የሁላችንም አሻራ የሚፈልገው የሰላም ጉዳይ...
በለውጦች መካከል ሰላማችንን ሊያደበዝዙ የሚችሉ አጋጣሚዎች ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ ከሰሜን እስከ ደቡብ ፣ከምስራቅ እስከ ምዕራብ ዋልታዎች ድረስ በሁሉም አቅጣጫ የሰላምን አየር ከመተንፈስ ይልቅ ለዘመናት በፍቅርና በአንድነት ከኖረው ህዝብ ይልቅ በህዝብ ጭንብል የራሳቸው ክብርና ዝና ለማግኘት ፀብ አጫሪ ንግግሮችን በመናገር፣የተዛቡ ፅሁፎችን በመፃፍ፣ምስሎችን በማህበራዊ ሚዲያዎች በመለጠፍ ህዝብ እርስ በእርሱ እንዳይተማመን አለፍ ሲልም ቂም በማስያዝ ወደ ግጭት እንዲያመራ የሚሰሩ እፉኝቶች መኖራቸው ጥርጥር የለውም፡፡
40ኛው የአሜሪካ ፕሬዝደንት የነበሩት ሮናልድ ሬገን በአንድ ወቅት ስለ ሰላም እንዲህ ሲሉ መናገራቸው ይታወቃል፤ "Peace is not absence of conflict, it is the ability to handle conflict by peaceful means "ሠላም ጥል የሌለበት ማለት አይደለም፤ሠላም ማለት ግጭቶችን በሠላማዊ መንገድ መፍታት መቻል ማለት ነው" ብለዋል፡፡
ሀገሪቱን ለመበታተን የሚጥሩ የእነዚህንና መሰሎቻቸውን ሀላፊነት የጎደለው እኩይ ተግባር ደባ ማጋለጥ ብሎም ከመንግስት ጎን ሆኖ ሀላፊነትን መወጣት ለነገ የማይባል የዛሬ የቤት ስራ ሊሆን ይገባዋል፡፡ እያንዳንዱ አስፈፃሚ አካልም ከህዝቡ፣ከወጣቱ፣ከተማሪዎች፣ከንግዱ ማህበረሰብ እንዲሁም ከሌሎችም አካላት የሚነሱና ግልፅነት የሚፈልጉ ዙሪያ መለስ ፖለቲካዊ መፍትሄ የሚሹ ጉዳዮችን በመለየትም ለሀገራችን ሠላም ግንባር ቀደም ሚናቸውን መጫወት ይጠበቅባቸዋል፡፡
በእኛም ሀገር ቢሆን መልካም መልካም ስራዎችን ከማበረታታት ይልቅ ሰበቦችን እየፈለጉ ህዝብን ከህዝብ ለማጋጨት የሚፈልጉ እንቅፍ አጥተው የሚሰሩ ሀይሎች እንዳሉ እሙን ነው፡፡
የህዝብና የሀገር ሰላም ማጣት ለማን በጄ? ችግሮች እንኳ ሲኖሩ ተቀራርበን ለችግሮቹ መፍትሔ ማምጣት ለመንግስት ወይም ለገዢው ፓርቲ ብቻ የሚተው ሳይሆን እያንዳንዳችን የመፍትሔው አንድ አካል እንደሆን ልናስብና የጋራ ሰላማችንን በተልካሻ ምክንያት እንዳናጣው ልንረባረብ ይገባል ባይ ነኝ፡፡
መንግስት ብቻውን መፈፀም የሚችለው ስራ የለም፡፡ እያንዳንዱ ስራ የህብረተሰቡን እገዛና ቀናኢነት የተሞላበት ፍላጎት ይጠይቃል፡፡ ይህ ሲሆን ዜጎች በሰላም ወጥተው ይገባሉ፣ ስራ ሰርቶ ቤተሰብ መምራትም ሆነ፣ የሀገሪቱ ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ሳይንገራገጭ እንዲቀጥል ማድረግ ይቻላል፡፡ ለህዝባችንና ለሀገራችን ሰላም ሁሉም ዘብ ሊሆን ይገባዋል፡፡
በማወቅም ይሁን ባለማወቅ የሚንፀባረቁ የእኔነት አስተሳሰቦች ሄዶ ሄዶ መጨረሻቸው የህዝብንና የሀገርን ሰላም ማናጋት ነውና ከወዲሁ ልናስብበት ይገባል ፡፡
የሁላችንም ሰላም ከታወከ ደግሞ አገርም እንደ አገር ህዝብም እንደ ህዝብ ሊቀጥል አይችልም ፡፡ይህ አይነቱ አካሄድ ደግሞ በአብሮነታችን፣ በአንድነትና በመከባበራችን፣ በሰላማችንና በፍቅራችን ላይም ጥላሸት መቀባቱ አይቀርምና ከወዲሁ መክሸፍ ይኖርበታል፡፡
አንድነት፣ ሰላምና ፍቅርን ለማስፈን መንገድ የሚሆኑ የማስፈጸሚያ ዘዴዎች በርካታ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ከእነዚህም መካከል የኢትዮጵያውያንን ሰላም ሊያስጠብቅ በሚችል መልኩ የሰላምን ዋጋ በአግባቡ ማስረዳት ጠቀሜታው በእጅጉ ከፍ ያለ ይሆናል፡፡
ሰላማችን ሲረጋገጥ ሀገር የሰላም አየር ይነፍስባታል ፣እርግቦች በሰማይ የሰላምን አውደ ዝማሬ በሚያምር ዜማቸው ያሰማሉ፡፡ሰላም ሲኖር አንድነታችንና የእርስ በእርስ ግንኙነታችን ይበልጥ ይጎለብታል፡፡
ህዝቦችን ሊለያዩ ከሚችሉ ይልቅ አንድ የሚያደርጋቸው ብዙ ሺ ምክንያቶችን ማንሳት ለሰላማችን ዘላቂነት ቁልፍ ጉዳይ መሆኑ አይቀርምና ስለ ጋራ ሰላማችን ተገቢውን ትኩረት ልንሰጠው ይገባል ባይ ነኝ፡፡ሰላም!
/በሚራክል እውነቱ/
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ