የአማራና የኦሮሞ ህዝቦችን ለማጋጨት የሚጥሩ አካላትን ነቅቶ በመጠበቅ......

የአማራና የኦሮሞ ህዝቦችን ለማጋጨት የሚጥሩ አካላትን ነቅቶ በመጠበቅ ሰላምና ልማትን ማስቀጠል እንደሚገባ አክቲቪስት ጀዋር መሐመድ አስታወቀ፡፡
አክቲቪስቱና የልዑካን ቡድኑ ትናንት በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን ከሚሴ ከተማ ሲገቡ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡
አክቲቪስት ጀዋር በከሚሴ ሁለገብ ስታዲዬም በተደረገው አቀባበል ላይ እንደተናገረው በሁለቱ ህዝቦች መካከል ያሉትን ጥቃቅን ችግሮችን በማጉላት ግጭት እንዲፈጠር የሚያደርጉ አካላትን በመታገል ሰላም እንዲሰፍንና ልማት እንዲፋጠን መሥራት አስፈላጊ ነው።
የአካባቢው ኅብረተሰብ በኦሮሚያና አማራ ክልሎች ህዝቦች መካከል የልማትና የሰላም ድልድይ ሆኖ ለማገልገል እንደሚያስችልም እምነቱን ገልጿል፡፡
በአካባቢው የሚኖሩ አክቲቪስቶች፣ ቄሮዎችና ፖለቲከኞች ለሰላምን ለልማት ትኩረት ሰጥተው እንዲረባረቡም ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
ሕዝቡ ወንጀለኞችን አጋልጦ መስጠትና ሕግ የማስከበር ኃላፊነቱን ለጸጥታ ኃይሉ መተው እንዳለበትም አስገንዝቧል፡፡
የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ተቀዳሚ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ አህመድ አሰን በበኩላቸው በኦሮሞ ህዝቦች ትግል የሚታወቀው አክቲቪስት ጀዋር ወደ ዞኑ በመምጣቱ መደሰታቸውን ገልጸዋል፡፡
የኦሮሞ ህዝብ ፈታኝ ችግሮችን አልፎ ማንነቱንና ቋንቋው የተከበረለት በትግሉ መሆኑን አመልክተው፣ይህንን ለማስቀጠል ህዝባዊና አገራዊ አደራ አለብን ብለዋል፡፡
በጅሌ ጥሙጋ የሚኖሩት ሼህ አህመድ ሁሴን በህዝቡ ውስጥ ለተቀጣጠለው የለውጥ እንቅስቃሴ የአክቲቪስት ጀዋር ሚና ጉልህ እንደነበር አውስተው፣ ፍትሃዊ ሥርዓት እውን እንዲሆን፣ የጋራ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥና አገራዊ አንድነቱ እንዲጠናከር ጀዋርና ሌሎች ፖለቲከኞች በትጋት እንዲንቀሳቀሱ ጠይቀዋል፡፡
ከባቲ ወረዳ የመጡት አቶ አህመድ መሐመድ በበኩላቸው የአካባቢው ህዝብ በርካታ ሥርዓትንና ገዢዎችን እንዳሳለፈ ጠቅሰው፣አሁን በአገሪቱ እየተካሄደ ያለውን ለውጥ ለማስቀጠል ሁሉም በጋራ መንቀሳቀስ እንደሚገባው አመልክተዋል፡፡
ለአክቲቪስት ጀዋርና ለልዑካን ቡድኑ የእንስሳት፣ የአልባሳትና የግብርና ምርቶች ስጦታ ተበርክቶላቸዋል።
አክቲቪስት ጀዋር የተበረከተለትን ኮርማ በአካባቢው ሰላም እንዲረጋገጥ የዜግነት ግዴታውንን እየተወጣ ላለው የመከላከያ ሠራዊት በስጦታ አበርክቷል፡፡
Source: ENA

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Eessa turre,Maalirra Geenyeerra? Kutaa 4ffaa