ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በተደረሰው ስምምነት ደስታቸውን ገልጸዋል

 



"ሰላም የንግግር መክፈቻ፣ የኑሮ ቅመም፣ የሰው ልጆች ሕይወታዊ ሀብት ነው" ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ

ጥቅምት 24/2015 ዓ.ም
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በተደረሰው ስምምነት ደስታቸውን ገልጸዋል፡፡
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በመልዕክታቸው "ለእርቅና ለሰላም የምሥራች ያደረሰንን አምላክ እናመሰግናለን" ብለዋል፡፡ በሰላም መወለድ፣ በሰላም መኖር፣ በሰላም መሞት የሰው ልጆች የሚሹት ናፍቆት መሆኑንም ፓትርያርኩ ገልጸዋል፡፡
"ሰላም የንግግር መክፈቻ፣ የኑሮ ቅመም፣ የሰው ልጆች ሕይወታዊ ሀብት ነው" ብለዋል፡፡ ሰላም ለዚህች ዓለም አንድ ዓይን መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ ሰላምን አክብሮ መኖር የሰውነት ግዴታ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
መሪ በዙፋኑ፣ ጳጳስ በመንበሩ፣ ዜጋ በሀገሩ፣ ገበሬ በምድሩ የሚኖረው ሰላም ሲሆን ነው ያሉት ቅዱስነታቸው "የእግዚአብሔር ትልቅ በረከትም ሰላም ነው" ሲሉ ገልጸዋል፡፡
"ኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን አሸንፎ በተነሳ ጊዜ የሰበከው ሰላምን ነው" ያሉት ቅዱስነታቸው ሰላም የእኛ ከሆነች ደስታችንና የድካማችን ፍሬ እንበላለንም" ብለዋል፡፡
ጦርነት የሰሙ ጀሮዎቻችን ዛሬ ሰላምንና እርቅን በመስማታቸው ደስታችን ወደር የሌለው መሆኑን ለልጆቻችን እንገልጻለንም ነው ያሉት፡፡
ኢትዮጵያን ከአስከፊ የጦርነት ታሪክ ለማውጣት፣ እግዚአብሔር በሰጣት መልካም ዕድል፣ የተፈጥሮና የሃይማኖት ሃብት እንድታድግ ሰላምን መናፈቅና የሰላም መልዕክተኞች መሆን እንደሚያስፈልግም አሳስበዋል፡፡
ሐሳብ የበላይ ሲሆን የጦር መሳሪያ የእርሻ መሣሪያ ወደ መሆን ይለወጣል ነው ያሉት፡፡
በተሰማው መልካም የምሥራች መደሰታቸውንም ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን በሙሉ ሀገሩ የሁላችን ነውና ልንጠብቀው፣ አለመግባባታችንን በውይይት ልንፈታው፣ ቃላችንን ከመሬት ላይ አሳርፈን እርቁን እውነተኛ ልናደርገው ይገባልም ብለዋል፡፡
ወጣቶች ሲሞቱ ሳይሆን ተምረው ሲመረቁ፣ ተዋድደው ጋብቻ ሲመሰርቱ ለማየት እንናፍቃለን ያሉት ቅዱስነታቸው የተዘጉ ደጆች ሁሉ በምሕረት እንዲከፈቱ፣ የተጨነቁ ሁሉ ፀሐይ እንዲወጣላቸው በብርቱ እንሻለን ነው ያሉት፡፡
ለሰላም ለደከሙትን ሁሉ ቅዱስነታቸው ምሥጋና ማቅረባቸውን ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መገናኛ ብዙኃን አገልግሎት የተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Eessa turre,Maalirra Geenyeerra? Kutaa 4ffaa