በወቅታዊ ሀገራዊ የደኅንነትና ጸጥታ ጉዳዮች ዙሪያ በመምከር፣ ከብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት የተሰጠ መግለጫ


የተከበራችሁ የሀገራችን ሕዝቦች፣
ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤት፣ ከአንድ ወር በፊት፣ ሚያዝያ 14 ቀን 2014 ዓ.ም.፣ ሀገራዊ የጸጥታ ሁኔታን በጥልቀት መገምገሙ ይታወሳል። በዚያ ግምገማውም እንደ አልሸባብ፣ ሸኔና ጁንታ ያሉ የሽብር ኃይሎችን ሁኔታ ተመልክቷል። ከኮንትሮባንድ፣ ከሕገ ወጥ ታጣቂዎች፣ ከጽንፈኛ የሚዲያና የፖለቲካ ቡድኖች፣ ከአክራሪ ሃይማኖተኞችና ከሙሰኞች የሚመጡ ፈተናዎች በሀገር ላይ ያስከተሉትን ሥጋት ተመልክቷል። የመንግሥት መዋቅር የጥራትና የቁርጠኝነት ችግሮች እንደታዩበትም ገምግሟል። እንዲሁም የውጭ ጠላቶቻችንን ሤራና የውክልና ጦርነቱን ሁኔታ በጥልቀት መርምሯል።
ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤቱ በሚያዝያ ወር ባደረገው ስብሰባው እነዚህ ፈተናዎች በሀገርና በሕዝብ ላይ ያሳደሩትን ሥጋትና ፈተና በሚገባ ተንትኖ አስቀምጦ ነበር። የሕዝቡ የደኅንነት ሥጋትና ሀገራዊ አለመረጋጋት መባባሱን፤ ሕዝብ በመንግሥት ላይ እምነት እንዲያጣ እየተደረገ መሆኑን፤ በሃይማኖትና በብሔር አክራሪነት የተነሣ የሀገርን አንድነት ለመሸርሸር እየተሠራ መሆኑን፤ የሕገ ወጥ ታጣቂዎች ዐቅም እየጨመረ የሕጋዊ መዋቅሮች ዐቅም እየደከመ መምጣቱን፤ የሕገ ወጥ ታጣቂዎች መበራከትና መጠናከር ለኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴው ፈተና መሆኑን፤ ሕገ ወጥ ቡድኖቹ የሕዝቡን ሰብአዊና ማኅበራዊ መብቶች እየጣሱ ሕዝብ መሰቃየቱን፤ በጠቅላላ ሥርዓት አልበኝነት እንዲስፋፋ ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረለት መሆኑን፤ ይህም ለውጭ ጠላቶቻችን ዕድል እንደፈጠረላቸው፤ ነገሩ በአስቸኳይ ካልተስተካከለ ሀገርን ወደ ከፋ አደጋ እንደሚያስገባ በሚያዝያ ስብሰባው መገምገሙ ይታወቃል።
እነዚህን ችግር ፈጣሪዎችና በሕዝቡ ላይ ያንዣበቡ ፈተናዎች በዝምታና በትዕግሥት ማየቱ አደገኛውን ቀይ መሥመር እንዲታለፍ እንደሚያደርግ ታምኖበት ነበር። መንግሥት ችግሮችን በሆደ ሰፊነት እያለፈ፣ በጊዜ ብዛት ቀስ በቀስ ለማረም የተከተለው ስልት እንደ ድክመትና ዐቅመ ቢስነት መታየቱን የደኅንነት ምክር ቤቱ አረጋግጧል። ሕዝቡ በተለያዩ ጊዜያት በተደረጉ ውይይቶችና በተወካዮቹ አማካኝነት መንግሥት ጠበቅ ያለ የሕግ ማስከበር ሥራ እንዲሠራ እየወተወተ መሆኑን ምክር ቤቱ ተመልክቷል። ችግሮችን በውይይት፣ በሀገር ሽማግሌዎችና በሃይማኖት አባቶች በኩል ለማረም የተደረጉ ጥረቶች መጠነኛ ውጤት ማምጣታቸውን ተረድቷል። የተወሰኑ አካላት በሕጋዊ መሥመር ለመሥራት መወሰናቸውን፤ ወደ መደበኛ የጸጥታ ተቋማት ገብተው ለመሠማራት መወሰናቸውን ተገንዝቧል። አንዳንድ አካላትም ወደ ሰላማዊ ኑሮ ለመመለስ ያደረጉትን ውሳኔ በሚያዝያው ስብሰባው በክብር ተቀብሎት እንደነበር ይታወሳል።
መንግሥት የሰጠውን የሰላም ዕድል ያልተጠቀሙና በሕገ ወጥ ተግባራት ከመሠማራት ያልተቆጠቡ አካላትን በተመለከተ የደኅንነት ምክር ቤቱ በሚያዝያ ወር ባደረገው ውይይት የሚከተሉትን አቅጣጫዎች አስቀምጦ ነበር፡-
• በተደራጁና ያለፈቃድ በታጠቁ ቡድኖች ላይ ሕግን የማስከበር ሥራ መሠራት እንዳለበት፣
• በሁሉም አካባቢዎች የሚታዩ ሕገ ወጥ ተግባራት በፍጥነት መስተካከል እንዳለባቸው፣
• በየአካባቢው የሕዝብ ቅሬታ ምንጮች የሆኑ ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በፍጥነት ማስተካከል እንደሚገባ፣
• ግጭት ቀስቃሽና ጽንፈኛ የሚዲያ አካላት፣ የፖለቲካ ቡድኖችና አክቲቪስቶች ሕጋዊውን ሥርዓት ብቻ እንዲከተሉ የሚያደርግ ሥራ መሥራት እንደሚያስፈልግ፣
• የመንግሥትን መዋቅር በማጥራት፣ ሚናውን ለይቶ በቁርጠኝነት እንዲሠራና ሕዝብና መንግሥት የጣሉበትን ኃላፊነት እንዲወጣ የሚያደርግ ተግባር እንዲከናወን አቅጣጫዎች ተቀምጠው ነበር።
በዚህ መሠረት የተከናወኑትን ተግባራት ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤቱ ረቡዕ ሰኔ 1 ቀን 2014 ዓም ባደረገው ስብሰባ በጥልቀት ገምግሟል። በግምገማውም መሠረት የመንግሥትን ኃይልን በብቸኝነት የመጠቀም ሕጋዊ ሥልጣን የሚገዳደሩ ኃይሎችንና የሕገ ወጥነት ተግባራትን ወደ ተገቢው ሥርዓት የማስገባቱ ሥራ በታቀደለት መንገድና በተሻለ ጥራት እየተከናወነ መሆኑን፤ ሥራውም የታለመለትን ግብ እያሳካ እንደሆነ አረጋግጧል።
በኦሮሚያ ክልል በተከናወነው አኩሪ ሥራ የሸኔን ልዩ ልዩ ቡድኖች በመደምሰስ፣ ሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎችን በማምከን፣ በጠላት እጅ የነበሩ አካባቢዎችን መልሶ በመቆጣጠር፣ መዋቅሩን በማጥራት፣ ሕዝብን በማወያየትና በማሰለፍ ውጤታማ ሥራ መከናወኑን ለማወቅ ተችሏል። በሺዎች የሚቆጠሩ የሸኔ አባላት መገደላቸውን፣ መማረካቸውንና በፈቃዳቸው እጅ መስጠታቸውን ከሪፖርቶቹ ተረጋግጧል። አያሌ የጦር መሣሪያዎችና ቁሳቁሶች ከሸኔ አባላት ተማርከዋል። መንግሥታዊ መዋቅሩን በሚገባ በማጥራት፣ ለአመራር ብቁ የማድረግ ተግባር በመልካም ሁኔታ ተከናውኗል።
በአማራ ክልል በተሠሩ ሥራዎች ሕዝቡን ለእፎይታ ያበቁ ተግባራት መከናወናቸውን የደኅንነት ምክር ቤቱ ገምግሟል። በዚህም መሠረት ከጸጥታ ተቋማት የከዱ አባላትን በመያዝ፣ በተለያዩ ወንጀሎች የተሳተፉ አካላትን በቁጥጥር ሥር በማዋል፤ ተበትነው ለጸጥታ ሥጋት ሲሆኑ የቆዩ የጦር መሣሪያዎችን በማሰባሰብ፣ በሕገ ወጥ ተግባር ተሠማርተው የነበሩ አክቲቪስቶችን ሥርዓት በማስያዝ፣ ሕዝቡ የሰላምና የጸጥታው አካል እንዲሆን አወያይቶ በማሰለፍ፣ የተሻለ ሥራ መሠራቱን ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤቱ ተመልክቷል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተደረገውን ሰላምና ጸጥታ የማስፈን እንቅስቃሴ ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤቱ በገመገመበት ወቅት አበረታች ሥራዎች መከናወናቸውን ተገንዝቧል። የታጠቁ ሽፍቶችን ሥርዓት ከማስያዝና ከመደምሰስ አንጻር፣ ሕገ ወጥ ተግባትራን ከመቆጣጠር፣ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያዎችን ከመሰብሰብ፣ የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደ ቦታቸው ከመመለስ አንጻር የተከናወኑ ተግባራት ለውጥ ያመጡ መሆኑን ለመመልከት ተችሏል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ በደቡብና በጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥታትም የታጠቁና የተደራጁ ሽፍቶችን መልክ ከማስያዝ፣ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን ከመግታት፣ በተለያዩ ማኅበረሰቦች መካከል የሚከሠቱ ግጭቶችን ከማስቀረትና ከመፍታት፣ ሕገ ወጥ ተግባራትን ከመቆጣጠር፣ የመንግሥት መዋቅርን ከማጥራት አንጻር ሥራዎቹ በታቀዱት መሠረት መከናወናቸውን አረጋግጧል። በሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትና በኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች ሊደረግ ታስቦ የነበረው የአልሸባብ እንቅስቃሴ በጸጥታ አካላት ቅንጅት መክሸፉን ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤቱ ተመልክቷል። አልሸባብ ከጁንታውና ከሸኔ ጋር በተደጋጋሚ ሊያደርጋቸው የሞከራቸው ትሥሥሮች በተጠና የጸጥታ አካላት ኦፕሬሽን እንዲመክኑ መደረጋቸውን አረጋግጧል።
ዓለም አቀፍ የሚዲያ ትኩረትን ለመሳብ የሚሞክሩ የጥፋት ኃይሎች በመዲናችን አዲስ አበባ ላይ የተለያዩ የጥፋትና ጸጥታ የማደፍረስ እንቅስቃሴዎችን በተደጋጋሚ ሲሞከሩ የጸጥታና የደኅንነት ተቋማቱ የተናበበ አካሄድ እንዳከሸፈው ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤቱ ገምግሟል። በዝርፊያና በከተማ ወንጀሎች ላይ ተሠማርተው የከተማውን ነዋሪዎች ሲያማርሩ የቆዩ አካላትን ተከታትሎ በሕግ ጥላ ሥር ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራትም ውጤታማ ለውጥ ማምጣታቸውን የደኅንነት ምክር ቤቱ ተመልክቷል።
ከላይ የተገለጡት ሰላምንና ጸጥታን የማስከበር ሥራዎች በቁርጠኝነትና በመሥዋዕትነት የተከናወኑ ናቸው። ለዚህም በሥራ የተሳተፉትን ሁሉ ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤቱ ያመሰግናል። የፖለቲካ መዋቅሩ ከጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የፈጸሙት የሀገርን አንድነት፣ ሰላምና ብልጽግና የማረጋገጥ ሥራ ውጤታማ የሆነው መላው ሕዝብ በዓላማው አምኖ፣ በሥራው አብሮ በመሰለፉ መሆኑ ይታመናል። ኢትዮጵያ ሕዝቦቿ በነጻነትና በሰላም የሚሠሩባት፣ የሚንቀሳቀሱባትና የሚያመርቱባት ሀገር እንድትሆን ሕገ ወጥነት በምንም መልኩ ዕድል ሊያገኝ አይገባም። ሕገ ወጥነት - የብሔርን፣ የሃይማኖትን፣ የፖለቲካ ቡድንን ወይም የሚዲያና የአክቲቪስትነትን ካባ ቢደርብም፣ ሕገ ወጥነት መሆኑ አይቀርም። አይጥ ምንም ዓይነት ቀለም ብትቀባ አይጥ መሆኗና ንብረት ማበላሸቷ አይቀርም።
ውድ ኢትዮጵያውያን፣
ስለ ጸጥታና ደኅንነት እየተናገርን በሕግ ከተቋቋሙ የጸጥታ መዋቅሮች ውጭ የታጠቁ የጸጥታ አደረጃጀቶች እንዳሻቸው እንዲሆኑ መፍቀድ ተገቢ አይደለም። በሀገር ውስጥ ኃይልን በብቸኝነት የመጠቀም መብት ለመንግሥት የተሰጠ መብት ነው። ዜጎች በሰላም ጊዜ አልሚ፣ በጦርነት ጊዜ ተፋላሚ መሆናቸው ከጥንትም የነበረ ነው። ያ ማለት ሀገር ስትወረር ሁሉም ለሀገሩ ተፋላሚ ይሆናል፤ ሀገር ሰላም ስትሆን ደግሞ ሁሉም ወደ ሕጋዊ ማሕቀፍ ይገባል ማለት ነው።
ከዚህም በተጨማሪ በሚዲያ፣ በአክቲቪስትነት፣ በፖለቲካ ቡድን እና በብሔር ስም የሚደረግ ሀገር የማፍረስ ሤራን መንግሥት በምንም መልኩ እንደማይታገሥ መታወቅ አለበት። የሃይማኖት ተቋማት የሰላምና የጤናማ ማኅበረሰብ መገንቢያ ማዕከላት እንጂ የአክራሪዎችና የሀገር አፍራሾች መናኸሪያ እንዲሆኑ ሊፈቀድ አይገባም። ሃይማኖቶች በስማቸው ጥፋት የሚፈጽሙ ነውረኞችን መቆንጠጥ ሲገባቸው ችላ በማለታቸው ጥፋት ፈጻሚዎቹ የልብ ልብ እየተሰማቸውና ተቋማቱን እንደከለላ በመቁጠር በድርጊታቸው ቀጥለውበታል። በሀገራችን ሃይማኖት ተኮር ጥፋቶች በዘላቂነት ሊቀንሱ የሚችሉት አንዱ ወደሌላው ጣት በመቀሰር ሳይሆን ሁሉም በቅድሚያ በራሱ ተቋም ውስጥ የሚሸሸጉ ጥፋት ፈጻሚዎችን ምሽግ ለማሳጣት ሲችል ነው። ለዚህ ደግሞ ምእመናንና የሃይማኖት አባቶች የሚገባቸውን ኃላፊነት ሊወጡ ይገባል።
በአጠቃላይ የተጀመረው ሰላምና ጸጥታን የማስፈን፣ ሕግና ሥርዓትን የማስከበር፣ ብሎም የኢትዮጵያን ብልጽግና በጽኑ መሠረት ላይ የመገንባት ተግባር ከግብ እንዲደርስ፤ የተጀመረው ሕግና ሥርዓትን የማስከበር ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል። መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጸጥታ አካላት ጋር በመሆን የዜግነት ድርሻውን እንዲወጣ ብሔራዊ የጸጥታ ምክር ቤቱ ጥሪ ያቀርባል።
የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት
ሰኔ 1፣ 2014 ዓ.ም
አዲስ አበባ

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

Ministiroota Itiyoophiyaa har'a muudaman

Ibsa Dhaabbatummaa Dh.D.U.O

Eessa turre,Maalirra Geenyeerra? Kutaa 4ffaa