የቆሻሻው ፖለቲካ አጀንዳና ጀዋር መሃመድ
ከሰሞኑ ሰንዳፋና አካባቢዋ የሚገኙ አርሶ አደሮች የፊንፊኔ ደረቅና ፈሳሽ ቆሻሻ በእኛ ላይ መጣል የለበትም በማለታቸው በየእለቱ ከፊንፊኔ መንደሮች ተሰባስቦ ወደ ሰንዳፋ ተወስዶ ይጣል የነበረው ቆሻሻ አዚሁ ፊንፊኔ ውስጥ ተጠራቅሞ እንዳለ አለ።
በቅንነት ለሚያስብ ሰው የአርሶ አደሮቹ እምቢታ ተገቢና ትክክለኛ ነው፤ነገር ግን የሰንዳፋና አካባቢዋ አርሶ አደሮች ለፊንፊኔ ነዋሪዎች ክፉ ተመኝተው፤ፊንፊኔ በቆሻሻዋ ትግማማ፤ብክት ትበል የሚል አቋም እንደማይኖራቸው ይታወቃል በአርሶ አደሮቹ ክልከላ ማንም ቅር ሊሰኝ አይገባም አርሶ አደሮቹ ንፅህናው በተጠበቀ አካባቢ በነፃነት የመኖር ሕገ መንግስታዊ መብት አላቻውና
ይህ ሁኔታ ከሰባት ወራት ቆይታ በኋላ የተከሰተ መሆኑ ግን ነገርየው ለፖለቲካ ትርፍ መጠቀሚያነት እየዋለ እንደሆነ ቁልጭ ብሎ ይታያል።የማስተር ፕላኑ ጉዳይ ምላሽ ሲገኝ ሌላ አጀንዳ ተገኘ(በዚህ ጉዳይ ላይ ቀጥሎ የምለው አለኝ)
በአንድ ቢሊየን ብር ወጪ ተገነባ የተባለው የቆሻሻ ማስወጋጃ ላንድፊል እንደሚወራለትና ብዙ ገንዘብ ወጪ የተደረገለት መስሎ የማይታይ መሆኑን አካባቢውን ከሚያውቁ ሰዎች ጠይቄ ተረድቻለሁ።ለደረቅ ቆሻሻ ብቻ ታስቦ የተሰራው ላንድፊል የፍሳሽ፤የኬሚካል ነክ ነገሮች፤የቄራ ቅልጥምና ሌሎችም ቅንጥብጣቢዎችና ቅራቅንቦ መጣያ መሆኑ የአካባቢው ንፁህ አየር እንዲበከል ማድረጉ ይነገራል።
ይህ ችግር የፊንፊኔም የሰንዳፋም ከባድ ችግር ነው መፍትሄውም የጋራ መሆን አለበት። የአዲስ አበባ መስተዳድርና የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ባለስልጣናት በጉዳዩ ላይ በመወያየት ላይ እንደሚገኙ እየተነገረ ቢሆንም ሁለቱም በዝምታ ውስጥ መቆየታቸው ተገቢ አይደለም።በጉዳዩ ላይ በቅርቡ ከአዲስ አበባ መስተዳድር ተገኘ በሚል ምንጭ በአንድ የግል ነጻ ፕሬስ ላይ ከወጣው ቁንፅል ዜና በስተቀር እስከ አሁን ምንም የተባለ ነገር የለም፤ነገርየው ተከድኖ ይብሰል የተባለ ይመስላል።
በጉዳዩ ላይ ሕዝብ ተገቢ መረጃ እንዲያገኝ ጥረት በማድረግ ላይ የሚገኙ የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃኖች ጉዳዩ በሚመለከታቸው የአዲስ አበባና የኦሮሚያ ባለስልጣናት ምላሽ እንዲሰጥበት ጥረት ቢያደርጉም የተሳካላቸው አይመስልም፤ከንቲባውም ዝም መፅሃፉም ዝም ሆኗል ነገሩ።ብቻ ቄሱም ዝም መፅሃፉም ዝም የሚለውን ብሂል ለመዋስ ፈልገው እንዳይሆን ክቡር ከንቲባው።
እንግዲህ ዝምታው ይሰበር አካባቢውን የሚያስተዳድሩ የኦሮሚያ ባለስልጣናትም አቋማቸውን ግልፅልፅ አድርገው ለሚያስተዳድሩት ሕዝብ መንገር ይጠበቅባቸዋል ያበጠው ይፈንዳ አይነት አካሄድ ለማንም የሚጠቅም አይመስለኝም
ማስተር ፕላኑና የሰንዳፋው ቆሻሻ
ፅንፈኛውና አክራሪው ጀዋር መሃመድ የሃሰት ፕሮፓዳንዳውን መንዛት እንዲችል ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮለታል።በዚህ ምክንያት በፅንፈኛው ሚዲያ ነጋ ጠባ እየተራገበ ያለው ይህ ጉዳይ የቆሻሻው ሰው ጀዋር መሃመድ የጥላቻ ፖለቲካ ተቀባይነት እንዲያገኝ እያደረገ ይመስላል።ኦሮሚያ ከፊንፊኔ ማግኘት ስለሚገባት ልዩ ጥቅምም በዚህ ጊዜ እየተወራ ነው፤የልዩ ጥቅሙ ጉዳይ የስንፍና ነገር ሆኖ ዛሬ ነገ እየተባለ ቆይቶ ነው እንጂ የልዩ ጥቅሙ ጉዳይ በሕገ መንግስቱም ዋስትና ያገኘ ነው
ጀዋር መሃመድ ይህን ጉዳይ በማግለብለብ የፖለቲካ ትርፍ እንዲያገኝ መፈቀድ የለበትም ኦሮሚያ ከፊንፊኔ ልዩ ጥቅም እንድታገኝ የታገለና አሁንም ክልሉን በማስተዳደር ላይ የሚገኝ አካል አለ፤ይህ አካል እንዲካድ ማድረግ ኋላ ላይ ማስጠየቁ የሚቀር አይመስለኝም
ለማንኛውም አሁን ባለው ሁኔታ የማስተር ፕላኑንና የሰንዳፋውን ቆሻሻ ከጀዋር ፍላጎት ጋር በማነፃፃር ማየት ተገቢ ነው
ጀዋርና መሰሎቹ ይህቺ አገር በተቃውሞ ተበጥብጣ በሚፈጠረው ሁኔታ እነርሱ በአቋራጭ ስልጣን ላይ ጉብ ማለት ይፈልጋሉ፤በውጭም ሆነ በውስጥ የሚገኘው ኪራይ ሰብሳቢ ይህ ፍላጎታቸው ከግቡ እንዲደርስ አስፈላጊውን እገዛ እያደረጉላቸው ነው
ጀዋርና መሰሎቹ የሰንዳፋውን ጉዳይ ልክ እንደማሰተር ፕላኑ ጉዳይ ከጫፍ ለማድረስ በአግባቡ እየተጠቀሙበት ነው ነጋ ጠባ በመራገብ ላይ የሚገኘው ይህ የሰንዳፋ ቆሻሻ መጣያ ጉዳይ በጊዜው ዘላቂ መፍትሄ ካላገኘ ጀዋር የሚፈልገው የብጥበጣና የቀለም አብዮት ስልት ረዥም ርቀት እንዳይሄድ ያሰጋል
በተደጋጋሚ ሁኔታ ለሕዝብ ጥያቄ በሌሎች አካላት ግፊት ዘግይቶ ምላሽ መስጠት ተገቢ አይሆንም የማስተደር ፕላኑ ጉዳይ የሕዝብ ጥያቄና ፍላጎት በመሆኑ በጉዳዩ ላይ በመምከር ዘላቂና የማያዳግም ምላሽ መሰጠቱ ተገቢ ነው የአሁኑ የቆሻሻ ጉዳይም ለቆሻሻው ፖለቲካ ትርፍ መዋል የለበትም
የማስተር ፕላኑ ጉዳይ ምላሽ አግኝቶ ፋይሉ ሲዘጋ ሌላ አጀንዳ በመፈለግ ሲባዝን የቆየው ጀዋር መሃመድ የሰንዳፋው ቆሻሻ መጣያ ጉዳይ የፖለቲካ ትርፍ እያስገኘለት እንደሆነ መገንዘብ እንዴት ያቅታል?
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ