አቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ በ26 የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የሥራ ኃላፊዎችና ሰራተኞች ላይ ክስ ተመሰረተ

ፊንፊኔ ሚያዝያ 29/2011(ቶለዋቅ ዋሪ)አቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ በ26 የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የሥራ ኃላፊዎችና ሰራተኞች ላይ ክስ ተመሰረተ።
የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ እንዳስታወቀው፥ አቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ በ26 የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የሥራ ኃላፊዎችና ሰራተኞች ላይ በጠቅላላው 46 ክሶች ናቸው የተመሰረቱት።
በክሶቹ ውስጥ 22ቱ ተከሳሾች በአሁኑ ወቅት በእስር ላይ የሚገኙ ሲሆን፥ በሌላ በኩል የቀድሞ የአገልግሎቱን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጌታቸው አሰፋን ጨምሮ አቶ አጽብሃ ግደይ፣ አቶ አሠፋ በላይ እና አቶ ሽሻይ ልዑል በተባሉ የቀድሞ የአገልግሎቱ የሥራ ኃላፊዎች ላይ በሌሉበት ክስ ዛሬ ሚያዚያ 29 ቀን 2011 ዓ.ም በከፍተኛ ፍርድ ቤት ልዴታ ምድብ ችሎት ይመሰረትባችዋል።
በአቶ ጌታቸው ላይ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32/1/ (ሀ) (ለ) እና 407/1/ (ለ) (ሐ) እና 407/3/ ላይ የተደነገገውን በመተላለፍ ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል መፈጸም እንዲሁም በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 (1) ሀ እና ለ እንዲሁም የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9 /1/ (ለ) እና (ሐ) እና 9/3/ ላይ የተደነገገውን በመተላለፍ ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል በሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።
በሌሎቹ ሁሉም ተከሳሾች ላይ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32/1/ (ሀ) (ለ) እና 407/1/ (ለ) (ሐ) እና 407/2/ ላይ የተደነገገውን በመተላለፍ ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል መፈጸም እንዲሁም በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 32 (1) ሀ እና ለ እንዲሁም የሙስና ወንጀሎችን ለመደንገግ የወጣውን አዋጅ ቁጥር 881/2007 አንቀጽ 9 /1/ (ለ) እና (ሐ) እና 9/2/ ላይ የተደነገገውን በመተላለፍ ስልጣንን ያለአግባብ መገልገል ከባድ የሙስና ወንጀል ፈጽመዋል በሚል ክስ ተመስርቶባቸዋል።
ሥልጣንን ያለአግባብ መገልገል ክስ ሊቀርብባቸው የቻለው ተከሳሾች በግልጽ ከተሰጣቸው ሥልጣን ወይም ኃላፊነት አሳልፈው በመስራት እንዲሁም ሥልጣናቸው ወይም ኃላፊነታቸው የማይፈቅድላቸውን በተለይም ሥልጣን ወይም ኃላፊነት ሳይኖራቸው በሌላ ሰው መብት ላይ ጉዳት እንዲደርስ በማሰብ በተበዳዮች ላይ ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመፈጸማቸው ነው።
በአቶ ጌታቸው ላይ በንዑስ አንቀጽ 3 መሰረት ክስ ሊቀርብባቸው የቻለው
1ኛ) በሚኒስትር ማዕረግ የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር ጀነራል የነበሩ በመሆናቸው የኃላፊነት ወይም የሥልጣን ደረጃቸው ከፍተኛ በመሆኑ
2ኛ) ኃላፊነታቸውን የጣሱበት ዓላማ ከባድ በመሆኑ እንዲሁም
3ኛ) በሕዝቦች ወይም በተጎጂዎች ላይ የደረሰው ጉዳት ከባድ በመሆኑ የተፈፀመውን ወንጀል ከባድ ሊያደርገው በመቻሉ ነው።
ቀሪዎቹ ተከሳሾች በሙሉ በንዑስ አንቀጽ 2 መሰረት ክስ ሊቀርብባቸው የቻለው ከላይ ለአቶ ጌታቸው ወንጀል ከባድነት ከተጠቀሱት ምክንያቶች ውስጥ ቢያንስ አንዱ ተሟልቶ በመገኘቱ ነው።
አቶ ጌታቸውን ጨምሮ በአራቱ ተከሳሾች ላይ በሌሉበት ክስ ሊመሰረት የቻለው ደግሞ ተከሳሾች የቀረቡባቸው ክሶች ከባድ በመሆናቸው በህጉ መሰረት በሌሉበት ክስ ሊቀርብባቸው የሚገባ ስለመሆኑም ከኢፌዴሪ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ከባድ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽመዋል በሚል በፌደራል ፖሊስ ወንጀል መርማሪዎች ላይ፤ በማረሚያ ቤት የሥራ ኃላፊዎች ላይ እንዲሁም በብሔራው መረጃና ደህንነት አገልግሎት የሥራ ኃላፊዎች ላይ ሲካሔድ የነበረው የወንጀል ምርመራ ሲካሔድ መቆየቱ ይታወሳል።
በዚሁ መሰረት ዓቃቤ ሕግ በወንጀል መርማሪዎች ላይ፤ በማረሚያ ቤቱ የሥራ ኃላፊዎች ላይ እንዲሁም በብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የስራ ኃላፊዎችና ሰራተኞች ላይ በሶስት የተለያዩ መዝገቦች ክስ ተመስርቷል።
በመርማሪዎች ላይ በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የተከፈተው እና በማረሚያ ቤት ኃላፊዎች በነበሩት ላይ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተከፈቱት መዛግብት የከስ ሂደቱ ቀጥሎ ምስክር ለመስማት መቀጠራቸውም ይታወቃል።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Obbo Muktaar Kadir pireezidaantii Mootummaa Naannoo Oromiyaa ta’uun lammata filataman