በኤርትራ ከመሸጉ ሀይሎች መመሪያ በመቀበል በአማራና ትግራይ ክልሎች ሰላማዊ ሰዎችን የገደሉ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ
በኤርትራ ከመሸጉ ፀረ ሰላም
ሀይሎች መመሪያ በመቀበል በአማራ ክልል ሰሜን ጎንደርና በትግራይ ክልል ምእራባዊ ዞኖች ሰላማዊ ሰዎችን የገደሉና ዝርፊያ የፈፀሙ
ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ።
የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎትና
የፌዴራል ፖሊስ የጋራ የፀረ ሽብር ግብረ ሃይል ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፥ በቁጥጥር ስር የዋሉት
ግለሰቦች ኤርትራ ውስጥ መሽገው ከሚገኙ የፀረ ሰላምና አሸባሪ ሀይሎች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት በመፍጠርና መመሪያ በመቀበል በአማራ
ክልል ሰሜን ጎንደር ዞን ጠገዴ ወረዳ ሶሮቃና ቁርቢ አካባቢ እንዲሁም ትግራይ ክልል ምዕራባዊ ዞን ፀገዴ ወረዳ ደንሻና አካባቢው
ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ናቸው።
በአከባቢዎቹ በጦር መሳሪያ በመታገዝ
ሰኔ 21 ቀን 2008 ዓመተ ምህረት ከምሽቱ 2 ሰዓት አካባቢ በአንድ ሰላማዊ ሰው ላይ ግድያ መፈጸማቸውን መግለጫው ጠቁሟል።
እንደዚሁም አንደ ሌላ ግለሰብን
አፍነው ከወሰዱ በኋላ ለሁለት ሳምንታት በገንዘብ ሲደራደሩ መቆየታቸውም ነው የተመለከተው።
በተለይም በሰሜን ጎንደር ዞን
ጠገዴ ወረዳ ሶሮቃና ኩርባ አካባቢ የሚያልፉ የህዝብና የመንግስት ተሽከርካሪዎች ላይ ተደጋጋሚ ተኩስ በመክፈት ጥቃት በመፈፀም የህብረተሰቡን
ሰላማዊ እንቅስቃሴ አደጋ ላይ እንዲወድቅ ሲያደርጉ የነበሩ መሆናቸውን ነው ግብረ ሃይሉ የጠቆመው።
ግብረ ሃይሉ ይህንንም በመረጃና
በማስረጃ ካረጋገጠ በኋላ የፍርድ ቤት መያዣ ትዕዛዝ በማውጣት ሀምሌ 05 ቀን 2008 ዓመተ ምህረት ጠዋት አብዛኞቹ በቁጥጥር ስር
መዋላቸውን አስታውቋል።
ከመካከላቸው ሁለት ተጠርጣሪዎች
ግብረ ሃይሉ ላሰማራቸው የፀጥታ ሃይሎች እጅ ላለመስጠት ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸውን ነው ያመለከተው።
እነዚህ ተጠርጣሪዎች ሴቶችንና
ህፃናትን ከለላ በማድረግ በመንግስት ፀጥታ ሀይሎች ላይ የመሳሪያ ተኩስ በመክፈትና ቦንብ በመወርወር ጉዳት አድርሰዋል።
በህግ አስከባሪዎች ላይ ተኩስ
ከከፈቱት ሁለቱ ተጠርጣሪዎች መካከል አንዱ በመኖሪያ ቤቱ የነበረውን ሰው ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ተኩሶ በመግደል መሽጎ ከነበረበት
በማምልጥ ለጊዜው ተስውሯል።
ሁለተኛው ተጠርጣሪ ቤተሰቡን
እና ልጆቹን በጋሻነት አግቶ በመያዙ ግለሰቡን በቁጥጥር ስር ለማዋል የተሰማራው የፌደራል ፖሊስ ልዩ የጸረሽብር ቡድን በቤተሰቡ
እና በልጆቹ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ባሳየው ገደብ ያለፈ ትዕግስት ምክንያት ተጠርጣሪ ወንጀለኛው አጋጣሚውን ተጠቅሞ በተኮሰው ጥይት
አንድ የልዩ ጸረ ሽብር ቡድኑ አባል መገደሉን መግለጫው ጠቅሷል።
ይህው ግለሰብ የተፈጠረውን ግርግር
በመጠቀም ለተባባሪዎቹ ባስተላለፈው የድረሱለኝ ጥሪ ተባባሪዎቹ ወደ አካባቢው በምምጣት ፎቅ ላይ በመውጣት በከፈቱት ተኩስ በሁለት
የልዩ ቡድን አባላት የሞት በሌሎች አምስት አባላት ላይ ደግሞ የመቁሰል ጉዳት አድርሰዋል።
እስካሁን ድረስ ባለው መረጃ
በተፈጠረው ግርግር በተባራሪ ጥይት የአንድ ሰው ህይወት ከማለፉ በቀር በሰላማዊ ሰው ላይ የህይወትም ሆነ የንብረት አደጋ የደረሰ
የለም።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ