ምክር ቤቱ የኦዲት ግኝት ባለባቸው ተቋማት ላይ ልዩ ክትትል እንደሚደርግ ገለፀ

የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የኦዲት ግኝት ባለባቸው ተቋማት ላይ ልዩ ክትትል እንደሚደርግ ገለፀ
የኦዲት ግኝት ያለባቸው መስሪያ ቤቶች ላይ ልዩ ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያደርግ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ገለፀ።
የፌደራል ዋና ኦዲተር በ2009/2010 የኦዲት አስተያየት መሰረት የጎላ ችግር ያለባቸው 53 ተቋማት እና አስተያየት መስጠት ያልተቻለባቸው ስምንት ተቋማት አንዳሉ ይፋ አድርጎ ነበር።
እነዚህን ተቋማት ካሉበት ዝቅተኛ የኦዲት ደረጃ እንዲወጡ የማድረግ ስራ እንደሚሰራ ቋሚ ኮሚቴው ገልጿል።
በ2008 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ የተቆጣጣሪና ህግ አስከባሪ መስሪያ ቤቶችን የያዘ የኦዲት ግኝት የባለ ድርሻ አካላት ፎረም አደራጅቶ እየሰራ እንደሆነ የቋሚ ኮሚቴው ዋና ሰብሳቢ ወይዘሪት ወይንሸት ገለሶ ተናግረዋል።
ቋሚ ኮሚቴው ዛሬ ከባለድርሻ አካላት ጋር ባደረገው ውይይት በህግ የተሰጣቸውን ስልጣንና ተግባር መሰረት በማድረግ ጠንካራና የተቀናጀ ዕቅድ በማዘጋጀትና ቋሚ የግምገማ ስርዓትን በማበጀት ተጠያቂነትን በሚያረጋግጥ መንገድ መስራት እንደሚገባ ተገልጿል።
የኦዲት ግኝቶች ከአመት አመት እየጨመረ መምጣቱ እና የመጠን ልዩነት ካልሆነ በስተቀር ከችግሩ ነፃ የሆነ የመንግስት ተቋም የሌለ መሆኑን በክትትልና ቁጥጥር ስራ መረጋገጡን ቋሚ ኮሚቴው ገልጿል።
የጥሬ ገንዘብ ጉድለት፣ውዝፍ ተሰብሳቢ ሂሳብ መኖር፣ የተሟላ ማስረጃ ሳይቀርብ በወጪ ተመዝግቦ የተገኘ ሂሳብ መኖር፣ ህግን ያልተከተሉ ክፍያዎችና ግዥዎች መፈፀም ለኦዲት ክፍተት ምክንያት መሆናቸው ተገልጿል።
አብዛኞቹ ኦዲት ተደራጊ መስሪያ ቤቶች በኦዲት የተሰጡ አስተያየቶችን መሰረት በማድረግ ማስተካከያ እርምጃ እየወሰዱ አለመሆኑም እንዲሁ።
በውይይቱ ለኦዲት ግኝቱ መንስኤው የባለበጀት መስሪያ ቤቶች በቂና ብቁ የሂሳብ ሰራተኛ አለመኖሩ የችግሩ አንዱ ምክንያት መሆኑ ተነስቷል።
ሁሉም መስሪያ ቤቶች ላይ እንዴት የኦዲት ግኝት ክፍተት ሊኖር ቻለ? የሚለው መጠናት እንዳለበት እና ችግሮቹ ሳይከሰቱ ምክክር ማድረግ አስፈላጊ ነው ተብሏል።
ክፍተት ባለባቸው መስሪያ ቤቶች ላይ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ክስ መመስረት እንዳለበትም ተጠይቋል።
ቋሚ ኮሚቴው በበኩሉ የኦዲት ግኝቶች በምክር ቤቱና ከምክር ቤቱ ውጭ ሀላፊነት ባላቸው አካላት አጀንዳ እንዲሆን በተደረገው ጥረት አጀንዳ ማድረግ እንደተቻለና የኦዲት ግኝቶችን በተቋማቸው የማያርሙ አስፈፃሚዎች በስራቸው መቆየት የማይችሉበት አሰራር እየተዘረጋ መሆኑን ገልጿል።
ክፍተት ባለባቸው መስሪያ ቤቶች የባለ ድርሻ አካላት በተገኙ የኦዲት ጉድለቶች ላይ በቅንጅት ክትትልና ቁጥጥር እንደሚያደርግ ዋና ሰብሳቢዋ ወይዘሪት ወይንሸት አረጋግጠዋል።
የተጠራቀሙ ተሰብሳቢ ሂሳቦችን መፍትሄ እንዲያገኙ ማድረግና ተደጋጋሚ ችግር እንዳይፈጠር የህግና የአሰራር ማሻሻያ እንዲደረግ ድጋፍ ይደረግላቸዋል ብለዋል።
የፍትሃብሄርና ወንጀል ነክ ባህሪ ባላቸው የኦዲት ግኝቶች ላይ ክስ የመመስረት ስራ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።
በመንግስት በኩል የኦዲት ግኝት ችግሮችን መፍትሄ ለመስጠት የተለየ ትኩረት መሰጠቱን ጠቁመው ሁሉም የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች የየራሳቸውን እቅድ በማቀድ ለኦዲት ግኝት መፍትሄ ለመስጠት እየተረባረቡ ነው ብለዋል።

Source: /ኢዜአ/

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Obbo Muktaar Kadir pireezidaantii Mootummaa Naannoo Oromiyaa ta’uun lammata filataman