ስኳር ኮርፖሬሽን ሜቴክ በያዛቸው ፕሮጀክቶች ላይ

ስኳር ኮርፖሬሽን ሜቴክ በያዛቸው ፕሮጀክቶች ላይ ዕርምጃ እንዳይወስድ በከፍተኛ አመራሮች ዛቻና ማስፈራሪያ ይደርሰው እንደነበር ገለጸ
‹‹እኛን በየመድረኩ ማስጨነቅ ተገቢ አይደለም›› የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ

የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) የያዛቸውን አንዳንድ የስኳር ፕሮጀክቶች ውል በማቋረጥ ለማስቆም ሲሞከር የፕሮጀክቱን ባለቤት የስኳር ኮርፖሬሽን አመራሮች፣ ‹‹ይህ ማለት ከግንብ ጋር መጋጨት ነው፣ ወዮላችሁ አርፈችሁ ተቀመጡ፤›› የሚሉ ዛቻና ማስፈራሪያዎች ሲደርሷቸው እንደነበር የስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ እንዳወቅ አብቴ ይፋ አደረጉ።
በፓርላማው የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኮርፖሬሽኑን ሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ሰኞ ሰኔ 25 ቀን 2010 ዓ.ም. በገመገመበት ወቅት ነው ሥራ አስፈጻሚው ይህንን የተናገሩት።
የቋሚ ኮሚቴው አባላት የስኳር ፕሮጀክቶቹ ለበርካታ ዓመታት መጓተታቸውን በመጥቀስ፣ ኮርፖሬሽኑ እንደተቋም የሚጠበቅበትን ዕርምጃ አለመውሰዱን ተችተዋል።
ለፕሮጀክቶቹ መጓተት መንስዔና ተጠያቂ መሆን የነበረበት አካል እየታወቀ፣ በኮርፖሬሽኑ አመራሮች ላይ ተደጋጋሚ ትችት መሰንዘር በመቀጠሉ የተበሳጩ የሚመስሉት አቶ እንዳወቅ፣ ‹‹ይህ ቋሚ ኮሚቴ ሳይቀር እኛ የገጠመንን ችግር ግልጽ አድርገን ካስረዳነው በኋላ ፕሮጀክቶቹን ተዘዋውሮ ጎብኝቶ በቴሌቪዥን ለሕዝብ በተላለፈ ዜና ሜቴክን ሲያደንቅ አልነበረም ወይ? የኦሞ ኩራዝ ፋብሪካ 80 በመቶ ደረሷል፣ ወደ መገባደዱ ነው ብሎ መግለጫ አልሰጠም ወይ?›› ሲሉ በጥያቄ ኮሚቴውን ወቅሰዋል።
‹‹ከእኛ አቅም በላይ ከሆነ ምንም ማድረግ አንችልም፣›› ያሉት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ ‹‹ሁሉም በየፊናው አጨብጭቦ ካደነቀ በኋላ እኛን በየመድረኩ ማስጨነቅ ተገቢ መስሎ አይታየኝም፡፡ ይህ ማለት ግን የሚመለከተንን ኃላፊነት አንወስድም ማለት አይደለም፤›› ብለዋል።
Source:Reporter

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Eessa turre,Maalirra Geenyeerra? Kutaa 4ffaa