ከተማው ወደ ጐን መለጠጡን ያቆማል

ቅይጥ ግንባታዎች አፓርታማዎችን ማካተት አለባቸው
ፋብሪካዎች ከመሀል ከተማ ይወጣሉ
ቤተ መንግሥትና መከላከያ ሚኒስቴር ሙዚየም ይሆናሉ
ከተማው ወደ ጐን መለጠጡን ያቆማል

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አሥረኛውን ማስተር ፕላን በይፋ ተግባራዊ ለማድረግ ዝግጅቱን ማጠናቀቁን አስታወቀ፡፡ አስተዳደሩ በተዘጋጀው ማስተር ፕላን ላይ ሰኔ 27 ቀን 2008 ዓ.ም. ከሚዲያና ከሕዝብ ግንኙነት ባለሙያዎች ጋር ውይይት አድርጓል፡፡
በዚህ ውይይት ላይ በቀረበው ጥናታዊ ጽሑፍ የመኖሪያ ቤቶች ችግርን በዘላቂው ለመፍታት በአሥር ዓመት ጊዜ ውስጥ 1.2 ሚሊዮን ቤቶች እንደሚገነቡ ተገልጿል፡፡ በመንግሥት ከሚገነቡት ከእነዚህ ቤቶች በተጨማሪ በግሉ ዘርፍ የሚገነቡ የንግድ ተቋማት (ቅይጥ) ከንግድና ከአገልግሎት መስጫዎች ጋር አፓርታማዎችን መገንባት እንዳለባቸው ማስተር ፕላኑ ምክረ ሐሳብ አቅርቧል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሪ ፕላን ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት፣ የመዋቅራዊ ፕላን ቡድን መሪ አቶ ታምራት እሸቱ እንደገለጹት፣ አዲስ አበባ ያላትን መሬት በቁጠባ መጠቀም አለበት፡፡ በዚህ መርህ መሠረት በተለይ ለቅይጥ አገልግሎት ቦታ የሚወስዱ ባለሀብቶች፣ ለመኖሪያ ቤት የሚሆን አፓርታማ በመገንባት ለመኖሪያ ቤት አቅርቦት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚኖርባቸው ተገልጿል፡፡
በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ ከተማ ከሚያስተዳድረው 54 ሺሕ ሔክታር መሬት ውስጥ ለማስፋፊያ የተመደበው መሬት አልቋል የሚባልበት ደረጃ ላይ መድረሱ ተገልጿል፡፡
በዚህ ምክንያት በአሥር በመቶ ውስጥ የሚተገበረው ማስተር ፕላን ትኩረቱን ሙሉ ለሙሉ መካከለኛው የከተማው ክፍል (መልሶ ማልማት) ላይ አድርጓል፡፡
በዚህ መካከለኛ ክፍል ላይ የሚገኘው በካይ ፋብሪካዎች እንዲሁም ሰፋፊ ቦታ የያዙ ኢንዱስትሪዎች ከከተማ ክልል እንዲወጡ እንደሚደረግም ተመልክቷል፡፡
ከከተማ ከሚወጡ ተቋማት መካከል በልደታ ክፍለ ከተማ ሜክሲኮ አካባቢ የሚገኘው የቢጂአይ (ቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ ፋብሪካ)፣ በቦሌ ክፍለ ከተማ የሚገኘው አምቼ የከባድ ተሽከርካሪዎች አስመጪና መገጣጠሚያ ተጠቃሾች ናቸው፡፡
ማስተር ፕላኑ እንደሚገልጸው አዲስ አበባ እንድታድግ የሚጠበቀው በኢንዱስትሪ ሳይሆን በአገልግሎት ዘርፍ ነው፡፡ ሆኖም ግን ለኢንዱስትሪ ቦታ የሚሰጠው ከፍተኛ ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ ለሚሆኑና ቦታ ለማይፈጁ፣ እንዲሁም ለአዳጊ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች ነው ይላል፡፡
በዚህ መሠረት አሁን ያለው የቦታ አሰጣጥና የኢንዱስትሪ ልማት ከዚህ ሐሳብ ጋር እንዲሄድ ማድረግ እንደሚያስፈልግ የማስተር ፕላኑ ማብራሪያ ይጠቅሳል፡፡
ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ቀርቦ ይፀድቃል ተብሎ የሚጠበቀው አዲሱ ማስተር ፕላን፣ በከተማ ደረጃ አሥር ማዕከላት እንደሚኖሩት ይገልጻል፡፡
ከእነዚህ ማዕከላት መካከል ግዮን ሆቴል፣ ፍልውኃና ብሔራዊ ቤተ መንግሥት አንድ ላይ አንድ ማዕከል እንደሚሆኑ ፕላኑ ያስቀምጣል፡፡ ግዮን ሆቴል የሆቴል አገልግሎት መስጠቱ ቀርቶ የፓርክ አገልግሎት፣ ቤተ መንግሥት ደግሞ ሙዚየም ሆኖ ከፍልውኃ ጋር በተናበበ መንገድ እንደሚለማ ማስተር ፕላኑ ያስቀምጣል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ መከላከያ ሚኒስቴርና የቸርችል ጎዳና ከብሔራዊ ቴአትር ጋር በተናበበ መንገድ ከብሔራዊ ቴአትር እስከ ቸርቸር ጎዳና ድረስ ከተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ነፃ ሆኖ ከኢትዮ ኩባ ፓርክ ጋር አንድ ላይ የሕዝብ መዝናኛና የእግረኛ መንገድ ይሆናል ተብሏል፡፡
እነዚህ አሥር ማዕከላትና የተመረጡ ፕሮጀክቶችን ለማልማት በአሥር ዓመት ጊዜ ውስጥ በአጠቃላይ 289.4 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ተገልጿል፡፡
በአጠቃላይ አዲስ አበባ ከተማ በአዲሱ ማስተር ፕላን ወደ ጐን መለጠጡን አቁሞ ወደ ላይ እንዲያድግ እንደሚሠራና፣ ለዚህም አገልግሎት ከፍተኛ ድርሻ የሚኖራቸው የውኃና የፍሳሽ መሠረተ ልማቶች ግንባታ እንደሚካሄድ ተመልክቷል፡፡
የአዲስ አበባ መሪ ፕላን ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ማቴዎስ አስፋው እንደገለጹት፣ አዲሱን ማስተር ፕላን ተግባራዊ ለማድረግ አሁን ያለው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መዋቅር ብቁ አይደለም፡፡ ይህን ጉዳይ ከግንዛቤ በመክተት መሪ ፕላን ጽሕፈት ቤት አራት ዘርፎችን በመለየት ጥልቅ ጥናት አካሂዶ፣ መዋቅር አዘጋጅቶ ለከተማው አስተዳደር መስጠቱንና የሰው ኃይል ሥልጠናም እንዲሰጥ መደረጉን ተናግረዋል፡፡
ከአቶ ማቴዎስ በተጨማሪ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባና የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ክላስተር አስተባባሪ አቶ አባተ ስጦታው ጨምረው እንደገለጹት፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አጠቃላይ የመዋቅር ለውጥ ለማድረግ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት አቋቁሞ ወደ ሥራ ገብቷል፡፡
ይህ ጥናት ሲጠናቀቅ ወረዳዎች፣ ክፍለ ከተሞች ሥልጣንና ኃላፊነት፣ እንዲሁም የከተማው አስተዳደር በፖሊሲና በስትራቴጂክ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩር የሚያስችል ሥራ እየተሠራ ሲሆን፣ በፕሮፌሽናል ሠራተኞች የሚመሩ መስኮችም ይለያሉ ብለዋል፡፡

Source:Reporter

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Obbo Muktaar Kadir pireezidaantii Mootummaa Naannoo Oromiyaa ta’uun lammata filataman