ኢትዮጵያ ውስጥ 17 የዓለም አቀፍ የሽብር ቡድን አባላት በቁጥጥር ስር ዋሉ


ፊንፊኔ/አዲስ አበባ ታህሳስ 14/2012(TW)

ኢትዮጵያ ውስጥ 17 የዓለም አቀፍ የሽብር ቡድን አባላት ጥቃት ከመፈጸማቸው በፊት በቁጥጥር ስር ማዋሉን የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ገለፀ።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጪ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የስድስት ወራት እቅድ አፈፃፀምና የተቋሙን እንቅስቃሴ ለመገምገም ዛሬ የመስክ ጉብኝት አካሂዷል።
ከጉብኝቱ በኋላ የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዳባ እና የብሔራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር ጄኔራል ኮሚሽነር ደመላሽ ገብረሚካኤል በጋራ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።
በዚሁ ወቅት ኮሚሽነር ደመላሽ እንደገለጹት፤ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት የአገሪቷን ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ በርካታ ተግባራት አናውኗል።
በተለይም የሽብር ተግባራት ለመፈፀም ሊንቀሳቀሱ የነበሩ ዓለም አቀፍ የሽብር ቡድኖችን ጥቃት ከማክሸፉም በላይ አባላቱን በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉን ተናግረዋል።
የዓለም አቀፍ የሽብር ቡድኖችም አይ. ኤስ. አይ. ኤስ እና አልሸባብ መሆናቸውን የጠቆሙት ኮሚሽነር ደመላሽ፤ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ የስለላ ተቋማት ጋር በመቀናጀት የተሳካ ስራ በማከናወን የሽብር ጥቃቱን ማስቆምና በቁጥጥር ስር ማዋል መቻሉን አውስተዋል።
በዚህም 17 የሽብር ቡድን አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጠቁመው፤ ጥቃት ለማድረስ የለዩዋቸውን ቦታዎችና የጥቃት ሰነዶች መገኘታቸውን ተናግረዋል።
አዲስ አበባ፣ ድሬዳዋ፣ ጅግጅጋ እና ሞያሌ የሽብር ቡድኖቹ የጥቃት ኢላማ ካደረጓቸው መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውንም አብራርተዋል።
በዚህ ኦፕሬሽን የተገኘውን መረጃ ለ16 አገሮች በተለይም ለአሜሪካ፣ ጣሊያን፣ ፈረንሳይ፣ ህንድና ለአንዳንድ አፍሪካ አገሮች ጭምር በማካፈል አገራቷ የሽብር ቡድን አባላት በቁጥጥር ስር ማዋል መቻላቸውን ገልፀዋል።
ተቋሙ በአጠቃላይ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ በኢኮኖሚ አሻጥሮች፣ በህገ ወጥ ገንዘብና ጦር መሳሪያ ዝውውር፣ በግብር ማጨበርበር እና ከባድ የሙስና ወንጀሎች የፈጸሙ አካላትን በመከታተልና በቁጥጥር ስር እንዲውሉ በማድረግ በኩል ውጤታማ ስራ መከናወኑን ተናግረዋል።
በዚህ ተግባር በቢሊዮን የሚቆጠሩ የአገሪቷ ሀብቶችን ማዳን መቻሉን ተናግረው፤ ተቋሙ ቀድሞ በህዝብ ዘንድ የነበረውን አሉታዊ አመለካከት ለመቀየርና ጠንካራ፣ ዘመናዊ በህግና ስርዓት የሚመራ ተቋም ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
ለአብነትም ተቋሙ አሁን ያለውን የብሔራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎት የሚለውን ወደ “ብሄራዊ መረጃ ማዕከል” በሚል ስያሜውን እንዲቀይር ሀሳብ መቅረቡን አመልክተው፤ በተጨማሪም በአዲሱ አዋጅ ውስጥ ሌሎች ማስተካከያዎች መካተታቸውን ተናግረዋል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የውጪ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዳባ በበኩላቸው፤ የቋሚ ኮሚቴ አባላት ባለፈው ዓመት ተቋሙን በጎበኙበት ወቅት ትኩረት አድርጎ ሊያከናውናቸው በሚገቡ ጉዳዮችና ዋና ዋና የሪፎርም ሀሳቦች ላይ ስምምነት መደረሱን አስታውሰዋል።
የቋሚ ኮሚቴ አባላት ባካሄዱት የመስክ ምልከታ ባለፉት ስድስት ወራት ተቋሙ ባከናወናቸው ተግባራት መርካታቸውን አስታውቀዋል።
ከዚህ ቀደም በቋሚ ኮሚቴው እና ብሔራዊ መረጃ ደህንነት አገልግሎት የነበረው መልካም ያልሆነ እና የሻከረ ግንኙነት በአገሪቷ ለውጥ ከመጣ በኋላ መስከካከሉን አንስተዋል።
ተቋሙ የአገርን ሰላምና ደህንነት ከማስጠበቅ አኳያ እየሰራ ያሉት ሰራዎች ውጤታማ መሆናቸውን ቋሚ ኮሚቴው ማረጋገጡንም አቶ ተስፋዬ ተናግረዋል።

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Eessa turre,Maalirra Geenyeerra? Kutaa 4ffaa