕድሎች የተማርነዉን ትምህርት ቀምረን በ2015 ለበለጠ አዳዲስ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትልምች እና ድሎች የምናከናዉንበት ዓመት ይሆናል። ከሁሉ በላይ ህብረ-ብሔራዊነታችንን በፅኑ ወንድማማችነት እና እህትማማችነት ላይ በመገንባት ተጋላጭነታችንን የምንዘጋበት ዓመት ይሆናል፡፡ 2014ን ከልብ በመነጨ ይቅርታና በፍቅር እንሻገር። ዋነኛ ተጋላጭነታችን ድህነት ስለሆነ በ2014 ያስመዘገብናቸውን ኢኮኖሚያዊ እምርታዎችን በማስቀጠል ጉድለቶቻችንን በመሙላት እና ጠማማዎችን በማቅናት ከድህነት ለመዉጣት በቁጭት የምንረባረብ ይሆናል። የተፈጥሮ ፀጋዎቻችንንም አሟጠን ለብልፅግናችን ግብዓት እንጠቀምበታል።
በድጋሚ እንኳን ከ 2014 ዓ.ም ወደ 2015 ዓ.ም ዘመን በሠላም ተሻገርን እያልኩ አዲሱ ዘመን፣ ፍቅር እንጂ ፀብ የማንሰማበት፣ ሞትና መፈናቀል የሚያበቃበት፣ በጀመርነው አገራዊ ዕርቅ የቁርሾዎች ምእራፎች የሚዘጉበት፣ በመላዉ ሀገራችን ሠላም የሚሰፍንበት፣ ጠላቶቻችን ከስመዉ አንድነታችን የሚያይልበት፣ የደስታ፣ የፍሰሃ እና የብልፅግና ዘመን እንዲሆንልን ከልብ እመኛለሁ።
ፍቃዱ ተሰማ
በብልፅግና ፓርቲ የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ፅ/ቤት ሃላፊ
ጳጉሜ 5/2014
ፊንፊኔ

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Eessa turre,Maalirra Geenyeerra? Kutaa 4ffaa