የሳትነው መንገድ!

 

ጋዜጠኝነት እውነት ነው። ነገር ግን እውነት የሆነውን ሁሉ ላንናገርበት እንችላለን። ያ ማለት ይዋሻል ማለትም አይደለም። ነገር ግን መረጃው ወጥቶ በሀገር እና በሕዝብ ላይ የሚፈጥረውን ተጽእኖ በማሰብ ሊዘገይ ወይንም ዝም ሊባል ይችላል።/ይህ ትክክል ነው አይደለም በሚል ሲያከራክር ቆይቷል አሁንም ያከራክራል። አንዳንዶች ሁሉም ነገር እየተነገረው ሕዝቡ በራሱ ይወስን የተሻለውን ይምረጥ ይላሉ ሌሎች ደግሞ በተለይ በ3ኛው ዓለም ሀገራት ላሉ ሕዝቦች መረጃ እንደወረደ ከመስጠት በትንታኔ ማስደገፍ ወይንም ምቹ ጊዜን መጠበቅ የተሻለ ይሆናል በማለት ከማኅበረሰብ ንቃተ ሕሊና ጋር ያያይዙታል/። አንድ ወታደር በአውደ ውጊያ ላይ የያዘውን ጥይት በምን ቦታ ላይ መተኮስ እንዳለበት እንደሚያውቅ ሁሉ አንድ ጋዜጠኛም የያዘውን መረጃ በምን ሁኔታ እና ጊዜ ማውጣት እንዳለበት ጠንቅቆ ማወቅ አለበት። ያ ካልሆነ መቼ መተኮስ እንዳለበት ባለማወቅ ጥይቱን ያለአግባብ እንደጨረሰ ወታደር ካለጊዜው በራሱ ሜዳ እጅ መስጠቱ የማይቀር ነው።

አንዳንዶች የያዙትን ጥለው የእንግዳውን ሃሳብ ተከትለው ይጠፋሉ። ሌሎች ደግሞ የእኔን ካልተቀበልክ ውርድ ከራሴ በሚል ሁኔታ ካፈርኩ አይመልሰኝ የሚሉ አሉ። አንድ ጋዜጠኛ ፕሮግራም ከመስራቱ በፊት አላማ እና ግቡን ጠንቅቆ ማወቅ አለበት ይህም በሜዳው ለሚደረገው የሃሳብ ጦርነት የበላይነትን ለመያዝ ይረዳዋል። የበላይነቱ ግን ከተነሳበት አንጻር በመረጃና በማስረጃ እንጅ "ጀግንነትን" በመናፈቅ ብቻ የሚሆን አይደለም።
ይህንን ሁሉ ለምን አልኩኝ? አሁን አሁን ከቶክ ሾው ፕሮግራሞች ጋር "ባህል" እየሆነ የመጣ የውረድ እንውረድ አካሄድ መኖሩ ነው። ቃለ መጠይቁ ለምን እንደተደረገ የጠያቂውም ሆነ የጣቢያው አላማ ምን እንደሆነ ሳይገባን የሚያልቁ በርካታ ናቸው። ብዙዎቹ ማኅበራዊ ሚዲያውን እንደትልቅ የመረጃ ምንጭ የሚጠቀሙ በመሆኑ ገና ከመጠየቃቸው በሰነዘሩት "ዱላ" መልሶ የሚገርፋቸው ጥቂት አይደሉም።
hard talk ፕሮግራም ለመስራት መናፈቅ መመኘት ባልከፋ ነገር ግን በጥያቄ ድረታ እንኳን ለተጠያቂው ለጋዜጠኛው/ዋ ግልጽ ባልሆነ መንገድ እና ስርዓት አልባ መጯጯህ ግን መሆን የለበትም።
hard talk ፕሮግራሞች ተበራክተው በሕዝቡም በመንግስትም በተፎካካሪ ፓርቲዎችም ዘንድ ተጠያቂነት ቢኖር የሁላችንም ምኞት ነው። ነገር ግን ይህ የሚሆነው ማኅበረሰባዊ ኃላፊነት ያለው ፣ በሃሳብ የበላይነት የሚያምን ለዚያም ለጋዜጠኞቹ አንጻራዊ ነጻነትን የሚሰጥ ጣቢያ እና አድማጭ ፣ ትሁት ፣ በማስረጃ የበለጸገ እና እነዚያን ማስረጃዎች በተመረጡ ቦታ የሚጠቀም ባለሙያ ሲኖረን ብቻ ነው። ካለበለዚያ የተከበረውን ሙያ ቁልቁለት ይወስደው እንደሆነ እንጅ የሚጨምርለት ነገር አይታየኝም።
በስተመጨረሻ ከትናንትናው የፋና ውይይት አንደ የገረመኝን ብቻ ላንሳ። በመስቀል አደባባይ ጉዳይ ቤተ ክህነት እያለች እናንተ ማን ወከላችሁ ለምን ትጠይቃላችሁ? የሚል ጥያቄ ሲያነሳ መላሹ መልስ ያሉትን ሰጥተዋል። የእኔ ጥያቄ ግን ለራሱ ለጠያቂው ነው። ባልደራስ ይህ ጥያቄ በሚያነሳበት ሰዓት መሰረቱ አዲስ አበባ እንደሆነ ይታወቃል።ከአዲስ አበባ ከ80% በላይ ኦርቶዶክሳዊ መሆኑም እንደዛው። ታዲያ ብትመርጠኝ አስተዳድርሃለሁ ብሎ ለሚወዳደርለትን ሕዝብ ጥያቄ ካልጠየቀ ምኑን ፓርቲ ሆነው? መስቀል አደባባይስ በእርግጥ የቤተ ክህነት ጥያቄ ብቻ ነው ወይ? ከሀገሪቱ ሕዝብ ከግማሽ በላይ የሆነው ሕዝብ ጥያቄ በመሆኑ እንኳን በስስ ጎናችን ገብቶ የበላይነትን ለመያዝ ለሚሻ ማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ ቀርቶ እናንተስ መጠየቅ አልነበረባችሁም ወይ?
ልዩ ምልከታ ᎓- ጽሑፉ ፓርቲ የመደገፍ እና የመቃወም ሳይሆን የመርሕ እንደሆነ ልብ በሉልኝ!
 
 
@ (መስከረም ጌታቸው)

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Obbo Muktaar Kadir pireezidaantii Mootummaa Naannoo Oromiyaa ta’uun lammata filataman