የሰማያዊ ፓርቲ ቅሌት

የሰማያዊ ፓርቲ የሥነ ሥርዓት ኮሚቴ በወሰደው አምስት የፓርቲውን ከፍተኛ አመራሮች የማሰናበትና የማገድ ውሳኔን በተመለከተ፣ የፓርቲው የኦዲትና የኢንስፔክሽን ኮሚቴ የመጨረሻውን ውሳኔ ረቡዕ መጋቢት 21 ቀን 2008 ዓ.ም. እንደሚሰጥ፣ የኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ አበራ ገብሩ ለሪፖርተር አስታወቁ፡፡


የሥነ ሥርዓት ኮሚቴው ያሳለፈው አምስት የፓርቲው አመራሮችን የማገድ ውሳኔ እንደደረሳቸው፣ የመጨረሻውን የኮሚቴውን ውሳኔ ለማሳለፍ ውይይት መካሄዱንና የመጨረሻውን ውሳኔ እንደሚሰጥ አቶ አበራ አስታውቀዋል፡፡

የፓርቲው የሥነ ሥርዓት ኮሚቴ የማሰናበትና የማገድ ውሳኔ ያሳለፈባቸው አምስት አመራሮች ናቸው፡፡ በዚህም መሠረት ፕሬዚዳንቱ ኢንጂነር ይልቃል ጌትነትና የሒሳብ ክፍል ኃላፊው አቶ ወረታው ዋሴ ከፓርቲው እንዲባረሩ የተወሰነባቸው ሲሆን፣ የፓርቲው የቀድሞ ምክትል ሊቀመንበርና አሁን የፓርቲው ምክር ቤት አባል አቶ ስለሺ ፈይሳና ሌላዋ የምክር ቤት አባል ወ/ሪት ወይንሸት ሞላ ደግሞ ለሁለት ዓመታት ከማንኛውም የኃላፊነት ቦታ እንዲታገዱና አቶ ጌታነህ ባልቻ ደግሞ ለሦስት ወራት በምክር ቤቱ በድምፅ እንዳይሳተፉ መወሰኑን፣ የፓርቲው ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ነገሠ ተፈረደኝ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

የውሳኔው ምክንያት በዋነኛነት ከገንዘብ ጋር የተገናኘ እንደሆነ አቶ ነገሠ አስረድተው፣ የሥነ ሥርዓት ኮሚቴው ሲያካሂድ የነበረውን ምርመራና ማጣራት ወደ መጨረሻ ላይ መስመሩን ስቷል በማለት ጨምረው አብራርተዋል፡፡

‹‹በምክር ቤት ደረጃ ከዚህ በፊት በፓርቲው ውስጥ የገንዘብ ምዝበራ አለ የሚል ሐሳብ በመቅረቡ፣ ያንን ሐሳብ የሚያጣሩ የምክር ቤት አባላት ተመርጠው ዋና ዋናውን መረጃ እንዲሰበስቡ ተወሰነ፡፡ ከዚያ በኋላ ጉዳዩ በጥልቀት መጣራት ስላለበት ምክር ቤቱ ጉዳዩን ወደ ሥነ ሥርዓት ኮሚቴው መራው፡፡ የሥነ ሥርዓት ኮሚቴም የቀረበለትን ጉዳይ እስካሁን ድረስ ሲመረመር ቆይቶ ወደ መጨረሻ ላይ መስመሩን በመልቀቅ ውሳኔውን ይፋ አደረገ፡፡ ውሳኔው ተገቢ ባለመሆኑ በግሌም አልቀበለውም፤›› በማለት አቶ ነገሠ ጉዳዩን በዝርዝር አስረድተዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በጉዳዩ ላይ የመጨረሻ ውሳኔ የሚሰጠው አካል የኦዲትና ኢንስፔክሽን ኮሚቴ በመሆኑ፣ የመጨረሻው ውሳኔ የሚሆነው የእርሱ እንደሆነና የኮሚቴው ውሳኔ ሳይታወቅ እንዲህ እንዲህ ማለቱ ተገቢ እንዳልሆነ ጨምረው አስረድተዋል፡፡

በዚህ ሐሳብ የሚስማሙት የሥነ ሥርዓት ኮሚቴው ሰብሳቢ ወ/ሮ ሀና ዋለልኝ በበኩላቸው፣ ‹‹እኛ ወስነን የቅጣት ውሳኔውን ለሚመለከታቸው አካላት ሰጥተናል፡፡ የኦዲትና ኢንስፔክሽን ኮሚቴ እንዲህ ዓይነት ጉዳዮች ሲቀርቡለት ውሳኔውን ዓይቶ የመጨረሻውን ውሳኔ ከ15 ቀናት በኋላ ይሰጣል፤›› በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

በዚህም መሠረት ጉዳዩ የኦዲትና ኢንስፔክሽን በሚሰጠው ውሳኔ መሠረት የሚታወቅ ይሆናል በማለት ገልጸዋል፡፡ ‹‹የኦዲትና ኢንስፔክሽን ኮሚቴ ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት የሚሠሩ ሥራዎች ሁሉ ደንብና መመርያን ያልተከተሉ፣ ተቋማዊ አሠራርን የጣሰና ሥርዓት አልበኝነት የሰፈነባቸው አካሄዶች ናቸው፡፡ ስለዚህ እነዚህ መታረም ይኖርባቸዋል፤›› ሲሉ የመጨረሻው ውሳኔ ከኦዲትና ኢንስፔክሽን ኮሚቴው የሚጠበቅ እንደሆነ አስታውቀዋል፡፡

በመተዳደርያ ደንቡ መሠረት የሥነ ሥርዓት ኮሚቴው ፕሬዚዳንቱን የማገድ ሥልጣን አለው ወይ? የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው ወ/ሮ ሀና፣ ‹‹ማንኛውም ክስ የተመሠረተበት አባል አይታገድ የሚል ነገር የለም፡፡ ማንኛውም የጥፋተኝነት ውሳኔ የተበየነበት ሰው እንደ ጥፋተኛ ነው የሚታየው ምንም የተለየ ድንጋጌ የለም፤›› በማለት ፕሬዚዳንቱም ከዚህ ውጪ መሆን አይችሉም ሲሉ ተከራክረዋል፡፡

የሰማያዊ ፓርቲ የሥነ ሥርዓት ኮሚቴ ከዚህ ቀደም የምክር ቤት አባላት የነበሩ የቀድሞው የፓርቲውን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ዮናታን ተስፋዬን ጨምሮ፣ ሌሎች አባላትን ማገዱ የሚታወስ ነው፡፡ ሆኖም የፓርቲው ምክር ቤት ውሳኔውን ውድቅ አድርጐታል፡፡ በኦዲትና ኢንስፔክሽን ኮሚቴ ይተላለፋል ተብሎ የሚጠበቀው ውሳኔ ደግሞ ቀጣይ የፓርቲውን አቅጣጫ የሚጠቁም እንደሆነ እየተነገረ ነው፡፡  

Source:Reporter



አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Obbo Muktaar Kadir pireezidaantii Mootummaa Naannoo Oromiyaa ta’uun lammata filataman