ከፅኑ ድህነት ለመላቀቅ መፍትሔው ሥራ ብቻ ነው!
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ታኅሳስ 2 ቀን 2012 ዓ.ም. የሰላም የኖቤል ሽልማታቸውን ምክንያት በማድረግ በብሔራዊ ቤተ መንግሥት በተዘጋጀው የደስታ መግለጫ የእራት ምሽት ባደረጉት ንግግር፣ ሁሉም ሰው ወደ ሥራው እንዲሰማራ አሳስበዋል፡፡ እሳቸውም በዚያን ምሽት የሚጠብቋቸው በርካታ ሥራዎች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡ በእርግጥም ኢትዮጵያን በመሉ ኃይል ወደ ሥራ ማስገባት የግድ የሚል ወቅት ላይ ነው ያለነው፡፡ ኢትዮጵያ ከፊቷ በርካታ ሥራዎች ይጠብቋታል፡፡ ደካማዎቹን መንግሥታዊ ተቋማት ማጠናከር፣ ዕውቀትና ብቃት ያላቸውን ዜጎች በኃላፊነት መመደብ፣ የዴሞክራሲ ተቋማትን አደረጃጀት ከነፃነታቸው ጋር መልክ ማስያዝ፣ ለአገር ጠቃሚ ሐሳብና ልምድ ያላቸውን ዜጎች ማሰባሰብ፣ ለመጪው ምርጫ የሚያግዙ ተቋማዊና ሙያዊ አሠራሮችን መዘርጋት፣ በግለሰቦች ተክለ ሰብዕና ላይ ሳይሆን በተቋማት የሚመራና ተጠያቂነት ያለበት አሠራር ለማስፈን የሚረዱ ዕርምጃዎችን በተጠና መንገድ መውሰድ፣ ለአገር ሁለንተናዊ ጠቀሜታ ያላቸው የሕግ ማዕቀፎችን ሥራ ላይ ማዋል፣ ለሰላምና ለመረጋጋት መስፈን የሚረዱ ተግባራዊ ዕርምጃዎችን መውሰድና የመሳሰሉት ላይ ማተኮር ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሠሩ እንጂ ሥራ ያጡ ወገኖች ሲበዙ ችግር ይፈጠራል፡፡ በሁሉም መስኮች የተሰማሩ ወገኖች ከሕገወጥ ድርጊቶች ተቆጥበው በሕጋዊ መንገድ ብቻ እንዲሠሩ መደላድሉን ማመቻቸት፣ እንዲሁም የቁጥጥር ሥርዓቱን ማጥበቅ የመንግሥት ኃላፊነት ነው፡፡ ኢትዮጵያ የሚሠራባት አገር ትሁን፡፡
አርሶ አደሮች፣ አርብቶ አደሮች፣ ነጋዴዎች፣ ኢንቨስተሮች፣ መምህራን፣ ሐኪሞች፣ መሐንዲሶችና በተለያዩ መስኮች የተሰማሩ ኢትዮጵያውያን ሙሉ ትኩረታቸውን ሥራቸው ላይ ማድረግ ይገባቸዋል፡፡ በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በዲፕሎማሲና በመሳሰሉት የውሳኔ ሲጪነትም ሆነ ድጋፍ ሰጪነት የተሰማሩ ወገኖችም፣ በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት የሚጠበቅባቸውን መወጣት አለባቸው፡፡ ዳኞች፣ ዓቃቢያነ ሕግ፣ እንዲሁም የፖሊስ፣ የፀጥታና የደኅንነት ኃይሎች በከፍተኛ ትጋት ለአገራቸውና ለወገናቸው መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ወደ ሥራ ገብታ ውጤታማ መሆን የምትችለው ሁሉም ወገኖች ተባብረው ሲሠሩ ብቻ ነው፡፡ ለፖለቲካ ሥልጣን የሚፎካከሩ የሰላማዊ ፖለቲካውን የጨዋታ ሕግ ማክበር አለባቸው፡፡ ሥልጣን በሰላማዊ የፖለቲካ ፉክክር የሚገኝ መሆኑን መተማመን ይኖርባቸዋል፡፡ ሥልጣን በጠመንጃ ወይም በኃይል መታሰብ የለበትም፡፡ ለዚህም ሲባል መጪው ምርጫ በትክክለኛ መንገድ እንዲካሄድ በጋራ መወሰን የግድ ይሆናል፡፡ ይህ ፍላጎት ዕውን እንዲሆን ደግሞ ከምንም ነገር በላይ ለሰላም መስፈን ግንባር ቀደም መሆን አለባቸው፡፡ ከዚያ ውጪ ለሰላም መስፈን አስተዋጽኦ ሳይደረግ የግርግር ምርጫ እንዲካሄድ መጣደፍና ማጣደፍ ፋይዳ ቢስ ነው፡፡ ለኢትዮጵያም አይጠቅማትም፡፡ ፈቀቅ አያደርጋትም፡፡
በንግድና በኢንቨስትመንት መስኮች የተሰማራችሁ ወገኖች ከሸፍጥ የፀዳ ሥራ ይጠበቅባችኋል፡፡ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ የኢኮኖሚ ችግር ያለባት አገር ናት፡፡ ከዚህ ችግር መውጣት የሚቻለው በትክክለኛው መንገድ መሥራት ሲቻል ብቻ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለቁጥር የሚያታክቱ የተፈጥሮ ፀጋዎች ባለቤት ናት፡፡ የሚያነሳሳው ከተገኘ ሠርቶ ተዓምር መፍጠር የሚችል ጠንካራ ሕዝብ አላት፡፡ የተፈጥሮ ፀጋዎችን ከዕውቀትና ከጉልበት ጋር በማቀናጀትና ዘመን አፈራሽ የሳይንስና የቴክኖሎጂ ግብዓቶችን በመጠቀም፣ በአፍሪካ ግዙፍ ኢኮኖሚ መገንባት ይቻላል፡፡ ንግድና ኢንቨስትመንትን ለማቀላጠፍ የግድ ማጭበርበርና ተራ ሌብነት ውስጥ መግባት አያስፈልግም፡፡ ከአቋራጩ የአየር በአየር መንታፊነት ውስጥ በመውጣት፣ ዘላቂና አስተማማኝ ሥራ ለመጀመር መተባበር የግድ ይላል፡፡ የንግድና የኢንዱስትሪ ዘርፍ ማኅበራትን በማጠናከርና ጠንካራ የሥራ ሥነ ምግባር መመርያ በማውጣት፣ ከኋላ ቀርና ልማዳዊ አሠራር ውስጥ በፍጥነት መውጣት ተገቢ ነው፡፡ ከግብር መሰወር እስከ ተራ ሚዛን ማጭበርበርና ሌብነት ውስጥ በመውጣት፣ ለሥራ ፈጠራና ለጤናማ የንግድ ውድድር መስፈን አስተዋጽኦ ማበርከት የግድ ይላል፡፡ ለአገር አንዳች የረባ ነገር ሳያበረክቱ መሬት፣ የባንክ ብድር፣ የውጭ ምንዛሪ፣ ወዘተ ካላገኘን እያሉ በችግር ላይ ችግር መፍጠር አሳፋሪ ነው፡፡ ኢትዮጵያ እንዲህ ዓይነቶቹን የምትሸከምበት ጫንቃ የላትም፡፡ ሰልችቷታል፡፡
በተለያዩ የሥራ መስኮች የተሰማሩ ኢትዮጵያዊያን አገራቸው የሥራ ምድር እንድትሆን መጠንከር አለባቸው፡፡ ሥራ ፈትተው ሌሎችን በማስፈታት አሉባልታ የሚነዙ ሰዎችን የማስቆም ኃላፊነት እንዳላቸው ሊያውቁ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያን ወደ ኋላ ያስቀሯት ወሬና አሉባልታ ናቸው፡፡ ሰፊ ለም መሬት፣ ከፍተኛ የሆነ የውኃ ሀብት፣ በጋ ከክረምት የሚያሠሩ የአየር ፀባዮች፣ ተዝቀው የማያልቁ የማዕድን ሀብቶች፣ በአፍሪካ ተወዳዳሪ የሌላቸው በርካታ የቱሪዝም መስህቦች፣ ጠንካራና ታታሪ የሰው ኃይል፣ ወዘተ ያሏት ኢትዮጵያ ለምን የረሃብና የልመና ምሳሌ ተደረገች? በምፅዋት ጠያቂነት መዝገብ ውስጥ ለምን ስሟ በደማቁ ሠፈረ? ዘይት፣ ስኳር፣ ስንዴና የመሳሰሉትን ለምን በከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ከውጭ ታስገባለች? በምግብ ምርት ተትረፍርፋ ነጋዴ መሆን ሲገባት በምን ምክንያት ነው ገዥና ተመፅዋች የሆነችው? ወዘተ ተብሎ በአንክሮ መጠየቅ አለበት፡፡ በተፈጥሮ ፀጋዎቿ ያልተጠቀመች አገር ዜጎች መባልም ስለሚያሳፍር አሁን በመቆርቆር መነሳት የግድ ይሆናል፡፡ ሥራ ፈቶ ወሬ መለቃቀም ለማንም አይጠቅምም፡፡ የችጋርና የጠኔ ሰሌዳ ለጥፎ መንቀባረር አይቻልም፡፡ በምግብ እጥረት የሚቀነጭሩ ሕፃናት ቁጥር ከፍተኛ በሆነበት አገር ውስጥ፣ ቅድሚያ ለሥራ ካልተሰጠ እንደ አገር መቀጠል አይቻልም፡፡ የአስተሳሰብ መቀንጨር ባለበት ዕድገት የለም፡፡ ዕድገት የሚኖረው በሥራ ብቻ ነው፡፡ እስካሁን ድረስ ኢትዮጵያ ፅኑ የሆነ የድህነት አረንቋ ውስጥ የተዘፈቀችው ለሥራ የተሰጠው ክብር እጅግ በጣም ዝቅተኛ በመሆኑ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ያለባት ፅኑ ችግር በሥራ ባህል መቀረፍ አለበት፡፡
ኢትዮጵያዊያን በአርዓያነት የሚያሠራቸው መሪ ይፈልጋሉ፡፡ ይህ ዓይነቱ መሪ በዘፈቀደ አይገኝም፡፡ ብርቱ ተፎካካሪዎች ኖረው በሰላማዊና በትክክለኛ ምርጫ መለየት አለባቸው፡፡ ከመሀላቸው የተሻለ የሆነው በሕዝብ ድምፅ ይመረጣል፡፡ ‹‹ከሰው መርጦ ለሹመት፣ ከእንጨት መርጦ ለታቦት›› እንደሚባለው፣ ኢትዮጵያን ወደፊት ለማራመድ አቅሙ አለን የሚሉ በሙሉ በእኩልነትና በፍትሐዊነት የሚወዳደሩበት ዓውድ መፍጠር ይገባል፡፡ ሕዝብ በነፃነት መርጦ ይሾማል፡፡ ለዚህ ደግሞ ኢትዮጵያውያን በጋራ መሥራት አለባቸው፡፡ ሴራ፣ ሸፍጥ፣ ጥላቻ፣ መጠላለፍ፣ ሐሜት፣ አሉባልታና ክፋት ያተረፉት ውድቀት ነው፡፡ እርስ በርስ መከባበር፣ መወያየት፣ መከራከርና መደራደር በሌሉበት የሚኖረው መጠፋፋት ነው፡፡ ከቤተሰብ ጀምሮ እስከ መንግሥት የላይኛው እርከን ድረስ ሥነ ምግባር ያስፈልጋል፡፡ በሞራልና በሥነ ምግር ያልተኮተኮተ ማኅበረሰብ እንኳን ከመራር ድህነት ውስጥ ሊወጣ ህልውናውም ያጠራጥራል፡፡ ሌብነትንና አጭበርባሪነትን በይፋ የማያወግዝ ማኅበረሰብ የዘራፊዎችና የአምባገነኖች መጫወቻ ይሆናል፡፡ በአገሩ ጉዳይ አንገቱን ቀና አድርጎ ያገባኛል በማለት ተሳትፎ የማያደርግ ዜጋ ሕይወቱ ትርጉም የለውም፡፡ በጨዋነት፣ በንፅህና፣ በከፍተኛ ሥነ ምግባርና በአስተዋይነት የማይመራ ሕይወት ለአገር ፋይዳ አይኖረውም፡፡ ኢትዮጵያን በከፍተኛ ደረጃ ለማሳደግ ጊዜው አሁን ነው፡፡ ኢትዮጵያን ወደፊት ማራመድ የሚቻለው በሥራ ብቻ ነው፡፡ ከፅኑ ድህነት ለመላቀቅ መፍትሔው ሥራ ብቻ ነው!
Source:Reporter
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ