የህዝብ ውግንና በጥፋት አይገለጽም
በኢፌዴሪ ህገ መንግሥት አንቀጽ 30 ንዑስ አንቀጽ 1 እንደተደነገገው ማንኛውም ሰው ከሌሎች ጋር በመሆን መሣሪያ ሳይዝ በሰላም የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነፃነትና አቤቱታ የማቅረብ መብት አለው። በዚህም መሰረት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በተዘረጋባት ኢትዮጵያ ህዝቡ የልማት፣ የዴሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ባገኛቸው አጋጣሚዎችና መድረኮች፣ በጥቆማ፣ በውይይት መድረኮች፣ ጉዳዮቹ ባስ እያሉ ሲመጡም በሰላማዊ ሰልፍ ሲያነሳ ቆይቷል። እያነሳም ይገኛል።
መንግሥትም ይህን መሰረት በማድረግ ከህዝቡ እንዲሁም ከተወካዮቹ ጋር በጥያቄዎቹ ላይ በመምክር በርካታ የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ ጥያቄዎች እንዲመለሱ አድርጓል። በሀገሪቱ በልማትና በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ተጠቃሽ የሆነ ውጤት ማስመዝገብ የተቻለውም የህዝቡን ጥያቄና ፍላጎት መሰረት በማድረግ በተከናወኑ ተግባሮች ነው። መንግሥት የህዝብ ውግንና ያለው በመሆኑ የህዝብ ትክክለኛ ጥያቄዎች በተገቢው መንገድ እየመለሰ መጥቷል። ወደፊትም ይህን ተግባሩን አጠናክሮ ይቀጥላል።
ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ ከተማ እና ከኦሮሚያ ክልል ፊንፊኔ ልዩ ዞን የተቀናጀ ማስተር ፕላን ጋር ተያይዞ የክልሉ ተማሪዎች ጥያቄ ማቅረባቸው ትክክለኛ ነው። መንግሥትም በተማሪዎቹና በህዝቡ ፕላኑን አስመልክቶ እየቀረቡ ያሉ ጥያቄዎች ተገቢ መሆናቸውን አረጋግጧል።
የተማሪዎቹና የህዝቡ ጥያቄ ግን ብቻውን አደባባይ እንዳይወጣ ተደርጓል። የልማት ጥያቄ በምንም ዓይነት መልኩ ልማትን በማውደም ሊቀርብ አይገባም፤ የሆነው ግን ልማትን ማውደም የሰው ህይወት ማጥፋት ነው። ፀረ ሰላም ኃይሎች የህዝቡን በሰላም የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ ነጻነትና አቤቱታ የማቅረብ መብት ተገን በማድረግና መሣሪያ ይዘው ጭምር አደባባይ በመውጣት እኩይ አጀንዳቸውን ለማራመድ ተጥቅመውበታል።የህዝብ ውግንና የሌላቸው ሃይሎች ስለሆኑ ህዝባዊ ተቋማት ላይ በማነጣጠር ውድመት አድርሰዋል። የጥፋት ኃይሎች ከጥፋት ሌላ ተግባር የላቸውምና።
ተማሪዎችና ህዝቡ እያነሱ ያሉት ጥያቄም የፀረ ሰላም ኃይሎች እኩይ ተግባር ማራመጃ ለመሆን ተገዷል። ለእዚህም ፀረ ሰላም ኃይሎቹ ያሰማሯቸው ኃላፊነት የጎደላቸው ኃይሎች በተለያዩ የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች የፈጸሟቸው እኩይ ድርጊቶች ማሳያዎች ናቸው። እነዚህ ኃይሎች በፈጸሙት እኩይ ተግባር የሰዎች ህይወት ጠፍቷል፤ የህዝብና የመንግሥት ንብረት ወድሟል። የህዝብ የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ለስጋት ተዳርጓል። በእንዲህ ዓይነት ተግባር የተሠማራ ኃይል እንዴት ህዝባዊ ውግንና አለው ይባላል?
የህዝብን ጥያቄዎች ተገን በማድረግ ለእኩይ ዓላማቸው የሚንቀሳቀሱ ፀረ ሰላም ኃይሎች የጥፋት ድርጊታቸውን ለማራመድ ያልተንቀሳቀሱበት ወቅት እንደሌለ ይታወቃል። መንግሥት ከህዝቡ ጋር በመሆን እነዚህ ኃይሎች በህዝቡ ውስጥ ተሰግስገው እኩይ ዓላማቸውን ለማራመድ በተንቀሳቀሱ ቁጥር ከህዝቡ በመነጠል የሸረቧቸውን ሴራዎች በመበጣጠስ የህዝቡን የልማትና የዴሞክራሲ ጥያቄ እየመለሰ ሀገሪቱን አሁን ላለችበት የዕድገት ደረጃ አብቅቷል። ህዝባዊ ውግንና ያለው እና በህዝብ የተመረጠ መንግሥት በመሆኑ ይህን ተግባሩን አጠናክሮ ይቀጥላል።
በአንፃሩ ግን «ባልበላም እጭራለሁ»
አለች እንደተባለችው እንስሳ የህዝቡን ይሁንታ ያጡ ፀረ ሰላም ኃይሎች እንደ እባብ አፈር እየላሱ እየተነሱ ዛሬም የጥፋት ዓላማቸውን ማራመዳቸውን ቀጥለዋል። ለእዚህም ይህ በኦሮሚያ ክልል የተማሪዎችና የህዝቡ ጥያቄ ላይ ተንጠልጥለው ሊያራምዱ እየሞከሩ ያሉት እኩይ ተግባርና እያደረሱት ያለው ጥፋት ተጨባጭ ማሳያ ይሆናል። ከመቼ ወዲህ ነው ግን በሰው ህይወትና በህዝብ ተቋማት ላይ ጥቃት በማድረስ የህዝብ ተቆርቋሪነት መገለጫ የሆነው?
የእነዚህን ፀረ ሰላም ኃይሎች እኩይ ዓላማ በየትኛውም መልኩ ሊወገዝ እየፈጸሙት ባሉት የጥፋት ተግባርም ተጠያቂ መሆን አለባቸው። እንዳለፉት ጊዜያት ሁሉ እኩይ ዓላማቸው ለማምከን በመጀመሪያ ተግባራቸውን ለይቶ ማወቅ ይገባል። በገሃድ የታየው ተግባራቸው የፀረ ሰላምና ልማት ኃይል መሆናቸው ነው።
ለሁከት መነሻ የሆነው ማስተር ፕላን በረቂቅ ደረጃ ያለና ህዝቡ ከፈለገ ሊያሻሽለው ካልፈለገም ሊጥለው እንደሚችል መንግሥት በተደጋገሚ ገልጿል። ህዝባዊ መንግሥት በመሆኑ ከህዝባዊ ባህሪው በመነሳት ህዝብን ያደምጣል። የህዝብን ጥያቄም ይመልሳል።
ረቂቅ ማስተር ፕላኑ በህዝቡ ዘንድ በቂ ግንዛቤ ስላልተያዘበት ከ2006ዓ.ም ጀምሮ በወቅቱ በነበረበት ደረጃ መቆሙ ይታወቃል። አጀንዳው ፕላኑ ቢሆን እንኳ አሁን የተከሰተውን በሰው ህይወትና ንብረት ላይ የደረሰው ጉዳት ማስከተል አልነበረበትም። በውይይት የሚፈታ ጉዳይ ነውና። ነገር ግን ፀረ ሰላም ኃይሎች አጋጣሚዉን ለእኩይ ዓላማቸው ለማዋል በመንቀሳቀሳቸው ጉዳቱ ሊደርስ ችሏል። የእዚህ ድርጊት ተዋናይ የሆኑ ፀረ ሰላም ኃይሎች ሊወገዙ ይገባል። ህዝብን ሰላም በመንሳትና የህዝብን ሀብት በማውደም የህዝብ ውግንና አይገለጽም።
የህዝቡ ትክክለኛ ጥያቄ በፀረ ሰላም ኃይሎች ለእኩይ ተግባር እየዋለ መሆኑን ለህዝቡ በማስገንዘብም አምርሮ እንዲታገላቸውና እኩይ ተልዕኳቸው እንዲከሽፍ ለማድረግ ሁሉም መንቀሳቀስ አለበት።
የክልሉ መንግሥትና የኢፌዴሪ መንግሥት እየወሰዱ ያሉትን እርምጃ ተከትሎም ተማሪዎችና ህዝቡ ከመንግሥት ጋር እየመከሩ ይገኛሉ። ፀረ ሰላም ኃይሎች ግን አሁንም የገበያ ግርግር ለሌባ ይመቻልን ተጠቅመው እኩይ አጀንዳቸውን ለማስፈጸም ያለ የሌለ ኃይላቸውን እየተጠቀሙ ህይወት እንዲጠፋ፣ በህዝቡ ጥያቄ ብዙ ሀብት ፈሶባቸው የተገነቡ የልማት ተቋማትና ተሽከርካሪዎች እንዲወድሙ እያደረጉ ነው። ይህን ለማስቆም ህዝቡ ከፀጥታ ኃይሎች ጋር በመሆን የመከላከል ሥራዎን አጠናክሮ መቀጠል አለበት።
እነዚህ የእኩይ ድርጊት አራማጆች እንዳለፉት ጊዜያት ሁሉ የእጃቸውን እንዲያገኙ ከህዝቡ በመነጠል ላይ በትኩረት በመሥራት መንግሥት በቀጣይ ለሚወስዳቸው እርምጃዎችም ምቹ ሁኔታ መፍጠር ያስፈልጋል። ከዚህ አኳያም የተማሪዎችና የህዝቡ ሚና ከፍተኛ ነው። ይህ ፀረ ልማትና ፀረ ሰላም ኃይሎች ከህዝቡ የመነጠል፣ ተከታታይ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራዎች የማከናውን፣ በህግ እንዲጠየቁ የማድረግ ሥራ በማከናወን የህዳሴ ጉዞ ማስቀጠል ይገባል። ይቻላልም። የህዝብ ውግንና በጥፋት እንደማይገለፅም በሚገባቸው ቋንቋ ሊነገራቸውም ይገባል።
Sorce:Addis Zemen
Sorce:Addis Zemen
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ