የኢቢሲ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ከኃላፊነታቸው ለቀቁ

ነባሩን የሕወሓት አመራር አባል አቶ ብርሃነ ኪዳነ ማርያምን ከሁለት ዓመት በፊት በመተካት የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሸን (ኢቢሲ) ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ሥዩም መኮንን፣ ማክሰኞ ግንቦት 13 ቀን 2011 ዓ.ም. ከኃላፊነታቸው መልቀቃቸውን ለሠራተኞች አስታወቁ፡፡

አቶ ሥዩም ከኃላፊነታቸው መልቀቃቸውን ያሳወቁት የኮርፖሬሸኑን የዘጠኝ ወራት የሥራ አፈጻጸም አስመልክቶ፣ በኢትዮጵያ ሆቴል ከሠራተኞች ጋር ውይይት ካደረጉ በኋላ ነው፡፡ ከኃላፊነታቸው መልቀቃቸውን ሲገልጹ የስብሰባው ተሳታፊ የነበሩ ሠራተኞች በከፍተኛ ጭብጨባ የድጋፍ ይሁን ወይም የተቃውሞ ባይታወቅም ስሜታቸውን መግለጻቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
አቶ ሥዩም ከተሾሙበት ወርኃ ነሐሴ መጨረሻ 2008 ዓ.ም. ጀምሮ ኮርፖሬሽኑን በዋና ሥራ አስፈጻሚነት ሲመሩ የተለያዩ ለውጦችን ማምጣታቸው ቢወሳም፣ በሌላ በኩል ደግሞ ተቃውሞዎች እንደነበሩባቸው ይነገራል፡፡
እሳቸው በሚዲያው ዘርፍ የተሻለ ዕውቀት ያላቸው መሆናቸውን አብረዋቸው የሠሩ ይመሰክሩላቸዋል፡፡ የአማራ መገናኛ ብዙኃን ቢሮ ኃላፊ፣ እንዲሁም በአማራ ክልል የደቡብ ወሎ ዞን አስተዳዳሪ ሆነው ሠርተዋል፡፡ ከጥቂት ጊዜ ወዲህ አቶ ሥዩም በሥራቸው ላይ ተፅዕኖ እንደሚደርስባቸው በሚያስታውቅ ሁኔታ አባል ለሆኑበት የፖለቲካ ድርጅት የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ)፣ ከኃላፊነታቸው ለመልቀቅ በተለያዩ ጊዜያት ጥያቄ ማቅረባቸውን ምንጮች ይናገራሉ፡፡
ነገር ግን አቶ ሥዩም በፖለቲካ ድርጅታቸው ወይም በሌላ አካል ግፊት ይሁን ባይታወቅም፣ እስከ ግንቦት 13 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ ሲመሩት የቆዩትን ኢቢሲ ኃላፊነት መልቀቃቸውን ያሳወቁ ቢሆንም፣ ዝርዝር ምክንያታቸውን ግን ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት በ1994 ዓ.ም. ያገኙት አቶ ሥዩም፣ ሁለተኛ ዲግሪያቸውን ደግሞ አሜሪካ ከሚገኝ ዩኒቨርሲቲ አግኝተዋል፡፡
ኢቢሲ በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዳዲስ የቦርድ አባላት ሲመደቡለት፣ ቦርዱን በኃላፊነት እንዲመሩ የተመረጡት የኦሮሞ ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኦዴፓ) ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ፍቃዱ ተሰማ መሆናቸው ይታወሳል፡፡
አቶ ሥዩምን ከኃላፊነታቸው የለቀቁበትን ምክንያት ለማወቅ ሪፖርተር ጥረት ቢያደርግም፣ ኅትመት እስከሚገባ ድረስ ስልካቸው ዝግ በመሆኑ ማግኘት አልተቻለም፡፡

Source:Reporter

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Obbo Muktaar Kadir pireezidaantii Mootummaa Naannoo Oromiyaa ta’uun lammata filataman