የኢህአዴግ ስ/አ ኮሚቴ የኢኮኖሚ ሪፎርሞችን በመገምገም ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀመጠ

የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሚያዚያ 28/2011 ዓም ባካሄደው ስብሰባ ያለፉት ዓመታትን የኢኮኖሚ ዘርፍ አፈፃፀም በዝርዝር ከገመገመ በኋላ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርሞችን በማስቀመጥ ስብሰባውን አጠናቋል።
ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ከ2003 እስከ 2010 ዓም በአገሪቱ የተመዘገበውን የኢኮኖሚ አፈፃፀም የገመገመ ሲሆን በእነዚህ ዓመታት ውስጥ አጠቃላይ የአገር ውስጥ ምርት በአማካይ የ9.6 እድገት ማሳየቱን በዚህም የግብርና ዘርፍ የ5.7 በመቶ፣ የኢንዱስትሪ ዘርፍ ደግሞ የ19.1 በመቶ እንዲሁም የአገልግሎት ዘርፍ 10.3 በመቶ እድገት ማስመዝገቡን ተመልክቷል።
በሁለተኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ዘመን ከ2008 እስከ 2010 ባሉት ሶስት ዓመታት ዓመታዊ እድገቱ ከነበረበት 10.1 በመቶ ወደ 8.6 በመቶ ዝቅ ማለቱን እና አጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገቱ እየተቀዛቀዘ መምጣቱንም ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ገምግሟል። እየተመዘገበ ያለው የመዋቅራዊ ለውጥም አዝጋሚ መሆኑን ገምግሟል። በአገራችን ባለፉት ዓመታት በተፈጠረው አለመረጋጋት የተነሳም የውጭና የአገር ውስጥ ኢንቨስትመንት መቀዛቀዙን ነው ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው የገመገመው።
የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ በማስፈን የዋጋ ንረትን በነጠላ አሃዝ የመገደብ አጠቃላይ ግብ ከ2003 እስከ 2010 ባሉት ዓመታት የተሳካ እንዳልነበረ የገመገመው ኮሚቴው በ2010 በጀት ዓመት መጨረሻ በአገሪቱ ባለው አለመረጋጋትና የውጭ ምነዛሬ ቅነሳ የዋጋ ንረቱ 13.1 በመቶ መድረሱን አስቀምጧል።
ባለፉት ዓመታት በአጠቃላይ በአገራችን ተግባራዊ የተደረገው የልማት ፋይናንስ ሞዴል በብድር ላይ የተመሰረተ መሆኑና የፋይናንስ አቅርቦት የተመደበላቸው የመንግስት የልማት ድርጅቶች የፕሮጀክት አስተዳደር ብቃት ማነስ ኢኮኖሚውን ችግር ውስጥ እንደከተተው ገምግሟል። በመንግስት የልማት ድርጅቶች የሚወሰዱና አጭር የመክፈያና የችሮታ ጊዜ ያላቸው ብድሮች የአገሪቱን የውጭ ብድር ጫና እንዲገዝፍ በማድረጋቸው ላልተወሰን ጊዜ እንዲቋረጡ መደረጉን ጠቁሟል።
ኮሚቴው ሀገራችን ያጋጠሟትን የኢኮኖሚ ተግዳሮቶችን እና ሀገራዊ ለውጡ ያስገኛቸውን መልካም እድሎች በዝርዝር ከፈተሸ በኃላ ቀጣይ አቅጣጫዎችንም አስቀምጧል።
ለሁለንተናዊ እንቅስቃሴያችን የሰላም መስፈን፣ ፍትህ፣ መልካም አስተዳደርና ሰብዓዊ መብት መከበር መሰረት መሆናቸውን ያወሳው ኮሚቴው ባለፉት ወራት የአገራችንን ህዝቦች ለቅሬታ የዳረጉ በርካታ ጉድለቶችን ለማረም የሚያስችሉ ተግባራት መከናወናቸው ህዝቡ ወደ ልማት በመመለስ በተሻለ የለውጥ መንፈስ ለመስራት የሚያግዝ ምቹ ሁኔታ መሆኑን አመልክቷል።
አገራችን በዓለም አቀፍም ሆነ በአህጉራዊ ደረጃ ያላት ተሰሚነትና ተቀባይነት ማደጉ ባለፉት ዓመታት ያጋጠሙንን አጠቃላይ ኢኮኖሚያዊ ተግዳሮቶች ለመፍታት እንደ መልካም አጋጣሚ የሚያግዝ መሆኑንንም ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ገምግሟል።
በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያንና ትውልደ ኢትዮጵያዉያን በአገራችን የልማት አጀንዳ ላይ እንዲሳተፉ ማድረግ መቻሉ፣ ህብረተሰባችንም በአገራችን የፖለቲካና የልማት እንቅስቃሴ ላይ ያለው ተሳትፎ እየተጠናከረ መምጣቱ ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን ለማለፍ መልካም አጋጣሚ የሚፈጥሩ ናቸው ብሏል ኮሚቴው። በመሆኑም እነዚህን ምቹ ሁኔታዎች በመጠቀም ያለፉ ስህተቶችን በማረምና በተሻለ ግልፅነትና ተጠያቂነት መንፈስ ስራዎችን በማከናወን ውጤታማ ልማትን ማስቀጠል እንደሚገባ አስምሮበታል።
የመንግስትን ወጪ ውጤታማና ከገቢው ጋር የተቀራረበና የተገደበ ማድረግ፣ የታክስ ገቢን ማሳደግ፣ የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋን ለማረጋገጥና የኢኮኖሚ ብድር አቅርቦትን ላለመሻማት ለበጀት ጉድለት ማሟያ መንግስት ከባንክ የሚበደረው ከአጠቃላይ ኢኮኖሚው 3 በመቶ እንዳይበልጥ ገደብ መደረጉንም ተጠቅሷል።
በተመሳሳይ የኢንቨስትመንት ሁኔታን ለማሻሻል የንግድና የስራ ፈጠራን ማሳለጥ ማሻሻያ ፕሮግራም ተነድፎ ስራው መጀመሩን ጠቅሷል። የስራ እድል በሁሉም የልማት ዘርፍና በሁሉም የልማት ተዋናዮች የሚፈጠር ቢሆንም ስራውን በባለቤትነት የሚመራና የሁሉንም ተዋናዮች ሚና የሚያስተባብር ኮሚሽን መቋቋሙን ጠቅሷል።
የሲቪክ ማህበራት ድርጅቶች በአገራችን የኢኮኖሚና ማህበራዊ እንቅስቃሴ በተደራጀ መልኩ ተሳታፊ የሚሆኑበት ሁኔታ እንዲመቻች መደረጉንም ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው ጠቅሷል። የኢኮኖሚ ሴክተሮችን የሚያነቃቁ እርምጃዎች መውሰድ፣ ብክነትና የአመራር ዝርክርክነት የሚታይባቸውን የመንግስትን የልማት ድርጅቶችን ማስተካከል ባለፉት 12 ወራት ከተወሰዱት የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች መካከል መሆናቸውን አስገንዝቧል።
ስራ አስፈፃሚው በማክሮ ኢኮኖሚ ዘርፍ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት፣ የፊሲካል ፖሊሲና የውጭ ንግድ ቀጣይ ትኩረት የሚደረግባቸው ዘርፎች መሆናቸውን ጠቅሷል። የኢኮኖሚ እድገቱ ከጥራት አኳያ ያሉበትን ጉድለቶች በዝርዝር አጥንቶ የሪፎርም እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚገባ አቅጣጫ አስቀምጧል።
የታክስ አሰባሰብን ማዘመን፣ የግብር ግዴታቸውን በማይወጡ ላይ ህጋዊ እርምጃ መውሰድ፣ የኮንትሮባንድ ንግድን ከምንጩ ማድረቅ፣ የዕዳ ጫናቸው ከፍተኛ የሆኑ ብድሮችን ማገድ፣ ቀድሞ የተወሰዱ ብድሮችን የእዳ ክፍያ ጊዜ ማሸጋሸግ በቀጣይ ትኩረት የሚደረግባቸው መሆናቸውን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው አስታውቋል። የውጭን ንግድን በዓይነት በብዛትና በጥራት ማሳደግም ሌላው የትኩረት አቅጣጫ ነው።
የግብርናው ዘርፍ ሌላው የትኩረትና ርብርብ ማዕከል መሆኑን በማንሳት አነስተኛና ሰፋፊ የመስኖ ልማት፣ የግብርና ግብዓት ፋይናንስ አቅርቦት፣ እንስሳት እርባታ ምርታማነት፣ የግብርና አመራረት ዘዴን ማሻሻል፣ ድህረ ምርትን ብክነት መቀነስ፣ በጥናት ላይ የተመሰረተ የምግብ ዋስትና ስርዓት ተግባራዊ ማድረግ፣ የተፈጥሮ ሃብት አጠባበቅ የሁሉንም ትኩረትና ተሳትፎ አግኝቶ ተግባራዊ እንዲደረጉ ይሰራል ብሏል ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው። በእነዚህ ማሻሻያዎች መነሻነትም በአጭር ጊዜ ስንዴን፣ የቢራ ገብስን፣ የምግብ ዘይትና ጥሬ እቃዎችን ሙሉ በሙሉ በአገር ውስጥ እንዲመረቱ ማድረግ ይገባል ብሏል። ማዕድን ምርት፣ ማኑፋክቸሪንግ እና የቱሪዝም ዘርፍም በቀጣይ ትኩረት የሚደረግባቸው ናቸው።
መንግስት በኢኮኖሚው ውስጥ ጣልቃ የሚገባበት አግባብ ላይ የተለየ ዲስፕሊን መከተል፣ ሁሉንም የኢኮኖሚ ተዋናዮች በእኩል የሚያሳትፍ፣ ፍትሃዊ፣ ግልፅና ተጠያቂነት የሰፈነበት የውድደር ሜዳን መዘርጋት በቀጣይ ከሚወሰዱ እርምጃዎች ውስጥ መሆኖቸውን ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው አስቀምጧል።
የሀገር ውስጥ የስራ ፈጠራንም ሆነ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት መሰረት ልማትን በተለይም የኢንዱስትሪ ፓርኮችን መሰረት ያደረጉ የኢኮኖሚ እርምጃዎች ይወሰዳሉ። ነፃ የሰው ሃይል ዝውውር፣ የሲቪክ ማህበራት ተሳትፎ፣ የኢንቨስትመንት ከባቢያዊ ሁኔታን ማሻሻል ሪፎርሙ ትኩረት ከሚያደርግባቸው መስኮች ተጠቃሽ ናቸው።
ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በቀጣይ በአጭር ጊዜዎች ውስጥ በተከታታይ እየተገናኘ ስራዎችን በጋራ እንዲገመግምና አቅጣጫዎችን እንዲያስቀምጥ መግባባት ላይ መደረሱን የኢሕአዴግ ምክር ቤት ፅ/ቤት አስታውቋል።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Obbo Muktaar Kadir pireezidaantii Mootummaa Naannoo Oromiyaa ta’uun lammata filataman