"አንድ ሰው በህይወቱ ምግብ የሚበላበት ካጣ ከዚህ በላይ ፈተና የለም!"
"ተፈትኛለሁ!" ብሎ ነበር። አዎ በአስር አመቱ ወላጆቹን አጣ። በዚያ ሚጢጢዬ እድሜው መከራን ከነገፈቷ ተቀበላት።
"አንድ ሰው በህይወቱ ምግብ የሚበላበት ካጣ ከዚህ በላይ ፈተና የለም!" ይላል። እናም ተፈትኖ ላለመውደቅ ትንሹ ዳዊት ሲጋራ ከመሸጥ ጀምሮ ያልሰራው ስራ እንዳልነበር ይናገራል።
"መቀሌ ገበያ ላይ ያሉ ነገሮችን ሁሉ እሸጥ ነበር!" ይለናል መቀሌ ተወልዶ አይደር የተማረው ድምጻዊ ዳዊት ነጋ። ተስፋ መቁረጥ ሽንፈት የሚመስለው ድምጻዊ ኑሮን ለማሸነፍና ውሰጡ የሚንቀለቀለውን የሙዚቃ ፍቅሩን ጫፍ ለማድረስ መከራን ተቀብሏል።
"ሰርከስ ትግራይ ለመዝፈን ሄድኩኝ። በጊዜው አልተቀበሉኝም።...ማርሽ ባንድ ገባሁ። ድራመር ነበርኩኝ። ስድስት አመት ሰራሁ"
እንዲያ እያለ ተስፋ ባለመቁረጥ ወዳሰበው ቀረበ። የመጀመሪያ ስራውም 'ባባ ኢለን' አይኑን ገለጸለት። በሁሉም ሙዚቃ አፍቃሪያን ዘንድ ተወዳጅነትን አተረፈለት። በነጠላ ዜማውም ደጋግሞ ብቅ አለ። ወዛመይ፣ዘዊደሮ፣ቸኮላታ፣ኣጆኺ ትግራይ እና ሌሎቹም የዳዊትን የረጅም አመት ህልም እያሳኩለት መጡ። አክሱማዊት የተሰኘ ሙሉ አልበምም በመስራት ተወዳጅ ከሚባሉ ድምጻውያን ጎራም ተቀላቀለ።
ሰኔ 5 ቀን 2014 ዓ.ም ድምጻዊው ዜና ህልፈቱ ሲሰማ በርካቶች አዝነዋል። ሐዘኑንም እየተቀባበሉት ነው። ይህን ሳስብ በአንድ ወቅት ድምጻዊው ዳዊት ነጋ የተናገረው ትዝ አለኝ። እንዲህ ብሎ ነበር፦
"ታላላቅ ስራ የሚሰሩ የሀገራችን ሰዎችን በህይወት እያሉ የማመስገን ችግር አለብን። አንድ ሰው በህይወት እያለ ነው ማመስገን ያለብን።...ከሞተማ ሙቷል። የትም ሆኖ አይሰማውም። የሆነ ሰው በአቅሙ የሆነ ስራ ለሀገሩ ከሰራ... ማድነቅ መቻል አለብን።... ማድነቅ በጣም ትልቅ ስልጣኔ ነው!"
የድምጻዊ ዳዊት ነጋን ነፍስ ይማርልን። ለቤተሰቦቹ፣ ለአድናቂዎቹ ጽናቱን ይስጥልን!
አስተያየቶች
አስተያየት ይለጥፉ