ባለሀብትና ቤተሰቦቻቸው የእስራት ቅጣት ተወሰነባቸው

ፍርድ ቤት በመድፈር ወንጀል የታሰሩት ባለሀብትና ቤተሰቦቻቸው የእስራት ቅጣት ተወሰነባቸው

ቅጣት የተጣለባቸው ዶ/ር በዕውቀቱ ታደሰ፣ ወ/ሮ መሠረት በረደድ፣ ወ/ሮ ጥሩወርቅ በረደድ፣ አቶ ቴዎድሮስ በረደድ፣ አቶ ጊጋር በረደድና ወ/ሮ እናና መንግሥቴ ናቸው፡፡
ጥፋተኛ ሆነው የተገኙት ግለሰቦች ቅጣቱ የተጣለባቸው ዶ/ር በዕውቀቱ፣ አቶ ጌታቸው እሸቱ (ኢንጂነር) ከሚባሉ ግለሰብ ጋር በነበራቸው ክርክር በሰበር ሰሚው ችሎት ተሰይመው የመጨረሻ ውሳኔ የሰጡ ዳኞች ወደ ጽሕፈት ቤታቸው ሲመለሱ፣ ዶ/ር በዕውቀቱና ወ/ሮ መሠረት የተባሉት ግለሰቦች ‹‹እናንተ ሌቦች፣ በጉቦ ነው የወሰናችሁት›› በማለት መሳደባቸውን የቅጣት ውሳኔው ያሳያል፡፡ ሌሎቹ አራት ግለሰቦች ‹‹እውነት ነው ሌቦች ናችሁ›› በማለት ሁለቱን ተሳዳቢዎች በመደገፍ፣ የፍርድ ቤቱ ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች፣ ባለ ጉዳዮችና የችሎቱ ዳኞች በሚመለከቱበትና በሚሰሙበት ሁኔታ የችሎቱን ዳኞችና የፍርድ ቤቱን ክብር ማዋረዳቸውንም ውሳኔው ይገልጻል፡፡ የአገሪቱን የመጨረሻ ፍርድ ቤት በእጅጉ በሚያንጓጥጥና የችሎቱን ዳኞች ሞራል በሚነካ ሁኔታ፣ እንዲሁም የፍርድ ቤቱ ተገልጋይ ማኅበረሰብ በፍርድ ቤቶች ላይ እምነት እንዳይኖራቸውና በዳኞች ላይም ጥርጣሬ እንዲፈጠር ለማድረግ በማሰብ መሳደባቸውንም አክሏል፡፡
ዶ/ር በዕውቀቱና ወ/ሮ መሠረት የተባሉት ግለሰቦች በተደጋጋሚ መሳደባቸውን የተመለከቱ ዳኞች ከፍርድ ቤቱ ግቢ እንዳይወጡ ፌዴራል ፖሊስ እንዲያቆያቸው ትዕዛዝ በሚሰጡበት ጊዜ፣ ከተሳደቡት በተጨማሪ ‹‹እናንተ ሌቦች በጉቦ ነው የወሰናችሁት›› በማለት ትዕዛዝ ወደ ሰጡት ዳኞች ሕንፃ ለመውጣት ሲሞክሩ በግቢው ውስጥ ያሉ የፌዴራል ፖሊሶች ማስቆማቸውንም የቅጣት ውሳኔው ያስረዳል፡፡
 ችሎቱ ተሰይሞ ትዕዛዝ ሲሰጥ በተለይ ዶ/ር በዕውቀቱ ከአንድ የተማረና ራሱን ከገዛ ሰው በማይጠበቅ ሁኔታ ‹‹ታስሩኛላችሁ እንጂ አትገድሉኝም፣ አልሞትም ምንም አታመጡም፤›› በማለት በፖሊሶች ፊት የችሎቱን ክብር በእጅጉ በሚጎዳ ሁኔታ ማንጓጠጣቸውንና አልታዘዝም ባይነታቸውን በግልጽ ያሳዩ በመሆናቸው ችሎት መድፈራቸውን የቅጣት ውሳኔው ያሳያል፡፡ ችሎቱ፣ ‹‹ችሎት መድፈር ምን ማለት ነው?›› የሚለውን በወንጀል ሕግ አንቀጽ 449(1) ላይ በግልጽ ሰፍሮ እንደሚገኝና ተግባሩ በተፈጸመ ጊዜ ችሎቱ ወዲያውኑ ቅጣት እንዲወስንም ጠቁሟል፡፡
ፍርድ ቤቱን ለማስከበርም በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 480 ድንጋጌ ላይ ሥልጣን መሰጠቱንም አክሏል፡፡ በዚሁ መሠረት የፍርድ ቤት ችሎት ሰብሳቢ ዳኛ ለችሎቱ ክብር ወይም ለዳኝነቱ ሥነ ሥርዓት መልካም አሠራር ተቃራኒ የሆነ ጠባይ የሚያሳየውን ማናቸውንም ተከራካሪ ወገን ወይም ጠበቃ በያዘው መዝገብ ላይ የገንዘብ መቀጮ ሊወስንበት፣ ወይም ማናቸውንም አስፈላጊ መስሎ የታየውን ዕርምጃ ሊወሰድበት እንደሚችል ድንጋጌው ይፈቅዳል፡፡ በሥነ ሥርዓት ሕጉ 481 ሥር ደግሞ የትኛውም ፍርድ ቤት የእስር ቅጣት መቅጣት እንደሚችልም የቅጣት ውሳኔው ያብራራል፡፡

ከላይ ስማቸው የተጠቀሱት ግለሰቦችም ሕጉ የሚደነግገውን ክልከላ ተላልፈው የፍርድ ቤቱንና ዳኞችን ክብር በማዋረድ፣ የሕግ የበላይነትን በማንኳሰስ ችሎት የመድፈር ወንጀል መፈጸማቸውን አክሏል፡፡
ግለሰቦቹ ፍርድ ቤቱ ያቀረበውን ጉዳይ መርምሮ በሕግ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት ውሳኔ ካሳለፈ በኋላ ውሳኔውን አለመቀበልና መተቸት እንደሚችሉ መብታቸው ቢሆንም፣ ‹‹ለእኔ ካልተወሰነልኝ ምን ፍትሕ አለና?›› በማለት ጫፍ የወጣ የግል አስተሳሰብን በዳኞች ላይ ሰንዝረዋል፣ ያልተገባ ጫና በማሳደር ፍትሕ እንዲያዘነብልላቸው ሕግን በሚፃረር መንፈስም ተነስተዋል፣ ነገር ግን የሉዓላዊውን ፍርድ ቤት ታማኝነት በሚሸረሽር ሁኔታ ውሳኔ የሰጡትን ዳኞች ክብር በሚነካ ሁኔታ በማንቋሸሽ መቃወም እንደማይችሉ በውሳኔው ተተንትኖ ተገልጿል፡፡
በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 78(1)፣ 79 (2 እና 3) ላይ ፍርድ ቤቶች ከማናቸውም ጣልቃ ገብነት ሕግን መሠረት አድረገው ብቻ ሥራቸውን እንዲያከናውኑ መደንገጉን የቅጣት ውሳኔው አስታውሶ፣ ግለሰቦቹ የዳኞችን ክብር በማዋረድ የችሎት መድፈር ወንጀል በመፈጸማቸው በወንጀል ሕግ አንቀጽ 449(2) እና በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 480 እና 481 ድንጋጌን ተላልፈው በመገኘታቸው በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 149 (1) መሠረት ጥፋተኛ ተብለዋል፡፡
በመሆኑም በሕጉ በተደነገገው መሠረት የግለሰቦቹ ድርጊት ከፍ ያለ ቅጣት የሚያስቀጣ ቢሆንም፣ የወንጀልና የቅጣት ዓላማ አጥፊው ሌላ ጥፋት እንዳይፈጽም ማረምና መስተማር አልታረምም ካለም ለማስወገድ ሲሆን፣ ኅብረተሰቡም ከቅጣቱ እንዲማር፣ እንዲጠነቀቅ ማድረግና የመንግሥትና የዜጎችን ሰላምና ደኅንነት ለማረጋገጥ ጭምር መሆኑን በቅጣት ውሳኔው ተንትኗል፡፡
ዶ/ር በዕውቀቱ ትዕቢት በተሞላበት ሁኔታ በማንጓጠጥ፣ በመገላመጥና እንዲቆሙም ሲታዘዙ ዳኛ ወደ ቆሙበት ቦታ በመንደርደር በፖሊስ የተያዙ በመሆናቸው የማይገባ ተግባር መፈጸማቸውን ቅጣቱ ያብራራል፡፡ በመሆኑም ዶ/ር በዕውቀቱና ወ/ሮ መሠረት በረደድ እያንዳንዳቸው በስድስት ወራት ቀላል እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ቀሪዎቹ አራት ግለሰቦች ወ/ሮ ጥሩወርቅ፣ አቶ ቴዎድሮስ፣ አቶ ጊጋርና ወ/ሮ እናና እያዳንዳቸው በአንድ ወር ቀላል እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ በማሳለፍ በማረሚያ ቤት እንዲቆዩ ትዕዛዝ በመስጠት መዝገቡ ተዘግቷል፡፡

Source:Reporter

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Eessa turre,Maalirra Geenyeerra? Kutaa 4ffaa