ለአማራ ህዝብ ችግር ብዙ አክተሮችን ተጠያቂ ማድረግ እንዳለ ሆኖ ዋናው ችግር ከአብራኩ የወጡ አቀንጭራዎች ናቸው


ባልሆነው ኦሮሙማ እያሉ ማላዘን ትግል አይደለም። ኦሮሙማ የምትለውን ማስፈራሪያ ለግልህ ፍራው። በተለይ በወልቃይት እና ራያ ጉዳይ ኦሮሙማን እንደ መስፈራርቾ ልታመጣው አትችልም። የሰሜኑ ጦርነት ኦሮሙማ ሁለቱን የሰሜን ህዝቦች ለማጠፋፋት የጠነሰሰው ግጭት አድርገህ የምትተነትን ተንታኝ፣ ትን ብሎህ አለመሞትህ የፈጣሪ ድንቅ ስራ መሆን አለበት። ወያኔ በጥጋብ እና በእብሪት የሰሜን እዝን አጥቅቶ የጀመረው ጦርነት ፍጻሜው ቀበቶውን ፈቶ፣ መሬት ልሶ ታረቁኝ እንዲል ሆኗል። አዝናለሁ ምንም ማድረግ አልችልም። የሚታደገው ኃይል ካለ ሊሞክርለት ይችላል። ሐቁ ግን ይኸው ነው። ይኸንን ሐቅ ደግሞ እንመሰክራለን...!
ይህን ጦርነት ቀጥ ብሎ የተዋጋው አንተ ጭራቅ አድርገህ ለመሳል የምትሞክረው ኦሮሞ ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር ሆኖ ነው። አንተ ጀግና ብለህ ምስሉን ግድግዳህ ላይ የሰቀልከው አውደልዳይ አንድ ጥይት አልተኮሰም። የክላሽ እና የዲሽቃ ድምፅ መለየት አይችልም። እንዲያው ዝም ስለተባለ ብቻ ሜዳውን ለብቻ ልፏልበት ማለት ነውር ነው። በአንጻሩ አንተ እርኩስ የምታደርገው የኦሮሞ ልጅ ለእናት ሐገሩ በክብር ተፋልሟል። ቆስሏል፣ ደምቷል፣ ተሰውቷል። ይህንን እውነት ባልመሰክር በመንዝ ሸንተረር፣ በአጣዬ ሸለቆ፣ በካሳጊታ ንዳድ፣ በሚሌ በረሃ ወድቀው የቀሩ የኦሮሞ ልጆች አጥንት ይወጋኛል። በደብረታቦር፣ በክምር ድንጋይ፣ በጋሳይ፣ በጉና፣ በወለላ ባህር፣ በደብረዘቢጥ፣ በጋሸና፣ በዳውንት፣ በቀበሮ መስክ፣ በሙጃ፣ በድልብ፣ በድብኮ፣ በጋዝጊብላ፣ በአበርገሌ፣ በወልድያ፣ በመርሳ፣ በኩታበር፣ በቢስትማ፣ በኃይቅ፣ በሲሪንቃ፣ በቆቦ፣ በጎብዬ፣ በተኩለሽ፣ በግራ ካሶ ተራራ የአሞራ ቀለብ ሆነው የቀሩ የኦሮሞ ልጆች አጥንት ይኮሰኩሰኛል።
በወቅን፣ በብና ሜዳ፣ በድብ ባህር፣ በዛሪማ፣ በጨው በር፣ በቦዛ፣ የወደቁ የሐገሬ ልጆች ከእናት ሐገራቸው ዘብ መሆን ውጭ ሌላ ምን ዓላማ እንግበው ነው ልትለኝ ትችላለህ። ይህንን ሐቅ እኔ የቆምኩት ካልመሰከርኩላቸው ማን ሊመሰክር ይችላል። በአዋጊነት ትላለህ በተዋጊነት፣ በስንቅ ማቀበል ትላለህ በዲፕሎማሲ የኦሮሞ ልጆች የሰሜኑን ጦርነት ቀጥ ብለው እንደሌላው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ተዋግተዋል። በዚህ ጦርነት ውስጥ ሴራ የጎነጎኑ የኦሮሞ ልጆች አልነበሩም አልወጣኝም። በደንብ አሉ። ቁጥራቸው የአንድ እጅህን ጣቶች አጥፈህ ሳትጨርስ ያልቁብሃል። በጦርነቱ ለወያኔ ፌቨር ያደረጉ የአማራ፣ የአፋር፣ የሶማሌ ልጆች እንዳሉ ሁሉ የኦሮሞ ልጆችም እንደዛው አድርገዋል። ህዝቡን መወከል ቀርቶ አያውቁትም። እነዚህ የእናት ጡት ነካሽ ባንዳዎች ግን ከወያኔ እኩል ተሸንፈዋል።
አስር የማይሞሉ ባልጌ ኦሮሞዎች በሚያደርጉት ያልተገባ ነገር ጨዋውን ኦሮሞ ሲዘረጥጡ መዋል ግን ብልግና ነው ብዬ እነግርሃለሁ። ጥቂት የኦሮሞ ልጆች በዘሩት ጥላቻ ብዙ መከራ ደርሷል። አንተ ዛሬ ስትዘራው የምትውለው ጥላቻ ነገ በእግሩ ቀጥ ብሎ እንደሚሄድ ግን አታውቅምን። በእርግጥ እነዚህን አስር (አስር ሺህ እንኳን ቢሆኑ ቁጥራቸው አያስጨንቅም) የማይሞሉ ባልጌ የኦሮሞ ልጆችን እንታገላቸዋለን። አንተንም አብረን እንታገልሃለሁ። ባልጌ ብሄሩ ስለተለወጠ ጨዋ ሊሆን አይችልምና። ባልጌ ያው ባልጌ ነው። የእኔ ብሔረሰብ ባልጌ ከአንተ ብሔረሰብ ባልጌ የተሻለ ነው ብሎ ክርክር የለም።
ለዚህች ሐገር ትልቁ ነቀርሳ ወያኔ ነው። ሌላው ትንንሽ ነቀርሳ ከወያኔ በኋላ አንድ በአንድ ይነቀላል። የሚሻለው ተባብሮ መስራት፣ ተከባብሮ መኖር፣ የህዝብን ችግር ማቃለል ነው። የህዝብ ችግር ማቃለል ሲገባ የህዝብን ችግር በውብ ቃላት አጊያጊጦ መናገር እንደ ፖለቲካ እውቀት እየተወሰደ ነው። በተለይ በእኛ ዘንዳ እንደ ገዥ እውነት ሆኗል። ይህን ክፉ አመል በጊዜ መግራት ይበጃል። በእንቁላሉ ጊዜ ራስን መቅጣት የተገባ ነው። በእንቁላሉ ጊዜ ራስህን ካልቀጣህ በሬ የሚያክል ችግር አናትህ ላይ ተከምሮ ታገኘዋለህ።
በመጨረሻም ለአማራ ህዝብ ችግር ብዙ አክተሮችን ተጠያቂ ማድረግ እንዳለ ሆኖ አሁን ላይ ግን ዋናው ችግር ከአብራኩ የወጡ አቀንጭራዎች ናቸው። ክልሉ ተረጋግቶ እንዳይሰራ በማዋከብ፣ ሚስጢር አሳልፎ በመስጠት፣ በሚድያ ጋጋታ እና ሁካታ የሰከነ አመራር እንዳይሰጥ በመናጥ እየረበሹ ያሉት የራሱ ልጆች ናቸው። መጀመሪያ የቤትህን አመል ቤትህ ውስጥ ሳትጨርስ ወደ ጎረቤት ማንጋጠጥ አግባብ አይደለም። ጣታችን ሌላው ላይ ከመቀሰራችን በፊት የራሳችን ችግር እንፍታ የመልዕክቴ አንኳር ነው

 በጋሻው መርሻ ተፃፈ

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Obbo Muktaar Kadir pireezidaantii Mootummaa Naannoo Oromiyaa ta’uun lammata filataman