‹‹ዛሬ ፊታችሁ ቆሜ ስለሰላም የምናገረው የዕድል ጉዳይ ሆኖ ነው›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)

ማክሰኞ ኅዳር 30 ቀን 2012 ዓ.ም. በኖርዌይ ርዕሰ ከተማ ኦስሎ ተገኝተው የሰላም የኖቤል ሽልማታቸውን የተቀበሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ ስለጦርነት አስከፊነት ከማንም በላይ ምስክር መሆን እንደሚችሉ በማስረዳት ለሰላም ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባ ባሰሙት ንግግር ገለጹ፡፡ ከኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በአጋጣሚ ተርፈው ለዚህ ጊዜ መብቃታቸውንም በንግግራቸው አውስተዋል፡፡  
‹‹ይህን የሰላም የኖቤል ሽልማት የምቀበለው በተለይ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል በነበረው ጦርነትና የሰላም ዕጦት የመስዋዕትነት ዋጋ በከፈሉት ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ወገኖች ስም ነው፤›› በማለት ገልጸው፣ የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂም ለሰላም መምጣት ላሳዩት በጎ ፈቃደኝነት፣ እምነትና ቁርጠኝነትም በንግግራቸው ዕውቅና ሰጥተዋል፡፡
‹‹ዛሬ ከፊታችሁ ቆሜ ስለሰላም የምናገረው የዕድል ጉዳይ ሆኖ ነው፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በጦርነቱ ወቅት በአቧራማ ምሽጎች ውስጥ ከዓመታት በፊት በወታደርነት ማሳለፋቸውን አስታውሰዋል፡፡ በጦርነቱ የመጀመርያው ረድፍ ላይ ሆነው በውጊያ መሳተፋቸውን አስረድተዋል፡፡
የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት በሚደረግበት ወቅት ወጣት ወታደር እንደነበሩ ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በዚህም ምክንያት የጦርነትን አስከፊ ገጽታ በጦርነት አውድማ ሆነው መመልከታቸው ለሰላም ቀናዒ እንዲሆኑ እንዳደረጋቸውም፣ በሽልማቱ አዳራሽ በአጽንኦት ይከታተሏቸው ለነበሩ ታዳሚዎች አስረድተዋል፡፡
ጦርነት ምን ማለት እንደሆነ በአካል ባለመመልከታቸውና ባለመሳተፋቸው የሚያገኑትና የሚያንቆለጳጵሱት ቢኖሩም፣ ‹‹እነዚህ ግለሰቦች በጦርነት ውስጥ ያለውን ፍርኃት፣ ድካም፣ ዕልቂትና የልብ መሰበር፣ እንዲሁም ከጦርነቱ መጠናቀቅና ፍጅት በኋላ ያለውን የሐዘንና የብቸኝነት ስሜትን አያውቁትም፤›› በማለት፣ የጦርነትን አስከፊ ገጽታ ከልምዳቸው ያዩትን በመጥቀስ ገልጸዋል፡፡
አዛውንቶች፣ ሴቶችና ሕፃናት በሚርከፈከፉ ጥይቶችና በከባድ መሣሪያ አረሮች ሲሸበሩና ሲርዱ መመልከታቸው አስከፊው ነገር እንደሆነ በመግለጽ፣ ‹‹በጦርነቱ ውስጥ በማለፌ ጦርነት የሲኦል ተምሳሌት እንደሆነ መናገር እችላለሁ፤›› ብለዋል፡፡
‹‹በጦርነቱ ውስጥ በተዋጊነት ብቻ ሳይሆን አስከፊነቱንና የሚያደርሰውን ሰቆቃ ታዝቤያለሁ፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ለዚህም በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት የራዲዮ ኦፕሬተር ሆነው በውጊያ ሲሳተፉ ያጋጠማቸውን እንደ ማሳያነት አብራርተዋል፡፡
‹‹ከቀበሮ ጉድጓድ ውስጥ የተሻለ ሞገድ ፍለጋ ወጥቼ ከአፍታ በኋላ ስመለስ እኔ  የነበርኩበት አሃድ ሙሉ በሙሉ ወድሞ ጠበቀኝ፡፡ በዚህም ክፉኛ ደንግጬ ነበር፡፡ እስካሁን ድረስ በዚያ ክፉ ቀን ያጣኋቸው ወጣት ጓዶቼንና ቤተሰቦቻቸውንም አስባለሁ፤›› ብለው፣ የጦርነትን ዕልቂት በቅርብ መመልከታቸው ለሰላም ለመሥራት እንዳነሳሳቸው ገልጸዋል፡፡
ጦርነት ከሰዎች ዕልቂት ባለፈ ደግሞ ለበርካቶች መፈናቀል፣ ሥራ ማጣት፣ ከአገር መባረር፣ እንዲሁም ዜግነትን ማጣት የሚያስከትል ማኅበራዊ ቀውስም እንደሚያስከትል በመግለጽ፣ የዛሬ 18 ወራት ገደማ ወደ ሥልጣን ሲመጡ ለእነዚህ ጉዳዮች መቋጫ ማበጀት ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ መወሰናቸውን አስረድተዋል፡፡
በሁለቱ አገሮች መካከል የተጋረጠው ሐሳብ ወለድ የፀብ ግድግዳ መፍረስ እንዳለበትና በምትኩም የወዳጅነትና የትብብር ድልድይ መሥራት እንደሚቻል በማመን ለፕሬዚዳንት ኢሳያስ ያቀረቡት ጥሪም ተቀባይነት በማግኘቱ የሁለቱን አገሮች ሰላም መመለስ እንደተቻለም ለታዳሚዎቹ አስረድተዋል፡፡
‹‹በዚህም መሠረት ለዕልቂት የተመዘዘውን ሰይፍ ወደ ማረሻ፣ ለውጊያ የተዘጋጀውን ጦር ደግሞ ወደ ማጨጃ በመቀየር ለሁለቱ አገሮች ዕድገትና ብልፅግና በጋራ ለመሥራት በመቻላችን አሁን የሰላምን ፍሬ በማጣጣም ላይ እንገኛለን፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያና ኤርትራ ጠላት አገሮች ሳይሆኑ ድህነት የሚባል የጋራ ጠላት እንዳላቸው የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሁለቱ አገሮች በአረጀና በአፈጀ የጥላቻ ወጥመድ ተይዘው በሚዳክሩበት ወቅት የዓለም ሁኔታ መቀየሩንና በሒደቱም አገሮቹን ወደ ኋላ ጥሎ እየተጓዘ መሆኑን በመገንዘባቸው ለሰላም ዕድል እንደሰጡ በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡
በዚህም ምክንያት ባለፉት ሁለት አሠርት ዓመታት ተለያይተው የነበሩ  ቤተሰቦች ዳግም በመገናኘታቸው፣ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ሙሉ በሙሉ በመጀመሩ፣ እንዲሁም የአየር የትራንስፖርትና የቴሌኮም አገልግሎት ዳግም በመጀመሩ አሁን የሰላም ፍሬን ማጣጣም መቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡
‹‹በአጠቃላይ ሰላም ዘላቂ ራዕይ ያስፈልገዋል፤›› ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ‹‹የእኔ ራዕይ ደግሞ ከ‹መደመር› ፍልስፍና የሚመነጭ ነው፤›› በማለት የ‹መደመር› ፍልስፍናን ለታዳሚዎቹ ገለጻ አድርገዋል፡፡ በመደመር ጽንሰ ሐሳብ ‹‹እኛ›› እና ‹‹እነሱ›› የሚባል ነገር እንደሌለ፣ ነገር ግን ‹‹እኛ›› እና ‹‹እኛ›› ብቻ መኖሩን አውስተዋል፡፡ ለዚህም በፍቅር፣ በይቅርታና በዕርቅ የጋራ መዳረሻ ይኖራል ብለዋል፡፡
‹‹በሰላም እንድታድር ጎረቤትህ በሰላም ይደር›› የሚለውን አባባል በኦሮሚኛ ቋንቋ ጭምር በመጥቀስና በሌሎች የአፍሪካ ቋንቋዎች እንደሚታወቅ ገልጸው፣ የመደመር ጽንሰ ሐሳብን አካታችነት አውስተዋል፡፡ ይህም ኢትዮጵያ ባለችበት ክፍለ አኅጉር ግንኙነትን ለማጠናከርና ከጎረቤቶች አገሮች ጋር በሰላምና በኅብር አብሮ ለመኖር እንደሚያግዝ አስረድተዋል፡፡

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Obbo Muktaar Kadir pireezidaantii Mootummaa Naannoo Oromiyaa ta’uun lammata filataman