በኦሮሚያ በተከሰተው ተቃውሞ ወቅት የመንግሥት ድረ ገጾችን ሰብሮ የመግባት ጥቃት ተፈፅሟል

በኦሮሚያ በተከሰተው ተቃውሞ ወቅት የመንግሥት ድረ ገጾችን ሰብሮ የመግባት ጥቃት መፈጸሙን ዶ/ር ደብረጽዮን ገለጹ


-    ቴሌ የራሱ የኃይል አማራጭ እንዲኖረው ይደረጋል ብለዋል

በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ተነስቶ በነበረው ተቃውሞ ወቅት የመንግሥት ድረ ገጾችን ሰብሮ የመግባት ጥቃት መፈጸሙን፣ የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረ ሚካኤል ለፓርላማው ገለጹ፡፡

የተሰነዘሩት ጥቃቶች በአብዛኛው ያተኮሩት በወረዳ ኔት ድረ ገጽ ላይ መሆኑን፣ ለሚመለከታቸው ተቋማትና ለመረጃ መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ የማሳወቅ ሥራ በማከናወን የተጠቀሱትን ችግሮች ለመፍታት ጥረት መደረጉን፣ ማክሰኞ መጋቢት 20 ቀን 2008 ዓ.ም. የሥራ አፈጻጸማቸውን ለፓርላማ ባቀረቡበት ወቅት ተናግረዋል፡፡ አሁን ግን ችግር የገጠማቸው ድረ ገጾች አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውን ገልጸዋል፡፡

የወረዳ ኔት የኢንተርኔት ቴክኖሎጂ ሁሉንም የአገሪቱ ወረዳዎች በአንድ የሚያገናኝ ሲሆን፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የሚገኘው የብሔራዊ የዳታ ማዕከል ውስጥ የተካተተ መሆኑ ይታወቃል፡፡

‹‹ግርግር ሲጀመር ነው የወረዳ ኔት ድረ ገጽ ላይ ጥቃት የተሰነዘረው፡፡ ከየትኛው አገር እንደተሰነዘረም አውቀነዋል፡፡ ልዩ ትኩረትም እንሰጠዋለን፤›› በማለት ሚኒስትሩ ለፓርላማው አሳውቀዋል፡፡

ዓላማውን በተመለከተም አንድ ግርግር በኢትዮጵያ ውስጥ ሲፈጠር እሱን በማራገብ ለማቀጣጠል መሞከር እንደሆነ፣ የዚሁ አካል ሌላኛው ሙከራም በተለያዩ ማኅበራዊ ድረ ገጾች ላይ እንደታየ ተናገረዋል፡፡

በሌላ በኩል ለምክር ቤቱ ያቀረቡትን የስድስት ወራት ሪፖርት ተከትሎ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ በሞባይል ግንኙነት ላይ ችግር መፍጠሩ የተመለከተ ጥያቄን ሲመልሱም፣ የኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎት ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ጥገኝነት ለማላቀቅ ጥናት እየተከናወነ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

‹‹የቴሌ አገልግሎት ኤሌክትሪክ እስኪመጣ መስተጓጎል የለበትም፤›› ያሉት ሚኒስትሩ፣ የታዳሽ ኃይል የኤሌክትሪክ ምንጭን መሠረት ያደረገ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ተቋሙ ለብቻው እንዲኖረው ይደረጋል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ቴሌኮም የሚሰጣቸው አገልግሎቶች በአሁኑ ወቅት ከባንኮች፣ ከታክስ ተቋማት፣ ከሌሎች የንግድና ኢንቨስትመንቶችና ከመላው የአገሪቱ ሕዝብ ጋር የተሳሰረ በመሆኑ ጉዳዩ የህልውና ጭምርም እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

በዚህም የተነሳ አንድ ችግር በዚህ ዘርፍ ላይ ሲከሰት አገሩን ሙሉ ያንጫጫል  ብለዋል፡፡ ከአዲስ አበባ ጀምሮ እስከ ገጠር ድረስ የራሱ የኃይል ምንጭ እንዲኖረው የሚያስችል ዝርዝር ጥናት መጀመሩን ጠቁመዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት ኢትዮ ቴሌኮም 42.3 ሚሊዮን የሞባይል ደንበኞች ሲኖሩት፣ የኢንተርኔት ዳታ ተጠቃሚዎች 12.4 ሚሊዮን እንዲሁም 890 ሺሕ የመደበኛ ስልክ ደንበኞች እንዳሉት በቀረበው ሪፖርት ተመልክቷል፡፡ ይህም ኢትዮ ቴሌኮም ከአፍሪካ ሁለተኛው የቴሌኮም አገልግሎት ሰጪ እንዲሆን አስችሎታል ብለዋል፡፡


Source:Reporter



አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Eessa turre,Maalirra Geenyeerra? Kutaa 4ffaa