አቶ ንጉሱ ጥላሁን በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መግለጫ ሰጥተዋል
ፊንፊኔ ግንቦት 02/2011(ቶለዋቅ ዋሪ) ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ የተከሰቱ ግጭቶችን ያነሳሱ፣ ያቀናበሩ፣ የመሩ እና እጃቸው አለበት ተብለው የተጠረጠሩ 2 ሺህ 517 ያህል ተጠርጣሪዎች በህግ እንዲጠየቁ መለየታቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ፅህፈት ቤት ፕረስ ሴክሬተሪ ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን ገለፁ።
የዜጎች መፈናቀልን በተመለከተ ባለፉት ሁለት አስርት ዓመታት በሀገሪቱ ሲስተዋል መቆየቱን አቶ ንጉሱ ተናግረዋል።
በለውጥ ሂደት ውስጥም ዜጎች በየትኛውም አከባቢ ሰርቶ የመለወጥ መብታቸው እንዲከበር ታሳቢ ተደርጎ መንግስት ሲሰራ ቢቆይም አሁንም ችግር ሆኖ መቆየቱን ነው ያመለከቱት።
በአሁኑ ወቅትም በክልሎችም ሆነ ከክልል ተሻግሮ የሚታዩት ግጭቶች መነሻ በማንነት እና ከወሰን ጋር በተያያዘ የሚፈጠሩ መሆናቸውንም ነው አቶ ንጉሱ ያመለከቱት።
በተከሰቱ ችግሮችም የሰው ህይወት መጥፋቱ እና ንብረት መውደሙንም አንስተዋል።
875 ሺህ ዜጎች ወደነበሩበት ቦታ ተመልሰዋል
ችግሩን ለመቅረፍ ቅድመ ጥንቃቄ የማድረግ እና የመከላከል ስራ መሰራቱን በመግለፅ፥ በህብረተሰቡ እና በመንግስት ርብርብ የመከኑ ችግሮች መኖራቸውን ገልፀዋል።
ግጭቶች ከተከሰቱ እና መፈናቀል ካጋጠመ በኋላ ዜጎች የበለጠ ጉዳት እንዳይዳረጉ ባሉበት ቦታ እና ተፈናቅለው በሚገኙበት አካባቢ የምግብ፣ የህክምና እና የቁሳቁስ ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
ይህም ተግባር በመንግስት፣ በግብረ ሰናይ ድርጅቶች እና በህብረተሰቡ እየተከናወነም ይገኛል ነው ያሉት።
ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው እንዲመለሱ ከማድረግ አኳያ ከመመለሳቸው በፊት የሚመለሱበት አካባቢን ምቹነት በማረጋገጥ ከተፈናቃዮቹ ጋር ውይይት እንደሚካሄድ አመልክተዋል።
እንዲሁም 875 ሺህ ዜጎች ወደነበሩበት ቦታ እንዲመለሱ መደረጉን በመግለፅም፥ ይህም ሂደት ዓለም አቀፍ መስፈርቶች የሆኑቱን የተፈናቃዮቹን ፍላጎት፣ የአካባቢዎቹን ሰላማዊነት እና ምቹነት በራሳቸው በተፈናቃዮቹ ተወካዮች ማረጋገጥን እንዲሁም የተፈናቃዮቹ ክብር መጠበቅን መሰረት በማድረግ መከናወኑን ነው ያስረዱት።
በሁሉም ሂደት የተፈቃናዮችን ፍቃድ መጠበቅ ቀዳሚ መሆኑን አንስተዋል።
በሂደቱ ግን የመገናኛ ብዙሃንን ተሳትፎ ጨምሮ አዳዲስ ግጭቶች እንዲከሰቱ እና ተፈናቃዮች እንዳይመለሱ የሚስተዋሉ ተግባራት መኖራቸውን አስታውቀዋል።
በተለይም ተፈናቃዮች እንዳይመለሱ የሚያደርጉ በራሳቸው ውስጥ የሚገኙ እና ነገ ጫካው ሲመነጠር ወንጀለኛነታቸው የሚጋለጥባቸው ወገኖች እና ተፈናቃዮችን የእርዳታ መሰብሰቢያ ምንጭ አድርገው የሚጠቀሙ ወገኖች አሉ ብለዋል።
በመገናኛ ብዙኀን በተለይም በማህብራዊ ሚዲያ የሌሎች ሀገራት መረጃዎችን ጭምር በማምጣት ግጭቶችን የማስፋፋት እና የበቀል ድርጊቶች እንዲፈፀም የሚሰሩም አሉ ነው ያሉት።
መንግስት የተፈናቃዮችን ችግር ለመቅረፍ እየሰራ ባለበት ወቅት ጥቂቶች “የእኔ ወገን ተጠቃ” በሚል ስሜት ከሰብዓዊነት ባፈነገጠ መልኩ ጥቃት ሲያደርሱም ተስተውሏል ብለዋል።
እነዚሀን ልንታገል ይገባል ነው ያሉት አቶ ንጉሱ፥ በዚህ ዓይነቱ እንቅስቃሴ ላይ ህጋዊ አርምጃ መወስድ እንደሚገባና ለዚያም እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
በአጠቃላይም ችግሩን ለመፍታት የህግ የበላይነትን ማስፈን ግድ እንደሆነ ነው የጠቆሙት።
የህግ የበላይነትን ማክበር እና ዴሞክራሲን ማጣጣም ያጋጠሙ ሁለት ፈተናዎች
ባለፈው አንድ ዓመት የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ያነሱት አቶ ንጉሱ፥ ነገር ግን በዚህ ወቅት የህግ የበላይነትን መተላለፍ ቀይ መስመር መሆኑን የዘነጉ አካላት እንዳሉ ገልፀዋል።
ሀገሪቱ ባለችበት የለውጥ ሂደት ውስጥም የህግ የበላይነትን ማክበር እና ዴሞክራሲን ማጣጣም ያጋጠሙ ሁለት ፈተናዎች መሆናቸውንም አንስተዋል።
ከዚህ በኋላ ግን መንግስት ሀገርን አደጋ ላይ እንዲሁም ህዝብን ችግር ላይ የሚጥሉ ችግሮች ሲፈጠሩ ቀይ መስመር ስለሆነ የማስተካከል ስራ እንደሚሰራም ነው አቶ ንጉሱ ያስገነዘቡት።
ከዚህ አኳያም ክልሎች እና የፌደራል መንግስት ህግን የማስከበር ህገ መንግስታዊ ስልጣን በየደረጃው ተሰጥቷቸዋል፤ በየአካባቢው ለሚፈፀሙ ህግን የመተላለፍ ጉዳዮች በመጀመሪያ ህግ እና ስርዓትን የማስከበር ኃላፊነት የአስተዳደር እርከኖችና መዋቅሮች መሆናቸውንም አንስተዋል።
ለግጭት የሚዳርጉ ጉዳዮች እና ግጭቶች በሚኖሩበት ጊዜ እንዲሁም የህግ የበላይነት በሚጣስበት ጊዜ የሚመለከታቸው ክልሎች ህግ እና ስርዓትን የማስከበር ሙሉ ስልጣን እና ግዴታ አለባቸው ብለዋል።
ህግን ለማስከበር በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ነገሮች ከአቅማቸው በላይ በሚሆንበት ጊዜም የፌደራል መንግስትን ድጋፍ የሚሹ ሆነው ሲገኝ፥ በክልሎች ጥያቄ መሰረት የፌደራል መንግስት ጣልቃ ገብቶ ህግን የማስከበር ስራ እንደሚሰራ ገልፀዋል።
ግጭቶችን የማምከን ስራ
ፀጥታን ከማረጋገጥ እና የዜጎችን ደህንነት ከማረጋገጥ አኳያ ሶስት አንኳር ስራዎች እንደሚሰሩም አቶ ንጉሱ አክለው ገልፀዋል።
የመጀመሪያው መከላከል ነው ያሉት አቶ ንጉሱ፥ በዚህም ግጭቶች ከመከሰታቸው በፊት እና ለግጭት መንስኤ የሚሆኑ ነገሮችን በጥናት ላይ ተመስርቶ የፌደራል እና የክልል መንግስታት በትብብር እንዲሁም የፌደራል ፖሊስ፣ የመረጃ ደህንነት እና መከላከያ ከክልል የፀጥታ አካላት ጋር በመሆን የግጭት ምልክቶችን ቀድሞ በመለየት የማምከን ስራ ይሰራሉ ብለዋል።
ሁለተኛው ግጭት ሊከሰቱባቸው የሚችሉ ቦታዎችን መለየት ነው ያሉት አቶ ንጉሱ፥ በዚህም በኢትዮጵያ ውስጥ ግጭቶች ሊነሱባቸው የሚችሉ እና የተለያዩ መነሻ ምክንያቶችን መነሻ በማድረግ በጥናት የተደረሱባቸው ቦታዎችን መለየት እና ቅድመ ጥንቃቄ የመስራት ስራ እንደሆነም አስታውቀዋል።
በሶስተኛነት ደግሞ ግጭት ሲከሰት አፋጣኝ ምላሽ መስጠት መሆኑን ነው አቶ ንጉሱ የጠቀሱት።
አቶ ንጉሱ አክለውም፥ በአሁኑ ወቅት የፌደራል መንግስት እና የክልል መንግስታት በጋራ በመሆን ግጭቶች እንዳይከሰቱ ቀድሞ የማምከን እና ከተከሰቱም የመከላከል ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል።
በቀጣይም ህዝቡ ለሰላም ዘብ እንዲቆም የህዝብ ለህዝብ ውይይቶችን አጠናክሮ ለማካሄድ አቅጣጫ ተይዞ እየተሰራበት እንደሚገኝም ጠቁመዋል።
2 ሺህ 517 ያህል ተጠርጣሪዎች ተለይተዋል
በቀጣይም ግጭቶችን ለማስቆም ግጭት የሚቀሰቅሱ፣ የሚያነሳሱ እና የሚያባብሱ የግጭት ባለቤቶችን በቁጥጥር ስር ማዋል እና በህግ ጥላ ስር ሆነው ተገቢውን ብይን እንዲያገኙ የማድረግ ስራም ቅድሚያ የሚሰጠው ነው ብለዋል።
ከዚህ ረገድ ካለፉት ሁለት ዓመታት ወዲህ የተከሰቱ ግጭቶችን ያነሳሱ፣ ያቀናበሩ፣ የመሩ እና እጃቸው አለበት ተብለው የተጠረጠሩ 2 ሺህ 517 ያህል ተጠርጣሪዎችን በህግ ለመጠየቅ ተለይቷል።
እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም 1 ሺህ 300 ያህሉ በቁጥጥር ስር ውለው በህግ አግባብ ጉዳያቸው እንዲታይ ተደርጓል ያሉት አቶ ንጉሱ፥ ቀሪዎቹም ጉዳያቸው እየታየ መሆኑን ጠቅሰዋል።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ