የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሥልጣን ተሰጠው

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ፓርላማ ሳያፀድቀው አስፈጻሚ አካላትን ማደራጀት የሚያስችለው ሥልጣን ተሰጠው

በአዋጁ ክፍል ሦስት አንቀጽ 34 የፌዴራል አስፈጻሚ አካላትን እንደገና ስለማደራጀት የተደነገገ ሲሆን፣ ‹‹የሚኒስትሮች ምክር ቤት አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ደንብ በማውጣት ማንኛውም አስፈጻሚ አካል እንዲታጠፍ፣ ከሌላ አስፈጻሚ አካል ጋር እንዲዋሃድ ወይም እንዲከፈል በማድረግ፣ ተጠሪነቱ ወይም ሥልጣንና ተግባሩ እንዲለወጥ በማድረግ ወይም አዲስ አስፈጻሚ አካል እንዲቋቋም በማድረግ፣ የፌዴራል አስፈጻሚ አካላትን እንደገና የማደራጀት ሥልጣን በዚህ አዋጅ ተሰጥቶታል፤›› ሲል ይደነግጋል፡፡
በዚህም መሠረት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ተወያይቶ የሚያፀድቀውን የአስፈጻሚ አካላት አዋጅ ለፓርላማ ልኮ የሚያስፀድቅበትን አሠራር የሚያስቀር ሲሆን፣ ይኼንን አሠራር የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ በማውጣት ብቻ እንዲፈጽም የሚያስችለው ሥልጣን ተችሮታል፡፡
ካሁን ቀደም የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችንም ሆነ የሌሎች አስፈጻሚ አካላትን አስፈላጊነት በመተንተንና በመዘርዘር የሚኒስትሮች ምክር ቤት እንዲፀድቅለት ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅቶ ሲያቀርብ፣ በፓርላማው ውይይት ይደረግበት የነበረ አሠራር ነበር፡፡ በሚጨመሩ አስፈጻሚ አካላት አስፈላጊነት ላይ፣ በሚቀነሱ በሚታጠፉና በሚከፈሉት ላይ ደግሞ የምክንያታዊነት ጥያቄ ቀርቦ ክርክሮች ይደረጉም ነበር፡፡
ይህም ካሁን ቀደም የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የግብርናና እንስሳት ሀብት ሚኒስቴርን ለሁለት በመክፈል፣ የእርሻና የተፈጥሮ ሀብት ሚኒስቴርና የእንስሳትና የዓሳ ሀብት ልማት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን ሲያቋቁሙ በነበረው የምክንያታዊነት ጥያቄ የታየ ነበር፡፡
የአሁኑ ለውጥ በባለሙያዎች ዘንድ በሁለት ገጽታዎች ታይቷል፡፡ አንደኛው ቀድሞውኑ ፓርላማው ሲጠይቅ ውጤታማ ሥራ ለማከናወን ያመቻል ወይም አያመችም ተብሎ በሚሰጣቸው ምላሽ ብቻ የሚታለፉ ስለሆነ፣ የውጤታማ መሆንና አለመሆን በግምገማ የታገዘ ማስረጃ ቀርቦ ክርክር ስለማይደረግበት የአስፈጻሚው አካል ውሳኔ በቀጥታ መፅደቁ የተለመደ በመሆኑ፣ የአሁኑ ውሳኔ አግባብ ያለው እንደሆነ የሚገልጹ አሉ፡፡
ይሁንና ይህ ውሳኔ ፓርላማውን ሊያዳክም የሚችልና ሥልጣኑንና ኃላፊነቱን ለአስፈጻሚው አሳልፎ የሚሰጥ ስለሆነ፣ የቁጥጥር ሥራው ላይ ክፍተት ሊፈጥር ይችላል የሚሉም አሉ፡፡ አስፈጻሚ አካላት ሲዋቀሩ ዓላማቸውንና ተልዕኳቸውን ገምግሞ የሚጨመረው ጨምሮ፣ የሚቀነሰውን ቀንሶ በሚገባ ያልቀረፀውን መሥሪያ ቤት ለመቆጣጠርም አስቸጋሪ ይሆናል ሲሉም አስተያየታቸውን የሚሰጡ አሉ፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ፓርላማው በሕገ መንግሥቱ ከተሰጠው የፌዴራል መንግሥት አደረጃጀትን የመወሰን ሥልጣን ጋር የሚጋጭና የሕገ መንግሥት ጥሰት የፈጸመ ውሳኔ እንደሆነ የሚያስረዱ አሉ፡፡
የሕግ ባለሙያው አቶ አብዱ አሊ ሒጂራ ፓርላማው በደፈናው ያለውን ሕግ የማውጣት ሥልጣኑን አሳልፎ እንደማይሰጥና በሚኒስትሮች ምክር ቤትም እንዲሁ ሊነጠቅ እንደማይችል ያስረዳሉ፡፡ ምክንያቱም ዋነኛው የፓርላማው ሥልጣን ሕግ ማውጣት ነውና፡፡
‹‹ይህ በውክልና ሥልጣንን የማስተላለፍ መርህን የጣሰና ሕገ መንግሥታዊ ያልሆነ ነው፡፡ ፓርላማው የራሱን ሥራ በጭራሽ አሳልፎ ሊሰጥ አይችልም፤›› ሲሉ ይሞግታሉ፡፡
የሚኒስትሮች ምክር ቤት በሕገ መንግሥቱ በተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት በፓርላማው በተጠቀሰው ደንብ የማውጣት ኃላፊነት ብቻ ሕግ እንደሚያወጣ አውስተው፣ በተደጋጋሚ መንግሥት ሲጥሰው የነበረ የሕግ መርህ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ ከአሁን ቀደም ሳይንስና ቴክኖሎጂ ከጽሕፈት ቤት ወደ ኮሚሽንነት ሲያድግና የሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ሲመሠረቱ ተመሳሳይ ስህተት መሠራቱን፣ አሁንም ትምህርት ሊወሰድበት ያልተቻለ ጥፋት ነው ይላሉ፡፡
‹‹ይህ ቀድሞ የነበረ ሲሆን፣ አሁንም በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ያልተሻሻለ ነው፤›› ሲሉም ይወቅሳሉ፡፡
አዋጁ ለውይይት ሲቀርብ አንድ የፓርላማ አባልም በጉዳዩ ላይ ባቀረቡት ጥያቄ፣ ‹‹የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ አውጥቶ ማንኛውንም መሥሪያ ቤትና አስፈጻሚ አካል ማጠፍ፣ ማቋቋምና ማዋሀድ እንደሚችል ሥልጣን ይሰጣል፡፡ እንዴት ነው የታሰበው? በአዋጅ የተቋቋሙ ወሳኝ መሥሪያ ቤቶችንም ጭምር የማጠፍ ሥልጣን የሚሰጥ ከሆነ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዚህ መዋቅር ውስጥ ይኼንን አደረጃጀት የማፅደቅ ሚናው እንዴት ነው የታየው? ይህ አንቀጽ አተገባበሩ እንዴት ሊገመገምና ወደ ተግባር ሊቀየር ታስቧል?›› ብለዋል፡፡
በጉዳዩ ላይ ምላሽ የሰጡት የአደረጃጀቱን ጥናት የመሩት አቶ ታገሰ ጫፎ እንዳብራሩት፣ ‹‹የሚኒስትሮች ምክር ቤት በደንብ አማካይነት አዳዲስ ተቋማትን በተለይ አጠቃላይ የለውጥ እንቅስቃሴ ማዕከል በማድረግ መፍጠር በሚያስፈልግበት ጊዜ፣ እንዲሁም አሁን ያለንን ሀብት አጠቃቀም በሚመለከት በየጊዜው እየታየ ተቋማትን ለማስተካከል የሚያስችል ሥልጣን ቢሰጠው፣ አሁን በፌዴራል ደረጃ ያሉ ተቋማትን በዝርዝር ለማየት ዕድል ይሰጣል፤›› ብለዋል፡፡
‹‹ለምሳሌ አዲስ ተቋም ለማቋቋም በጣም እጅግ አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜ፣ በተለይ በአገር ውስጥ ሥራ ላይ ያሉ ችግሮችን መነሻ ያደረጉ ተቋማትን ማቋቋም በሚያስፈልግበት ጊዜ፣ ሁለተኛ ከውጭ ዓለም ጋር ባለን ግንኙነት ምክንያት ተቋማት እጅግ አስፈላጊ በሚሆኑበት ጊዜ፣ ይኼንን ለሥራው ስኬት ሲባል እንዲያቋቁም መፍቀድ ጥሩና ተገቢ ይሆናል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡
‹‹ሁለተኛ በፌዴራል ደረጃ ያሉ ተጠሪ ተቋማትን በሚመለከት እንዳያችሁት በዝርዝር የቀረቡ ተጠሪ ተቋማት፣ በዚህ ጥናት መሠረት እንዲታጠፉና እንዲዋሀዱ የተደረጉ አሉ፡፡ አሁንም ቢሆን በርካታ ተቋማት ናቸው ያሉት፡፡ አጠቃላይ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን ጨምሮ በፌዴራል ደረጃ 178 ተቋማት አሉ፡፡ ስለዚህ እነዚህን ተቋማት እያዩ ለሥራ ውጤታማነት በሚመች አግባብ እያሰባሰቡና እያጠፉም ውጤታማ በሆነ መንገድ የለውጥ ጉዟችንን ለማፋጠንና ለማሳካት እንዲረዳ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ይኼንን ሥልጣን የተከበረው ምክር ቤት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት አሁን ባለው ሁኔታ በፍጥነት ለውጡን ለማስቀጠል እንዲያስችል ቢሰጥ፣ የተሻለ አማራጭ ይሆናል ብለን ስላሰብን ያቀረብነው ነው፤›› ብለዋል፡፡
ፓርላማው ባደረገው ስብሰባ የአስፈጻሚ አካላት ከ28 ቀደ 20 ዝቅ እንዲሉ አድርጎ ያፀደቀ ሲሆን፣ የሰላም ሚኒስቴርን በማቋቋም ቀድሞ የነበሩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን አጥፎ፣ ቀላቅሎና ከፋፍሎ የቀረበለትን አዋጅ 1097/2011 በሙሉ ድምፅ አፅድቆታል፡፡ ካሁን በኋላ ተመሳሳይ ውሳኔዎች በሚኒስትሮች ምክር ቤት የሚወሰኑ ሲሆን፣ ለመፅደቅ ወደ ፓርላማው አይመጡም፡፡
ፓርላማው በዕለቱ ውሎው 16 አዳዲስ ሚኒስትሮችን የሾመ ሲሆን፣ ከጠቅላላው 20 የአስፈጻሚ አካላት መካከል አሥሩ ሴቶች ናቸው፡፡

Source:Reporter

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Eessa turre,Maalirra Geenyeerra? Kutaa 4ffaa