በኦሮሚያ ክልል ወጣቱ ለፀረ ሰላም ሀይሎች ተልዕኮ ማስፈፀሚያ ከመሆን እንዲቆጠብ የክልሉ መንግስት አሳሰበ
በኦሮሚያ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች ከሰሞኑ የተከሰተውን ሁከት በቁጥጥር ስር ለማዋል ጥረት እየተደረገ መሆኑን መንግስት የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ገለፀ።
የአዲስ አበባና ፊንፊኔ ዙሪያ ኦሮሚያ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላንን እና የክልሉን የተሻሻለው የከተሞች አዋጅን ምክንያት በማድረግ አንዳንድ አፍራሽ ተልዕኮ ያነገቡ አካላት የክልሉን ነዋሪዎች ባልተገባ መንገድ በማነሳሳት ለአመፅ እና ብጥብጥ እየዳረጉ እንደሆነ ቢሮው አስታውቋል።
የቢሮው ኃላፊ አቶ ፍቃዱ በዚህ ሰሞነኛ ሁከት ዙሪያ ዛሬ መግለጫ የሰጡ ሲሆን፥ የሁከቱ መነሻ የሆነው ኦነግና ግንቦት ሰባትን ጨምሮ በሃገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ፅንፈኛ አካላት ሁለቱን አብሮ የመልማት ሃሳብን ያነገቡ ዕቅዶችን አስመልክቶ ሃሰተኛ ፕሮፖጋንዳ በማስተላለፍ እና የክልሉን ነዋሪዎች እነርሱ ለሚያስቡት ተልዕኮ ማስፈጸሚያነት ለማዋል በማሰብ መሆኑን አንስተዋል።
በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ዘንድ በተቃውሞ መልክ ይስተዋሉ የነበሩ ብጥብጦችም እያደጉ መጥተውና ከዩኒቨርሲቲዎችም ወጥተው በክልሉ የተለያዩ ከተሞች ላይ መታየት ጀምረዋል ነው ያሉት።
በሁከቱ ውስጥም ተሳትፎ የሚያደርጉ ጦር መሳሪያ ሁሉ የታጠቁ አካላት መኖራቸው መረጋገጡን ሀላፊው ገልፀዋል።
በዚህ መልኩ የተፈጠረውን ሁከት ተገን በማድረግም በአንዳንድ አካባቢዎች ማረሚያ ቤት በመስበር እስረኞችን ለማስመለጥ የተደረገ ጥረትም እንደነበር እና የፀጥታ ኃይሎች ባደረጉት ያላሰለሰ ጥረት ግን እስረኞችን የማሰመለጡ ተልዕኮ መክሸፉን ነው ያመለከቱት።
እንደ ሀላፊው ከዚያ ባለፈ በተቃውሞ ሰበብ ለክልሉ ህዝብና ለሃገርም ጥቅም የሚሰጡ ፋብሪካዎች ላይ ጥቃት የማድረስና ፋብሪካዎችን ለማቃጠል የሚደረግ ሙከራም ተስተውሏል።
እነዚህ አካላት የኦሮሚያ ክልል ሉዓላዊነት እንደተጣሰና መሬቷም ለአዲስ አበባ እንደተሰጠ በማስወራት ወጣቶችን ለዓላማቸው እየመለመሉ እንደሚገኙ ገልፀዋል።
በተቃውሞ ሰልፎች ላይ የጦር መሳሪያ የታጠቁ ሰዎች በፀጥታ ኃይሎች ላይ ጭምር ጥቃት እየሰነዘሩ መሆኑም በመግለጫው ላይ አንስተዋል።
ሁከቱ በተለይም ትናንት ላይ ትንሽ ረገብ ያለ ቢመስልም አሁንም ግን በሃገር ንብረት ላይ ከፍተኛ ውድመት ለማድረስ እየተንቀሳቀሱ መሆኑን አቶ ፍቃዱ ተናግረዋል።
እስካሁን ባለው በንብረት ላይ ከደረሰው ጉዳት በተጨማሪ የአራት ሰዎች ህይወት ማለፉን በመንግስት ተጣርቶ መረጋገጡን ነው የገለፁት ።
ከዚህም ባለፈ በፀጥታ ኃይሎች እና ይህን ተቃውሞ በማይደግፉ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጨምሮ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት እየደረሰ መሆኑንና የክልሉ መንግስትም ሁከቱን በቁጥጥር ስር ለማዋል የተቻለውን ሁሉ እያደረገ እንደሚገኝ የቢሮ ኃላፊው አስታውቀዋል።
እነዚሁ አፍራሽ አካላት ግን በሁከቱ የጠፋውን የሰው ህይወት አጋኖ በማስወራት ጭምር ሁከትና ብጥብጡን ለማፋፋም ጥረት እያደረጉ መሆኑም ታውቋል ብለዋል የቢሮ ኃላፊው።
በአሁኑ ወቅትም አንዳንድ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ወደ እለታዊ የመማር ማስተማር ሂደት ውስጥ እንደገቡና ተደናግጠው ልጆቻቸውን ከየዩኒቨርሲቲው ያስወጡ ወላጆችም ልጆቻቸው ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመልሱ አቶ ፍቃዱ ጥሪ አቅርበዋል።
የክልሉ ወጣትም ከሁከቱ ጀርባ ያለውን አፍራሽ ዓላማ ተረድቶ ራሱን የእነዚህ የፀረ ሰላም ሀይሎች ተልዕኮ ማስፈፀሚያ ከመሆን እንዲጠብቅ ነው ያሳሰቡት።
ህብረተሰቡም የሁከትና የብጥብጥ መነሻው የሃገሪቱን ብሎም የክልሉን ልማት በማይፈልጉ ሰዎች የተቀነባበረ መሆኑን ተገንዝቦ አፍራሽ ተልዕኳቸው እውን እንዳይሆን የተለመደ ትብብሩን እንዲያደርግ የቢሮ ሀላፊው ጠይቀዋል።
በአንዳንድ ልማትን በማይደግፉ አካላት የክልሉን ህልውና ይገዳደራል በሚል የሚገለፀው ማስተር ፕላኑ፥ የክልሉን ከተሞች ከአዲስ አበባና ከሌሎች የክልሉ ከተሞች ጋር በመሰረተ ልማት፣ በንግድ እና ኢንቨስትመንት ለማስተሳሰር እንዲሁም የተፈጥሮ ሃብቶችን በጋራ ለመንከባከብና በጋራ ለመጠበቅ፣ የአካባቢ ብክለትን ለመቆጣጠር፣ ወንጀለኞችን በጋራ ለመከላከል፣ ያለመ በመሆኑ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት ያልተገባ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ያሉትን ሊታገል እንደሚገባ አቶ ፍቃዱ ጠይቀዋል።
በአጠቃላይ ማስተር ፕላኑ በጋራ መልማት ላይ ያተኮረ እና ከተሞች ተቀናጅተው ፈጥነው እንዲለሙ የህዝቡን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማሳደግ እና ወደ ኢንዱስትሪ መር የሚደረገውን ሽግግር ለማፋጠን ያለመ እቅድ በመሆኑ ሁሉም ሊደግፈው እንደሚገባ ነው ያነሱት።
በእርግጥም ይህ ማስተር ፕላን የማይመቸው ልማትን ለማይፈልጉ ወገኖች ብቻ መሆኑን ጨምረው ገልፀዋል።
ሌሎች ግዙፍ አገራዊ እቅዶች ህዝባዊ ውይይት ተደርጎባቸው ወደ ተግባር እንደሚገቡ ሁሉ፥ ማስተር ፕላኑም ውይይት ሳይደረግበት እና ከህዝብ እውቅና ውጪ የሚፈፀም አለመሆኑን እና አሁንም ለውይይት ክፍት እንደሆነ የቢሮው ሀላፊ አስታውቀዋል።
ከማስተር ፕላኑ ባለፈ የኦሮሚያ ክልል ከተሞችን የተመለከተው የክልሎች ማሻሻያ አዋጅ፥ ቀደም ሲል የክልሉ ከተሞች የሚሰበስቡትን ገቢ ለክልሉ ገቢ ካደረጉ በኋላ ዳግም በጀት ይበጀትላቸው እንደነበር አስታውሰው፥ የተሻሻለው አዋጅ ግን በከተሞች የሚሰበሰበው ገቢ በቀጥታ ለራሳቸው ለከተሞቹ ልማት እንዲውል የሚፈቅድ መሆኑን አስረድተዋል።
በከተሞች የነበረውን የከተማና ቀበሌ አስተዳደር በመባል የሚታወቁትን የአስተዳደር እርከኖች ለአስተዳደር እንዲያመችና የህዝቡን ጥያቄዎች በአፋጣኝ መመለስ እንዲያስችል ከሁለቱ መሃል የወረዳ አስተዳደር እንደ ሶስተኛ የአስተዳደር ዕርከን ተደርጎ እንዲዋቀር የሚፈቅድ ነው ብለዋል።
ከዚህም ባለፈ በክልሉ ያሉ የገጠር ቀበሌዎችን በዚያው ክልል ካሉ አጎራባች ከተሞች ጋር በልማት ለማስተሳሰር ያለመ እንጂ ፌደራሊዝምን የሚቃረንና የክልሉን ሉዓላዊነት የሚጥስ አለመሆኑን ሁሉም ሊገነዘብ ይገባል የሚል መልዕክትም አቶ ፍቃዱ ተሰማ አስተላልፈዋል።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ