ከአንድ ግብር ከፋይ ላይ 80 ሺህ ብር ጉቦ የተቀበለ የገቢዎች ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ባለሙያ እጅ ከፈንጅ ተያዘ
ፊንፊኔ ግንቦት 15፣ 2014 (TW) ሃሰተኛ ደረሰኝ አቅርበሃል በሚል ምክንያት ከአንድ ግብር ከፋይ ላይ 80 ሺህ ብር ጉቦ የተቀበለ የገቢዎች ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የታክስ ኢንተለጀንስ ባለሙያ እጅ ከፈንጅ ተይዞ ምርመራ እየተደረገበት እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡
ተጠርጣሪው የጉለሌ ክፍለ ከተማ ገቢዎች አነስተኛ ግብር ከፋይ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የታክስ ኢንተለጀንስ እና የኦፕሬሽን ባለሙያ ሲሆን÷ በየካቲት ወር ውስጥ የግል ተበዳይን ፋይል አውጥቶ ስልክ በመደወል ሃሰተኛ ደረሰኝ ለመስሪያ ቤታችን አቅርበዋል በወንጀል ይጠየቃሉ ብሎ ወደ ቢሮ እንዲመጡ መጥራቱን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ክፍል የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
የግል ተበዳይ ወደ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ ቢሮ ሄደው ከግለሰቡ ጋር ከተገናኙ በኋላ÷ ሃሰተኛ ደረሰኝ እንዳላስገቡ እና ይህንንም ማረጋገጥ እንደሚቻል ለባለሙያው ቢገልፁለትም ባለሙያው ግን ሊከሰሱ ስለሆነ ጉዳዩን ከእኔ ጋር ተደራድረው ቢፈቱ ይሻላል ብሎ 140 ሺህ ብር ጉቦ ይጠይቃቸዋል፡፡
ተጠርጣሪው ግን በድጋሚ ወደግል ተበዳይ ስልክ በመደወሉ ጭቅጭቁ የበዛባቸው የግል ተበዳይ ሁኔታውን ለገቢዎች የስራ ኃላፊዎች በማሳወቅ እና በጋራ በመሆን ጉዳዩን ለፖሊስ አመልክተዋል፡፡
ፖሊስም የቀረበለትን ጥቆማ ተቀብሎ ባደረገው ክትትል ተጠርጣሪው ከግል ተበዳይ ላይ 80 ሺህ ብር ለመቀበል ተስማምቶ ግንቦት 11 ቀን 2014 ዓ.ም ጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ፊናንስ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኝ አንድ ባንክ ውስጥ ቀጥሯቸው ከተገናኙ በኋላ ገንዘብ ገቢ ማድረጊያ ፎርም በመሙላት 80 ሺህ ብሩን ተቀብሎ ወደራሱ አካውንት ሊያስገባ ሲል እጅ ከፈንጅ ተይዞ ምርመራ እየተረገበት እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡
Source:FBC
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ