ሁላችንም ሀኪም
እናቶች በእንባ እየታጠቡ ተንበርክከው ለመኑ፤’’እባካችሁ በጡታችን ተለመኑ፣ ወደ ጥፋት አትሂዱ፣እርቅ ፍጠሩ፣ሰላም ለሀገራችን አውርዱ ‘’አሉ-መቀሌ ድረስ ተጉዘው፡፡የሀገር ሽማግሌዎችም ’’በኢትዮጵያዊ የሽምግልና ባህላችን መሰረት ተለመኑን፣ለሀገርና ለህዝብ ሰላም ስትሉ አለመግባባታችሁን በውይይት ፍቱ፣ታረቁ ‘’ በማለት ወገባቸው እየተንቀጠቀጠ ለመኑ፡፡የሀይማኖት አባቶች መጽሐፍ ቅዱስና ቁራን ጨብጠው ፊታቸው በመቆም እርቅና ሰላም እንዲያወርዱ ተማጸኑ፡፡ፌዴራል መንገስትም ሰላም እና እርቅ እንዲወርድ በራሱ የዲፕሎማሲ መስመር መለመኑና ማስለመኑ ተነገረ- ’’ተለማማጭ ‘’ተብሎ እስኪተች ድረስ!!ለዚሀ ሁሉ ልመና የተሰጠው ምላሽ ግን እብሪትና ፉከራ ነበር፡፡የፈረደበትን የትግራይን ህዝብ ልጆች ለጦርነት እሳት በመማገድ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ድል ለማግኘት በማለም ዘቻና ማስፈራሪያው በወታደራዊ ትርኢት ታጅቦ ይቀርብ ጀመር፡፡ሳይውል ሳያድርም ራሳቸውን ሲጠብቅ በኖረው የሰሜን ዕዝ ላይ ክህደት በመፈጸም ጨፈጨፉት-ልክ የዛሬ 2 ዓመት፡፡
ተደጋግሞ እንደሚባለውም ኢትዮጵያ የተአምረኞች አገር ናት፡፡ተአምረኛ ልጆቿ በየዘመናቱ በደም በአጥንታቸው ግብር ያስከበሯት ልጆች እናት ነች፡፡ዛሬም በዚህ ተአምረኛ ትውልድ ሌላ ተአምር ተሰራ!!’’እኔ ካልገዛኋትና ካልዘረፍኳት አፈርሳታለሁ ‘’ብሎ የጥፋት ናዳ ያወረደባትንና በታሪኳ ገጥሟት የማያውቀውን እብሪተኛ በደም ግብር አንበርክከው በታሪኩ አድርጎት የማያውቀውን የሰላም ስምምነት እንዲፈርም አደረጉት፡፡የኢትዮጵያንና የህዝቦቿን አንድነትና ሉአላዊነት ሊያከብር፣ለጥፋት የታጠቀውን የጦር መሳሪያ ፈትቶ ለመከላከያ ሰራዊት ሊያስረክብ፣ታጣቂውን ሊበትን….ተስማምቶ በዓለም ፊት ፈረመ፡፡ይህ ድል በዋናነት የትግራይ ህዝብ ድል መሆኑ የሚያጠራጥር አይደለም፡፡ምክንያት ቢባል በጋሻነት ተይዞ፣የራሱን አገርና የራሱን ወገን በጥላቻ ተመልክቶ እንዲወጋ ተፈርዶበት ልጆቹን ለእሳት ሲማግድ የሰነበተ ነውና!! የተሸነፉት ደግሞ ኢትዮጵያ እንድትፈርስና ህዝቦቿ አርስ በእርስ እንዲፋጁ የእብድ ዱላ ሲያቀብሉ የነበሩ የወስጥና የውጭ ባንዳዎች ናቸው፡፡እርግጥ ነው ይህ ይሆን ዘንድ ኢትዮጵያ ከባድ ዋጋ ከፍላለች፡፡ንጹሀን ያለኃጢአታቸው በመከራ ቁና ተሰፍረዋል፡፡ወደ ቀድሞ ቦታው ለመመለስ ብርቱ ጥረትና ጊዜ የሚጠይቅ በህዝቦቿ መካከል የጥላቻና የዘረኝነት መርዝ ተረጭቷል፡፡በተቃራኒ ወገን የተሰለፉ ኢትዮጵያውያን አንዱ በሌላው ላይ በመተኮስ ከባድ የህይወትና የአካል ጉዳት ደርሷል፡፡በቀላሉ የማይተካ ሀብትና ንብረት ወድሟል፡፡በቀላሉ የማይተኩ መሰረተልማቶች ፈራርሰዋል፡፡ይህ አሳዛኝና ቅስም ሰባሪ ፍጸሜ ነው፡፡ቢሆንም ለኢትዮጵያ ህልውና፣ለህዝቦቿ ሰላምና ልማት ሲባል የተከፈለ ዋጋ ስለሆነ እንጽናናለን፡፡መስዋትንት በመክፈል ኢትዮጵያን አሸናፊ ያደረጓትን ልጆቿን በክብር እንዘክራቸዋለን፡፡
አሁን ትኩረታችን የሰላም ስምምነቱ ሳይዛነፍና በሴራ ሳይጠለፍ ተግባራዊ እንዲሆን በማገዝ ላይ ነው፡፡አሁን ያሸነፈችው ኢትዮጵያ ናት፡፡ከአጠቃላዩ ድል በመውረድ በተራ ‘’የሰላም ስምምነት ተጠቃሚና ተጎጂ ‘’ዝርዝር ሂሳብ ኪሳችንን ሊሞሉ የሚፈልጉ ‘’ጭር ሲል አልወድም ‘’ፖለቲከኞችንና ጦርነትን በሌላ መንገድ ማስቀጠል የሚፈልጉ ጠላቶቻችንን ወሬ ማርከስ አለብን፡፡ከእንግዲህ ቁጭትና ቂምበቀል ወደ ታሪክ መዝገብ ይሂዱ፡፡የኢትዮጵያን አሸናፊነት ወደ ጎጥና መንደር ደረጃ አውርደው ሊነዘንዙን የሚፈልጉና ማህበራዊ እረፍት እንዳናገኝ ሊያደርጉን የሚሯሯጡትን አደብ ማስገዛት አለብን፡፡ከሁሉም በላይ ሁላችንም፣በተለይ ደግሞ ወገናችን የትግራይ ህዝብ በጦርነትና መዘዙ አካላዊና ስነልቦናዊ ጉዳት የደረሰበት ስለሆነ ይህንን ጉዳት ለማከም መጣር ይገባናል፡፡የተአምረኛዋ አገር ልጆች የልማት ተአምር ለመስራት እንነሳ፣ጊዜው ለህመማችን ፈውስ ሁላችንም ሀኪም እንድንሆን ይጠይቃል፡፡ቀጣዩ ጊዜ በብሩህ ተስፋ የተሞላ ነው፡፡ተስፋ ካለ ደግሞ ሁሉም ነገር ይቻላል(Once you choose hope, anything’s possible.)
@ዓለምነው አበበ
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ