የፌደራል የደህንነትና የጸጥታ የጋራ ግብረ ኃይል መግለጫ
በአማራ ክልል ማዕከላዊ ጎንደር ዞን ጎንደር ከተማ ከቀብር ስፍራ ጋር በተያያዘ በክርስትናና በእስልምና እምነት ተከታዮች ዘንድ የተቀሰቀሰውን ግጭት መነሻ በማድረግ በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎችም በሃይማኖት ሽፋን ሁከትና ብጥብጥ በመፍጠር ጸረ-ኢትዮጵያ የሆኑ ሃይሎችን ፍላጎት ለማሳካት በሚንቀሳቀሱ አካላት ላይ እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን የፌደራል የደህንነትና የጸጥታ የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቋል፡፡ የጋራ ግብረ ኃይሉ ዛሬ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፥ ጸረ ኢትዮጵያ አቋም የሚያራምዱ የተለያዩ የውስጥና የውጭ ኃይሎች ብሔርን መሰረት ያደረገ የጥላቻ አጀንዳ በማሰራጨት ሃገሪቱን ወደ ቀውስ ለማስገባት ጥረት ሲያደርጉ ነበር፡፡ ህብረተሰቡ ለአመታት በገነባው ጠንካራ የሆነ የጋራ እሴት ይህ ሙከራ የከሸፈባቸው ኃይሎች ቀሪውን የሃይማኖት ካርድ በመምዘዝ በተለያዩ እምነት ተከታዮች ዘንድ መጠራጠርና ጥላቻ እንዲፈጠር ብሎም ወደ ግጭት እንዲያመራ በተለያዩ መንገዶች ሲቀሰቅሱ ቆይተዋል ብሏል መግለጫው፡፡ በጎንደር የተከሰተው ግጭት በተለያዩ ዕምነቶች መካከል ግጭት በመቀስቀስ ወደ ሃገራዊ ቀውስ እንዲያመራ የሚደረገው ሴራ አካል መሆኑን ያመለከተው መግለጫው፥ በዚህ ድርጊት በተሳተፉ አካላት ላይ ተገቢ እርምጃ መወሰድ መጀመሩን ጠቁሟል፡፡ በዚህ መሰረት በጎንደር በተከሰተው ግጭት የተሳተፉና ሁከቱን ለማባባስ የተንቀሳቀሱ 280 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉን አመልክቷል፡፡ እንደ መግለጫው፥ በጎንደር የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ በሌሎች አካባቢዎችም በተለያዩ እምነት ተከታዮች መካከል ሁከትና ብጥብጥ እንዲፈጠር የሚጋብዙ ቅስቀሳዎች እንዲሁም ሃሰተኛ መረጃዎችም በተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎች በስፋ