ምርጫ ቦርድ ለቀጣዩ ሀገር አቀፍ ምርጫ የመራጮች ምዝገባ ሰነዶች ህትመትና የቁሳቁሶች ግዥ ጀመረ

ፊንፊኔ/አዲስ አበባ ታህሳስ 09/2012(TW)
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለቀጣዩ ሀገር አቀፍ ምርጫ የሚውል የመራጮች ምዝገባ ሰነዶች ህትመትና የቁሳቁሶች ግዥ መጀመሩን አስታወቀ።
ምርጫ ቦርድ ለቀጣዩ ሀገራዊ ምርጫ ከሚያደርጋቸው ዝግጅቶች መካከል አንዱ የሆነውን የመራጮችን ምዝገባ ዘመናዊ እና ተአማኒ የሚያደርግ የህትመት ስራ እንዲጀመር በትላንትናው እለት በዱባይ ስምምነት ተፈራርሟል።
የዚህ የህትመት ውል አላማም የምርጫው ሂደት አለም አቀፍ ደረጃን የጠበቀ እና አዲሱ የምርጫ ህግ ላይ የተቀመጡትን መስፈርቶች ያሟላ እንዲሆን የሚያስችል መሆኑ ተገልጿል።
እንዲሁም በምርጫ ሂደቱ ሊፈጠሩ የሚችሉ ስህተቶችን ለመቀነስና እና ማጭበርበርን ለማስወገድ የሚረዳ እንዲሆን እንዲሁም ለምርጫ አስፈጻሚዎች ለመረዳትና ለማስፈጸም ቀላል እንዲሆን ለማድረግ ያስችላል ነው የተባለው።
ስምምነት የተፈጸመበት የህትመት ስራ ከዚህ በፊት ከነበሩትና ሀገር ውስጥ ከሚደረጉ ህትመቶች የተለየ መሆኑም ተመላክቷል።
በዚህ መሰረትም ህትመቱ የመራጮች መመዝገቢያ መዝገቡም ሆነ የምዝገባ ማረጋገጫ ካርድ የራሳቸው የደህንነት ማረጋገጫ ያላቸውና ሊጭበረበሩ እና ሊባዙ የማይችሉ መሆናቸው ነው የተገለጸው።
የመራጮች ካርድ ቀሪ ያለው ሆኖ የሚዘጋጅና መራጮች ጋር ያለው ካርድ ቀሪ የምርጫ አስፈጻሚዎች ጋር የሚቀር መሆኑ በምዝገባ ወቅት ሊፈጠር የሚችል ማጭበርበርን ማስቀረት እንደሚያስችልም ተጠቁሟል።
ከዚህ ባለፈም እያንዳንዱ መራጭ በመራጮች ካርድ አማካኝነት የራሱ የሆነ ልዩ መለያ ቁጥር ያለው ሲሆን፥ ሁሉም ሰነዶች በአምስት ቋንቋ ማለትም፣ በአማርኛ፣ በአማርኛ/ትግርኛ፣ በአማርኛ/አፋን ኦሮሞ፣ በአማርኛ/ሶማሊኛ እንዲሁም በአማርኛ/ አፋርኛ የሚታተሙ ይሆናል።
ህገ ወጥ የሆነ የምርጫ እቃዎች አግባብ ባልሆነ እጅ እንዳይወድቁ እቃዎቹ የሚታሸጉበት ልዩ ቁሳቁስ ለመራጮች ምዝገባም ሆነ ለድምጽ መስጫ የሚውል መሆኑ ተገልጿል።
ከዚህ በተጨማሪም የህትመት ሂደቱ ጋር አብሮ የሚከናወነው ግዥ ጥቅል የሆነ ለመራጮች ምዝገባ የሚያስፈልግ ቁሳቁስ፣የማጭበርበር ሙከራ ካለ ሊያጋልጥ የሚችል የፕላስቲክ ቦርሳ እና የአጠቃቀም ስልጠናን እንደሚያካትት ከብሄራዊ ምርጫ ቦርድ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ይህንን ህትመት የሚያከናውነው ድርጅት ለኬንያ ፣ ለኡጋንዳ፣ ለማላዊና ለዛምቢያ የምርጫ ሰነዶችን በማተም የሚታወቅና የምርጫ ስራዎችን በልዩ ሁኔታ የሚሰራ ተቋም መሆኑ ተጠቁሟል።

VIA:FBC

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Obbo Muktaar Kadir pireezidaantii Mootummaa Naannoo Oromiyaa ta’uun lammata filataman