እየተለወጠች ያለችው አዲስ አበባ የሀገሪቱ መሪ ምኞት ማሳያ ናት -ዘ ኢኮኖሚስት
አዲስ አበባ የሀገሪቱ መሪ ምኞት ማሳያ ናት ሲል “ዘ ኢኮኖሚስት” የተሰኘው ታዋቂው የእንግሊዝ መጽሔት ዘግቧል።
ዘ ኢኮኖሚስት በዘገባው በሀገሪቱ ግጭት የነበረ ቢሆንም ከተከሰቱ ግጭቶች ጎን ለጎን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ አዲስ አበባን እየገነቡ ነው ሲል አስነብቧል፡፡
መጽሔቱ በቅርብ ጊዜ ተጠናቆ ለአገልግሎት የበቃውን የወዳጅነት ፓርክ ፕሮጀክትን እንደማሳያነት የጠቀሰ ሲሆን፥ የወዳጅነት ፓርክ የአዲስ አበባ አዲሱ የሕዝብ ማዘውተሪያ እና ተወዳጅ መዝናኛ ስፍራ መሆኑን ገልጿል፡፡
በፓርኩ ሲራመዱ የኢትዮጵያን የወደፊት እጣ ፈንታ ይመለከታሉ፣ ለስላሳ የፒያኖ ሙዚቃዎች አየር ላይ ይደመጣሉ፣ አዳዲስ ተጋቢዎች በሚያብረቀርቀው ሰው ሰራሽ ሐይቅ አጠገብ ፎቶ ይነሳሉ በማለት የፓርኩን ውበት አወድሷል፡፡
ከብዙ ፕሮጀክቶች በተጨማሪ በተያዘው ዓመት አንድ ትልቅ የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት መከፈቱን እና በአጠገቡ የሳይንስ ሙዚየም እንዲሁም ቴአትር ቤቶችም እተገነቡ መሆኑን ዘ ኢኮኖሚስት ሽፋን ሰጥቷል፡፡
የተለያዩ መሪዎች የተለያዩ ሐውልቶችን እና ህንፃዎችን ይገነቡ እንደነበር የሚያትተው መጽሔቱ፥ የተሰሩት
ህንጻዎች፣ መንገዶች እና የሕዝብ ቦታዎች በግዛት፣ በጦርነት እና በአብዮት ትሩፋቶች የተቀረፁ ስለመሆናቸው አስረድቷል፡፡
ያለፉት መንግስታት በራሳቸው ምስል ከተማዋን ለመገንባት ሞከረዋል ያለው ዘገባው፥ ከ2018 ጀምሮ ወደ ስልጣን የመጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ግን ከተከሰቱ ውስጣዊ ችግሮች ጎን ለጎን፥ ዘመን ተሻጋሪ ፕሮጀክቶችን በመገንባት ላይ መሆናቸውን አብራርቷል፡፡
የከተማዋ ነባር መሠረተ ልማቶች እድሳት እየተደረገባቸው ነው፣ የመንግስት መስሪያ ቤቶች ተለውጠዋል፤ የሕዝብ አውራ ጎዳናዎች በቀለማት ያሸበረቁ እና በአበባ ያጌጡ ሆነዋል፤ ታሪካዊው የመስቀል ዓደባባይ በ73 ሚሊየን ዶላር ውጪ እድሳት ተደርጎበታል፤ ይህ የሆነው ግጭት ስታስተናግድ በነበረች ሀገር ነው ሲልም ዘኢኮኖሚሰት ትዝብቱን አስፍሯል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ "አዲስ አበባን መቀየር ከቻልክ በእርግጠኝነት ኢትዮጵያን መለወጥ ትችላለህ" ሲሉ የተናገሩትን ቃለ በመጥቀስ፥ ፕሮጀክቶቹ የፖለቲካ ተሃድሶው ውጤት እና የብሔራዊ አንደነት ማሳያ ስለመሆናቸውም መጽሔቱ አትቷል፡፡
ከቀድሞው የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ መጽሔቱ አገኘውት ባለው መረጃም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የተገነቡ የሕዝብ መዝናኛ ስፍራዎች እና ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን መንግስት ገፅታ የሚያሳዩ ናቸው ብለው ያመናሉ ሲልም ያስረዳል፡፡
ከእነዚህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፕሮጀክቶች በተጨማሪ፥ በሀገሪቱ በስንዴ ልማት ዘርፍ እየተገኘ ያለው ለውጥም ከሰሞኑ የአፍሪካ ልማት ባንክን በመሰሉ ተቋማት አድናቆት የተቸረው መሆኑ ይታወቃል።
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ