በመዲናዋ መሬት በህገወጥ መንገድ ሲወረር በዝምታ የተመለከቱና መሰረተ ልማት እንዲዘረጋ የፈቀዱ አካላት ላይ ምርመራ ተጀመረ
በአዲስ አበባ ከተማ በህገ ወጥ
መንገድ መሬት ሲወረር በዝምታ የተመለከቱ እና በህገ ወጥ መንገድ ለተገነቡ ቤቶች መሰረተ ልማት እንዲዘረጋ የፈቀዱ የአስተዳደር
አካላት ላይ ምርመራ ተጀመረ።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ
ድሪባ ኩማ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር በነበራቸው ቆይታ፥ ምርመራው ሲጠናቀቅ ችግሩ እንዲፈጠር ባደረጉ አካላት
ላይ አስተዳደራዊና ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድ ገልፀዋል።
አዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች
የከተማው አስተዳደር በህገ ውጥ መንገድ የተወረረ መሬትን ለማስመለስ እየወሰደ ያለው እርምጃ ተገቢ ቢሆንም፥ የድርጊቱ ተዋናይ የነበሩ
ከቀበሌ ጀምሮ ያሉ የአስተዳደር አካለት ሊጠየቁ ይገባል የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ
ድሪባ ኩማ በበኩላቸው፥ ከቀበሌ ጀምሮ በተለያዩ የአስተዳደራዊ እርከን ላይ የሚገኙ አካላት በህገ ወጥ መንገድ መሬት ሲወረሩ እየተመለከቱ
አሰፈላጊውን እርምጃ ባለመውሰዳቸው እንዲሁም ለተለያዩ ተቋማት የድጋፍ ድብዳቤዎችን በመፃፍ የመስረተ ልማት እንዲሟላ ያደረጉና ያሟሉ
አካላት ላይ ምርምራ ተጀምራል።
በተለይም ከቀበሌ እስከ ክፍለ
ከተማ ያለውን አስተዳደር ህገ ወጥነት በመከላከል አገልግሎቱን ለህብረተሰቡ ማድረስ ሃላፊነቱ ሆኖ ሳለ ለህገ ወጥ ድርጊቱ መስፋፋት
አስተዋፅኦ አብርክቷል ነው ያሉት ክንቲባው።
የህገ ውጥ የመሬት ወርራ በስፋት
በተከናወነባቸው ቦሌ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶ እና ኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተሞች በህገ ውጥ መንገድ መሬት ከወረሩ ግለሰቦች ጋር በተደረገው
ውይይት ላይም ተመሳሳይ ሀሳብ ተነስቷል።
በተለይም በቅርቡ በቦሌና በንፋስ
ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተሞች በህገ ወጥ መንገድ የተያዙ 9 ሺህ ይዞታዎች ለማፍረስ በተደረገ ህዝባዊ ውይይት ላይ በወረዳውና ክፍለ
ከተማው ያሉ የአስተዳደር አካላት የመስረተ ልማት እንዲዘረጋ በማድረግ መሳተፋቸው ተነስቷል።
በተጨማሪም የከተማው አስተዳደር
አስቀድሞ በመዲናዋ በመሬት አስተዳደር ዙሪያ የሚታዩ ብልሹ አሰራሮችን ስር ነቀል በሆነ መንገድ ለመፍታት ለውሰደው እርምጃ አንዱ
መመዘኛው እንደነበር ነው ከንቲባ ድሪባ የሚያንሱት።
አሁንም ለህገ ወጥ የመሬት ወረራ
መባባስ አስተዋፅኦ ያደረጉና በአገልግሎት ሰጪው ተቋማት ይሁን በአሰተዳደር አካላት ላይ የተጀመረው ምርመራ ሲጠናቀቅ አስተዳደራዊና
ህጋዊ እርምጃ የከተማው አስተዳደር ይወሰዳልም ብለዋል።
በተያያዘ በህገ ወጥ መንገድ
መያዛቸው በጥናት የተለዩ ይዞታዎችን ወደ መሬት ባንክ የመመለስ እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ከንቲባ ድሪባ አረጋግጠዋል።
ቀድመው በህገ ውጥ መንገድ የተወረሩ
ቦታዎችን ወደ መሬት ባንክ ከማስመለስ በተጨማሪም በቀጣይ በዘላቂነት መሬት በህገ ውጥ መንገድ እንዳይወረር አስተዳደሩ ስርዓት እየዘረጋ
ይገኝል ብለዋል።
የሰው ሀይሉን በአስተሳሰብና
አሰራር በመቀየር፣ ብልሹ አሰራሩን መቆጣጣጠር የሚያስችል ቴክኖሎጂ መዘርጋትና የካዳስተር ስርዓቱ ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ማድረግ ችግሩን
በዘላቂነት ለመፍታት የሚወሰዱ እርምጃዎች እንደሆኑም ከንቲባው ገልጸዋል።
በአሁኑ ጊዜ ብቁ የሰው ሀይል
የመመደብ ስራውና ቴክኖሎጂ የመዘርጋቱ ስራ እየተጠናቀቀ ይገኛል።
ባለፈው ዓመት መጨረሻ የተጀመረው
በካዳስተር ስርዓት መሬትና በመሬት ላይ ያለውን ንብረት የመመዝገብ ሂደትም 80 ሺህ ይዞታዎች ተመዝግበዋል።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ