በኦሮሚያ ክልል የሚፈጠረውን ህገ ወጥ ተግባር ለመከላከል እና ወንጀል ፈጻሚዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል እየተሰራ ነው

በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች እየተፈጠረ ያለውን ህገ ወጥ ተግባር ለመከላከል እና ወንጀል ፈጻሚዎች ተገቢውን ቅጣት እንዲያገኙ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ገለጸ።
በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የሚታየውን ችግር ለመቅረፍ ከቀላል ወንጀል ጀምሮ እስከ ሰው ህይወት ማጥፋት የፈጸሙ ወንጀለኞችን፥ ተከታትሎ በቁጥጥር ስር በማዋል ለህግ የማቅረቡ ስራ እየተከናወነ መሆኑንም ኮሚሽኑ ገልጿል።

ከዚህ ጋር ተያይዞም ሰኞ ዕለት ደምቢዶሎ ከተማ አንድ ነፍሰጡር እናት ወደ ሆስፒታል በመጓዝ ላይ እያለች፥ ቤተሰቡ ላይ በተፈጸመ ጥቃት የነብሰ ጡሯ እናት ህይወት ሲያልፍ በቀሪዎቹ አራት ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱ ይታወሳል።

ይህን ተከትሎም ከጥቃቱ ጋር በተያያዘ በወቅቱ በጥበቃ ላይ የነበሩ ሶስት የጸጥታ አካላት በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ መጀመሩን፥ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሸን ኮሚሸነር አለማየሁ እጅጉ ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈም ቅዳሜ ሐምሌ 7 ቀን 2010 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ይከናወን የነበረውን የኤርትራውን ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን የአቀባበል ሥነ ሥርዓት ለመዘገብ ወደ አዲስ አበባ በመጓዝ ላይ በነበሩ፥ የድሬዳዋ የጋዜጠኞች ቡድን ላይ ጥቃት የፈጸሙ አካላትን በቁጥጥር ስር ለማዋል ምርመራ እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

ወንጀለኞችን ተከታትሎ ለፍርድ የማቅረብ ስራ ተጠናክሮ ቀጥሏል ያሉት ኮሚሸነሩ በአጠቃላይ በክልሉ እየተከሰቱ ያሉ ወንጀሎችን ለመከላከል እየተሰራ ነው ብለዋል።

ወንጀለኞችን ወደ ህግ በማቅረቡ ተግባር ላይም ህብረተሰቡ በንቃት እንዲሳተፍም ጠይቀዋል።

በቀጣይም ይህን መሰል ተግባር እንዳይከሰት እና የህግ የበላይነት እንዲከበርም የክልሉ ፓሊስ ከምን ጊዜውም በላይ ተጠናክሮ እንደሚሰራም ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

 Source:Fana Broadcasting Corporate(FBC)

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Eessa turre,Maalirra Geenyeerra? Kutaa 4ffaa