በስህተት ከባንክ የተሰጣቸውን 1 ሚሊየን ብር የመለሱት መምህር:


አቶ ዓለሙ ተስፋዬ (ዶ/ር) ባህርዳር በሚገኘው የአቢሲኒያ ባንክ በተንቀሳቃሽ ደብተራቸው የገባውን ገንዘብ ለማውጣት በጣና ቅርንጫፍ የተገኙት ሚያዝያ 29 ቀን 2011 ዓ. ም. ነበር።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን፤ ማኅበረ ቅዱሳን በሚያስተባብረውና አቶ ዓለሙ በሚሳተፉበት ፕሮግራም የአብነት ትምህርት ቤቶችና ገዳማትን ለማደራጀት የተሰበሰበ አንድ ሚሊየን ሁለት መቶ ሦስት ሺ ብር በስማቸው ገብቶ ነበር።

በገበያ አካባቢ በሚገኘውና የሥራ ጫና በሚበዛበት የጣና ቅርንጫፍ ያሉ ሠራተኞች የተለመደ የዕለት ከዕለት ሥራቸውን በማከናወን ላይ ሳሉ አቶ ዓለሙ ከፍጠኛ መጠን ያለው ገንዘብ ለማውጣት መጠየቃቸውን የጣና ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ቢራራ መላኩ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ደንበኛው የጠየቁት የገንዘብ መጠን አንድ ሚሊየን ሁለት መቶ ሦስት ሺ ብር ነበር። አቶ ቢራራ እንደሚሉት፤ የገንዘቡ መጠን ከፍ ያለ ስለነበረ ፊትለፊት የነበረው ገንዘብ ከፋይ ለደንበኛው 3000 ብሩን ብቻ እንዲሰጣቸው ተደርጎ፤ ቀሪውን 1.2 ሚሊየን ብር ወደ ውስጥ ገብተው እንዲወስዱ ተደርጓል።

''ወደ ውስጥ ከገቡ በኋላ ብሩን አብረን ቆጥረን እንዲረከቡ አደረግን። ደንበኛው ከጠየቁት አንድ ሚሊየን ብር ጭማሪ ተሰጥቷቸው ገንዘቡን ገቢ ወደሚያደርጉበት ቦታ ሄዱ።''

አቶ ቢራራ እንደሚሉት፤ ለአቶ ዓለሙ አንድ ሚሊየን ብር ተጨማሪ መሰጠቱንና ከባንኩ ብር መጉደሉን አላወቁም ነበር። አቶ ዓለሙ በስህተት የተሰጣቸውን ገንዘብ በጆንያ ጭነው እስከተመለሱበት ጊዜ ድረስ ምንም እንዳልጠረጠሩ ያስረዳሉ።

የተፈጠረውን ነገር "እጅግ አስገራሚ'' ሲሉም ይገልጹታል።

''ደንበኛው በመጀመሪያ ገንዘቡን ይዘው ሲመለሱ ትርፍ ብር ሊመልሱልን እንደሆነ አላወቅኩም ነበር። ሀሳባቸውን ቀይረው ብሩን ገቢ ሊያደርጉት እንደሆነ ነበር ያሰብነው።''

አቶ ዓለሙ ግን የራሳቸውን ገንዘብ ገቢ ሊያደርጉ ሳይሆን ባንኩ በስህተት የሰጣቸውን ተጨማሪ አንድ ሚሊየን ብር ሊመልሱ ነበር ወደ ቅርንጫፉ የተመለሱት።

በባህርዳር ዩኒቨርሲቲ የኬሚስትሪ ትምህርት ክፍል ኃላፊ የሆኑት አቶ ዓለሙ ተስፋዬ፤ ''ወደ ውስጥ ከገባን በኋላ ብሩ ሲቆጠር አጠገቡ ቁጭ ብዬ ስለነበር መጠኑ ትክክል መሆኑን እያረጋገጥኩ ወደ ጆንያ ውስጥ አስገባ ነበር'' ሲሉ ይናገራሉ።

አቶ ዓለሙ ብሩን ከተረከቡ በኋላ አብሯቸው ከነበረ ግለሰብ ጋር ለሥራ ማስኬጃ ብሩን ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ገቢ ለማድረግ ተንቀሳቀሱ።

ንግድ ባንክ ሲደርሱ ግን ፈጽሞ ያልጠበቁት ነገር አጋጠማቸው። የባንኩ ሠራተኛ ብሩን እንደተመለከተው ከመቁጠሩ በፊት "2.2 ሚሊየን ነው አይደል?" ብሎ ጠየቃቸው።

''እንደዛ ብሎ ሲጠይቀን፤ የብሩ መጠን 1.2 ሚሊየን ነው ብለን መለስንለት። ብሩን አብረነው በድጋሚ ስንቆጥረው እውነትም 2.2 ሚሊየን ብር ሆኖ አገኘነው'' በማለት አቶ ዓለሙ ስለሁኔታው ያስረዳሉ።

''የራሳችን የሆነውን 1. 2 ሚሊየን ብር ገቢ ካደረግን በኋላ ቀሪውን ብር ለመመለስ ወደ አቢሲኒያ ባንክ ጣና ቅርንጫፍ ተመለስን''

የባንኩ ሥራ አስኪያጅ የቀን ገቢ ሂሳብ የሚሠራበት ሰአት ባለመድረሱ ገንዘቡ መጉደሉን እንዳላወቁ ይናገራሉ። ''ብሩ ይጉደል አይጉደል ለማወቅ ሂሳብ መዝጋት ነበረብን'' ይላሉ።

አቶ ቢራራ እንደሚሉት፤ አቶ ዓለሙ ብር በስህተት ሰጥታችሁኛልና ልመልስ ሲሏቸው፤ በመጀመሪያ ነገሩ ቀልድ መስሏቸው ነበር። ኋላ ላይ ነገሩ እውነት ሆኖ ሲገኝ ግን ግርምትም ድንጋጤም እንደፈጠረባቸው ይናገራሉ።

አቶ ዓለሙ ገንዘቡን ባይመልሱ ምን ይፈጠር ነበር? የሚል ጥያቄ ያቀረብንላቸው አቶ ቢራራ፤ የሥነ ምግባር እርምጃዎች ሊያስከትል ይችል ነበር ይላሉ።

''ስህተቱ በሥራ ጫና ምክንያት ወይም ባለማወቅ የተፈጠረ እንደሆነ በምንም አይነት መንገድ ማረጋገጥ ስለማይቻል ሆነ ተብሎ እንደተፈጸመ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።''

ደንበኛው የሰሩት ስህተት ባለመኖሩና ባንኩ ክፍያ ፈጽሞላቸው ወደጉዳያቸው ስለሄዱ ገንዘቡን ለመመለስ የሚያስገድዳቸው የሕግ አሰራር አልነበረም።

''የአቶ ዓለሙን ስብዕና በቃላት ለመግለጽ እጅግ ከባድ ነው፤ ከህሊና በላይ ነው፤ ፈጣሪ በላባቸው ሠርተው ያገኙትን ገንዘባቸውንና ትዳራቸውን እንዲባርክላቸው እመኝላቸዋለሁ'' ብለዋል አቶ ቢራራ።

አቶ ቢራራ "ይህ ለትውልድ አርአያ የሚሆን ተግባር ነው። እድሜ ልካቸውን ሊኮሩበት የሚገባ ተግባር ነው። እኔም ብሆን እድሜ ዘመኔን በሙሉ አስታውሰዋለሁ። የመልካም ሥራ አርአያ አድርጌ የማስታውሳቸው ሰው ይሆናሉ'' በማለት የተሰማቸውን ደስታ በመግለጽ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

አቶ ዓለሙ በበኩላቸው፤ ተግባሩ ብዙ ሰዎች ሊያደርጉት የሚችሉት ነው በማለት፤ የባንኩን ሠራተኛ ከብዙ እንግልት በማዳናቸው ደስተኛ እንደሆኑና የህሊና እርካታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል።

Via #BBC

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Eessa turre,Maalirra Geenyeerra? Kutaa 4ffaa