በኦሮሚያ ሁለት ከፍተኛ አመራሮች ከኃላፊነት ተነሱ

አቶ በከር ሻሌ የኦሕዴድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ሆኑ

የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት (ኦሕዴድ) ፖሊት ቢሮ፣ ከወራት ወዲህ በኦሮሚያ ክልል ከተከሰተው የፀጥታ መደፍረስ ጋር በተያያዘ ሁለት የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮች ከሥልጣናቸው እንዲነሱ ወሰነ፡፡


ከሥልጣን እንዲነሱ የተደረጉት የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚና የኦሕዴድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዳባ ደበሌና የኦሕዴድ ሥራ አስፈጻሚና የኦሮሚያ ክልል አስተዳደርና ፀጥታ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ሰለሞን ኩቹ ናቸው፡፡

የኦሕዴድ ፖሊት ቢሮ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በኦሮሚያ ክልል እየተነሳና ዳግም እያገረሻ የሚገኘውን የፀጥታ ሁኔታ ገምግሟል፡፡ በዚህ ግምገማ በአቶ ዳባና በአቶ ሰለሞን የተያዙት መዋቅሮች ብዙ ቢጠበቅባቸውም፣ ችግሩን ለመፍታት ያበረከቱት አስተዋጽኦ ግን ዝቅተኛ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሷል፡፡ በዚህ መሠረት ኃላፊዎቹ እንዲነሱ መወሰኑን ምንጮች አመልክተዋል፡፡

የኦሕዴድ ፖሊት ቢሮ በእነዚህ ከፍተኛ አመራሮች ምትክ ሹመት ሰጥቷል፡፡ የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚና የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ በከር ሻሌን የኦሕዴድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አድርጎ ሾሟል፡፡ የኦሕዴድ ሥራ አስፈጻሚና የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የሕዝብ አደረጃጀት አማካሪ አቶ በዙ ዋቅቤካ ደግሞ የኦሮሚያ የአስተዳደርና ፀጥታ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ ሆነው እንዲሾሙ ወስኗል፡፡

መረጃዎች እንደጠቆሙት፣ አቶ በከር የካቲት 21 ቀን 2008 ዓ.ም. ስታዲየም አካባቢ በሚገኘው የኦሮሞ ባህል ማዕከል ውስጥ የሚገኙትን የኦሕዴድ ጽሕፈት ቤትና ኮማንድ ፖስት ጎብኝተዋል፡፡ አቶ በከር አዲሱ ምድባቸው በይፋ ባይገለጽላቸውም፣ መረጃው እውነትነት እንዳለው ለሪፖርተር አረጋግጠዋል፡፡

ነገር ግን የካቲት 22 ቀን 2008 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ሠራተኞችን ሰብስበው፣ የስድስት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበው ውይይት ሲያደርጉ ውለዋል፡፡

ካለፉት አራት ወራት ወዲህ በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ ቦታዎች የፀጥታ ችግር መከሰቱ ይታወቃል፡፡ የፀጥታ ሁኔታው ወደ ነበረበት ለመመለስ የተለያዩ የሰላም ኮንፈረንሶች ቢካሄዱም መረጋጋቱ ብዙም ሳይቆይ እንደገና እያገረሸ ይገኛል፡፡ የሚነሳው የፀጥታ ችግር የዜጎችን ሕይወት ከመቅጠፍና በአካል ላይ ጉዳት ከማድረስ አልፎ በርካታ ንብረት እያወደመ ነው፡፡

ለፀጥታው መደፍረስ የአዲስ አባባና የኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላን ረቂቅ፣ ቀጥሎም የመልካም አስተዳደር ችግሮች መንስዔዎች ናቸው ቢባልም፣ በምዕራብ አርሲ ዞን የተነሳው ግጭት የተለየ አጀንዳ ያለው ነው የሚሉ መረጃዎች እየወጡ ነው፡፡

የኦሮሚያን የፀጥታ ችግር ለመቆጣጠርም ሆነ ችግሩን ለመፍታት በዋነኛነት የኦሕዴድ ጽሕፈት ቤትና የክልሉ የአስተዳደርና ፀጥታ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊነት ቢኖራቸውም፣ መዋቅሮቹን የሚመሩት አመራሮች ኃላፊነታቸውን ባለመወጣታቸው በአዲስ አመራሮች እንዲተኩ መደረጉን ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

አቶ ዳባ በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየት እንዲሰጡ ቢጠየቁም ‘ስብሰባ ላይ ነኝ’ በማለት ምላሽ ሳይሰጡ ቀርተዋል፡፡ ከሪፖርተር ጥያቄ የቀረበላቸው የክልሉ ባለሥልጣናትም፣ የፖሊቲ ቢሮ ያሳለፋቸው ውሳኔዎች ደረጃቸውን ጠብቀው የሚገለጹ ናቸው በሚል ይፋዊ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከረቡዕ የካቲት 23 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ የኦሕዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት በሹም ሽሩ ላይ ግምገማ ለማድረግ በአዳማ መክተማቸውን ምንጮች ገልጸዋል፡፡ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላቱ በክልሉ እየተነሳና እያገረሸ የሚገኘውን የፀጥታ ሁኔታንም በተመለከተ እንደሚወያዩ ታውቋል፡፡


Source:Reporter

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Obbo Muktaar Kadir pireezidaantii Mootummaa Naannoo Oromiyaa ta’uun lammata filataman