ካስቀመጥኩት ቦታ ላጣሁት ለአንዲ

 


የማከብርህ የማደንቅህ አንዷለም አራጌ ሆይ ሰሞኑን በምትሰጣቸው ቃለመጠይቆችህ ከፍታህ "ተጠየቅ" ውስጥ እየገባ መሆኑን እየተመለከትኩ ነው። እንዲህ ያስባሉኝን ምክንያቶች ከንግግርህ የቀነጨብኳቸውን ነጥቦች በማቅረብ ጥያቄን አስከትላለሁ
1_ ብርሀኑ ነጋ ከብልፅግና ይልቅ ሚስቱንና ልጆቹን ብትተችበት ይመርጣል።
ነጋ ጠባ የፈጣሪን ስምና ቅዱስ ቃሉን እንደ ህይወት ፈለግህ ስታነበንብል የነበርክና እኛም ፈሪሀ እግዚአብሄር አለው ብለን የመሰከርንልህ አንዷለም፦ በዚህ ደረጃ መውረድ እንዴት ተመቸህ? ካልጠፋ ምሳሌ ለምን ልጁንና ባለቤቱን መረጥክ? እርግጥ ነው ብሬ ከቤተሰቡም ከነፍሱሞ በላይ ሀገሩን እንደሚያፈቅር አውርቶ ሳይሆን ሆኖ አሳይቷል። ከሰማይ በታች ለሱ ከሀገር በላይ የለም። አቶ አንዷለም ንፅፅሮችህ እውነት ቢሆኑ እንኳን በሀገር ጉዳይ አንተ ያመንክበትን የተከበሩ ባለቤትህ ባያምኑበት ባንተስ በሌላውስ አይተቹም ማለት ነው? ለመሆኑ ዶክተር ናርዶስና ዶር አለም እዚህ ጋ መምጣት ነበረባቸው?
_ትዝ ካለህ ከሆነ ከመአዛ መሀመድ ጋ በነበረህ ቃለመጠይቅ "እራሳችንን በአብይ ጫማ ውስጥ አስገብተን መመልከት አለብን" አላልክም? ባንድ በሌላ መድረክ ላይ "አብይን የመሰለ መሪ" እያልክ ስታንቆለጳጵሰውስ አልነበረም? ሌላው ቀርቶ እኔና ሰላሳ የምንሆን የፅናት ለኢትዮጲያ አባላት ጋብዘንህ ሳለ "በሚፈጠሩት ግድያዎችና መፈናቀሎች ዙሪያ ለምንድነው መግለጫ የማታወጡት" ብለን አጥብቀን ስንጠይቅህ ምን ብለህ ነበር የመለስክልን? "አብይ መታገዝ አለበት አብሮ ከመስራት ውጪ አማራጭ የለንም። አሁን ባለንበት ተጨባጭ ሁኔታ ብልፅግና ላይ እኛም ከዞርንበት ፅንፈኞቹ አቅም ያገኛሉ። ሀገራችን ቀጭን መስመር ላይ ስላለች ሌላ ጫና መሸከም አትችልም። ቢያንስ ገላጋይ ለመሆን ብዙ መታገስ አለብን" ብለህ ብዙዎችን አላሳመንክም?
2_ ብርሃኑ ነጋ በኢዜማም ሆነ በግ7 ተተኪ የማፍራት ባህሉ የላቸውም
ለመሆኑ የአግ7 አመራሮችን ታውቃቸዋለህ? የምር ግን እነዚህን ለሰማይ ለምድሩ የከበዱ፣ የትኛውም የአለም ክፍል ላይ ተለምነው መስራት የሚችሉ ጉምቱ ሰዎች አመራር ለመሆን ብቁ አልነበሩም ብለህ ታስባለህ? ለመሆኑ እነዚህን ሊቃውንት 'አቅምን በተመለከተ' ትክ ብለህ ባይንህ ሙሉ ታያቸው ዘንድ ይቻልሀል? ኢዜማስ ውስጥ እንደነ አርክቴክት ዮሀንስን የመሰለ የሞራል ልእልና ያለው ሰው ምክትሉ ያደረገ ሰው እንዴት በዚህ ይታማል? በርካታ ትንታግ ወጣቶች ኢዜማ ት/ቤታችን ነው እያሉ ሲመሰክሩ አላየንም፣ አላነበብንም። አንዲ፦ አንተም እኮ የዛሬ 3 አመት "ለመሪነት አልወዳደርም ከሳቸው መማር እፈልጋለሁ" ብለህ ነበር ደሞ በእስሩም በትግሉም ታውቀዋለህ። ታዲያ እንዴት ነው ባህሉ ካልነበራቸው ከሳቸው የምትማረው? ደሞም እኮ መሪ ነበርክ ወንድም አለም? ማንን አፈራህ? ራስህን ጠይቀህ ታውቃለህ? ማፍራቱ ይቅርና ባለፉት 3 አመታት ምን ያህል ጊዜ ነው ቢሮህ ላይ የተገኘኸው?
3_ ኢዜማ ውስጥ በመሆኔ፣ ከፕሮፌሰር ብርሀኑ ጋ አብሬ በመስራቴ ብዙ ውርደት ደርሶብኛል ይሄ ደሞ ያስጨንኛል።
ጓድ አንዷለም ገጥመን መስሎኝ? ድሮስ በዚህ ዘመን የዜግነት ፖለቲካን እያራመድክ ላትሰደብ ነበር እንዴ? ብርሀኑ የዜግነት ፖለቲካን ባያራምድ ይህ ሁሉ ስድብ ይዥጎደጎዱበት ነበር ብለህ ታስባለህ? በስድብ የሚፍረከረክ ፅናት ይዘህ ነው እንዴ ትግሉን የምትመራው? የቆምክለትን መርህ እንዴት በመንጋ ስድብ ተጠየቅ ውስጥ ታስገባዋለህ? ያመንክበትን አላማ የሚወስነው የደጋፊ ቁጥር ነው ወይ? ረጅም ማለም/ማሰብ ማለት ላንተ ምንድነው?
ውድ አንዷለም የሰሞኑ ቀናት ላንተ ጥሩ አልነበሩም። ማንንም ማጣት ባንፈልግም ይበልጥ ልናጣቸው ከማንሻቸው ሰዎች አንተ አንዱ ነህ።ዛሬ ለሀገራችን ጮሁ፣ ተንጫጩ፣ ታሰሩ፣ ተፈቱ የሚባል አይነት ዘመኑን የማይመጥን ትግል አይጠቅማትም። ከውስጥም ከውጪም አንገቷ ላይ ምሳር ያጋደመው መአት ነው። የድርጅት አቅምን አጠናክሮ ጠንካራ ተፎካካሪ መሆን ላይ ማተኮር ነው ብልህነት። ብልፅግናን ይበልጥ ልትገዳደረው የምትችለው ተቋም ግንባታ ላይ አድምተህ ስትበረታ ነው። ኢዜማን ለመምራት ከፕሮፌሰር ብርሀኑ የተለየ አቅም አለኝ ካልክ በጨዋነትና በሞራል ከፍ ብለህ ግጠም። የቀድሞ ባልንጀራህን ልደቱን ይመስል በየሜዲያው እየተሽከረከርክ ስብእናህንም፣ ኢዜማንም፣ የዜግነት ፖለቲካንም ኢትዮጲያንም አትጉዳ። ጠቅላላ ጉባኤው ላይ ተከራክረህ የመጣውን ውጤት ከመቀበል ይልቅ በግለሰቦች ስብእና ላይ ተረማምዶ በጡዘት ስልጣን ለመያዝ መሞከር ከምናውቀው አንዷለም ስብእናና ታሪክ ጋ የሚጣጣም አይደለም።
(እኔማ አንዴንዴ ያቺ አንዷለም እስክንድር ነጋና በቀለ ገርባ የታሰሩባት ክፍል ምን መተት ተደርጎባት ይሆን ሌላ ጊዜ ደሞ ምን አቅምሰዋቸው ይሆን እያልኩ እስከ ማሰላሰል ደርሻለሁ። እንቁዎቻችንን ሁሉ እየተነጠቁ አለቁ እኮ ጎበዝ?)
በመጨረሻም ጥቂት ጥያቄዎችን ላቅርብና ልሰናበት። ለመሆኑ በነማን እንደተከበብክ ልብ ብለሀል ወይ አንዲ? በ360፣ በባልደራስ፣ በቤተ አማራና በህወሃት ዲጂታሎች እኮ ነው። ለመሆኑ የኢዜማ ምርጫ ለነሱ ምናቸው ነው? ካንተ መመረጥስ ካሁኑ ያሰሉት ትርፍ ምንድነው? ለምንስ ከኢዜማ በላይ ኢዜማ ሆነው ተከሰቱ? አንተስ በነዚህ በከበቡህ ቡድኖች ምቾት እየተሰማህ ነው ወይ?

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Obbo Muktaar Kadir pireezidaantii Mootummaa Naannoo Oromiyaa ta’uun lammata filataman