አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ አራተኛዋ ፕሬዚዳንት ሆኑ

ታዋቂዋ ዲፕሎማት አምባሳደር ሳህለወርቅ ዘውዴ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመን (ዶ/ር) በመተካት አራተኛዋ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት በመሆን፣ በሕዝብ ተወካዮችና በፌዴሬሽን ምክር ቤት የጋራ ልዩ ስብሰባ ተሾሙ፡፡

ሐሙስ ጥቅምት 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ፕሬዚዳንት ሙላቱ ለጋራ ስብሰባው ባቀረቡት መልቀቂያ ላለፉት አምስት ዓመታት አገራቸውን በቅንነት ማገልገላቸውን በማስታወስ፣ ይህም የሚኮሩበት የታሪካቸው አካል እንደሆነ በማስታወቅ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥትን አመሥግነዋል፡፡ ሦስቱ ዓመታት ለአገሪቱ ፈታኝ እንደነበሩ ገልጸው፣ ካለፉት ስድስት ወራት ወዲህ ግን በርካታ አመርቂ ውጤቶች  መመዝገባቸውን አስረድተዋል፡፡
ሦስተኛው የሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት ለምን መልቀቅ እንደፈለጉ ሲያስረዱ፣ ይዘው የቆዩትን የርዕሰ ብሔር ኃላፊነት የሚያስረክቡት በአሁኑ ጊዜ የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠል የሚያስችል አመራር ወደ ኃላፊነት እየመጣ በመሆኑ ነው ብለዋል፡፡ የፕሬዚዳንቱ መልቀቂያም በጋራ ስብሰባው ተቀባይነት አግኝቷል፡፡ በኢትዮጵያ ካሁን በኋላ የመንግሥት ሥልጣን ከብሔርና ከፆታ አኳያ ብቻ መታየት እንደሌለበትም አስገንዝበዋል፡፡ ሥልጣናቸውንም በይፋ ለአዲሷ ፕሬዚዳንት አስረክበዋል፡፡
ፕሬዚዳንት ሙላቱ ሁለተኛው የሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት የነበሩትን አቶ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ በመተካት መስከረም 27 ቀን 2006 ዓ.ም. መሾማቸው ይታወሳል። ከአቶ ግርማ በፊት የመጀመርያው ፕሬዚዳንት ነጋሶ ጊዳዳ (ዶ/ር) በ1988 ዓ.ም. መሾማቸው አይዘነጋም፡፡

በምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ አማካይነት ለጋራ ስብሰባው በዕጩነት የቀረቡት አምባሳደር ሳህለወርቅ አራተኛዋ ፕሬዚዳንት በመሆን በሙሉ ድምፅ ተሹመዋል፡፡ ከዛሬ ጀምሮም ለሚቀጥሉት ስድስት ዓመታት በርዕሰ ብሔርነት ለማገልገል ቃለ መሃላ ፈጽመዋል፡፡ ባደረጉት ንግግርም ለሰላም ትልቅ ዋጋ መስጠት እንደሚገባ በጥብቅ አስገንዝበው፣ አገራቸውን በታማኝነትና በቅንነት ለማገልገል ቃል ገብተዋል፡፡
ለበርካታ ዓመታት በዲፕሎማትነት አገራቸውን ያገለገሉትና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) በከፍተኛ ኃላፊነቶች የሠሩት አምባሳደር ሳህለወርቅ፣ የመጀመርያዋ የአገሪቱ የሴት ፕሬዚዳንት እንዲሆኑ በሁለቱ ምክር ቤቶች ተሾመዋል፡፡ 
በአዲስ አበባ ከተማ በ1943 ዓ.ም. የተወለዱትና በሊሴ ገብረ ማርያም ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን የተከታተሉት አዲሷ ፕሬዚዳንት፣ ከፍተኛ ትምህርታቸውን በፈረንሣይ አገር ሞንትፔልየ ዩኒቨርሲቲ ተከታትለዋል፡፡ በፈረንሣይም የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር በመሆን ሲያገለግሉ፣ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ኢጋድን ጨምሮ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው አገልግለዋል፡፡
እ.ኤ.አ. በ2011 በቀድሞው የተመድ ዋና ጸሐፊ ባን ኪ ሙን በምክትል ዋና ጸሐፊነት ደረጃ የመንግሥታቱ ድርጅት የናይሮቢ ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ተደርገው መሾማቸው ሲታወስ፣ ኢትዮጵያን በመወከል በተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች አገልግለዋል፡፡

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Eessa turre,Maalirra Geenyeerra? Kutaa 4ffaa