ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በነገው ዕለት ወደ አሜሪካ ያቀናሉ

የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በነገው ዕለት ወደ አሜሪካ ያቀናሉ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሎስ አንጀለስና በዋሽንግተን ዲ ሲ በሚኖራቸው ቆይታ ከኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ይወያያሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከነገ ጀምሮ እስከ ሐምሌ 24 ቀን ድረስ ነው በአሜሪካ ቆይታ የሚያደርጉት።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉዞ የመንግስት ለመንግስት ግንኙነትን መሰረት ያደረገ ሳይሆን፥ በአሜሪካ ከሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጋር ተገናኝተው መወያየትን ዋና ዓላማው ያደረገ መሆኑን የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
“ግንቡን እናፍርስ ድልድዩንም እንገንባ” በሚል መሪ ቃል የሚያደርጉት ጉዞ በአጠቃላይ በአሜሪካ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን፥ በሀገራቸው እየተካሄደ ላለው ሁለንተናዊ ለውጥ አካል ሆነው ለሀገሪቱ ልማትና እድገት አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ያለመ ነው ተብሏል።
ከዚህ ባለፈም ኢትዮጵያውያኑና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ በሃገሪቱ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ተሳታፊ በመሆን ራሳቸውንና ሀገራቸውን እንዲጠቅሙ በማለም የሚካሄድ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀምሌ 21 ቀን በዋሽንግተን ዲ ሲ እና ሀምሌ 22 ቀን በሎስ አንጀለስ ከተማዎች ሁሉም ወገን የሚሳተፍባቸው ጉባዔ የሚያደርጉ ይሆናል።
ሁለቱ ከተሞች በምስራቁና በምዕራቡ የአሜሪካ ግዛቶች የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ወደ አቅራቢያ ማዕከል ለማሰባሰብ አመች በመሆናቸው ለጉባኤው መመረጣቸውም ነው የተሰማው።
በተለያዩ ግዛቶች የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይን በየአካባቢያቸው ለመቀበል ፍላጎት ያሳዩ ቢሆንም፥ ካለው ጊዜ አንፃር ግን ሁሉንም ለማዳረስ አዳጋች በመሆኑ ሁለቱ ከተሞች መመረጣቸው ተገልጿል።
በመሆኑም በመካከለኛው አሜሪካ የሚገኙ ወገኖች በሚያመቻቸው ሁኔታ እንዲሳተፉ ተጋብዘዋል።
በህዝባዊ ጉባዔው የፖለቲካ አመለካከት፣ ሀይማኖት፣ ብሄር፣ ወዘተ ሳይለያያቸው ሁሉም ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን እንዲሳተፉም ጥሪ ቀርቧል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉብኝታቸው ከአቡነ መርቆርዮስ ጋር ተገናኝተው የሚወያዩ ሲሆን፥ ሁለቱ ሲኖዶሶች እያካሄዱ ባለው እርቀ ሰላም ላይ በቦታው በመገኘት ድጋፋቸውን እንደሚሰጡም ታውቋል

Source:Fana Broadcasting Corporate(FBC)

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Eessa turre,Maalirra Geenyeerra? Kutaa 4ffaa